ፈልግ

ሄሮድስ ሕፃናትን አስገደለ ሄሮድስ ሕፃናትን አስገደለ 

ሄሮድስ ሕፃናትን አስገደለ

የአምላክ ልጅ ሕፃን በመሆን ወደ ምድር ሲወርድ የሰው ብዙ ሕፃናት በሰማዕትነት የሕይወታቸውን መስዋዕት በመክፈል ወደ ሰማይ ወጡ፡፡ ትናንት የአምላክ ልጅን ሥጋዊ ልደት በምድር አክብረን ዛሬ ደግሞ የእነዚህን ንጹሐን ሰማዕታት ሕፃናት ልደት በሰማይ አዲስ ሕይወት መጀመር እናስታውሳለን፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

ቤተክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ እነዚህን ሥጋ በለበሰ የእግዚአብሔር ልጅ ምክንያት የተገደሉትን ሕፃናት ታስታውሳለች፡፡ ንጉሥ ሄሮድስ የከዋክብት ተመራማሪዎች እንዳታለሉት ካወቀ በኋላ ተቆጥቶ ሕፃኑን ኢየሱስን አግኝቼ እገድለዋለሁ በሚል ቅዠት ወታደሮቹን ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ በዚያና በዙሪያዋ የነበሩትን ከሁለት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ እነርሱም ሄደው እንደ ታዘዙት አደረጉ፡፡ ያገኙዋቸውን ከሁለት ዓመት በታች ያሉትን ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጉያ ነጥቀው በሚያራራ ለቅሶአቸው ሳይራሩ በደነደነ ልብ ሁሉን የሚማርከውን የሕፃናት የዋህነት ሳይመለከቱ እነዚያን ሕፃናት ግማሾቹን በሰይፍ እየቆራረጡ ግማሾቹን ደግሞ ለስላሳ ሰውነታቸውን እንደ አፈር እያደቀቁ ጨረሱአቸው፡፡ ሰውነታቸው አፈር እስኪሆን ድረስ በምድር እየጣሉ ፈጁአቸው፣ አሰቃቂ ጭካኔ አሳዩ፡፡ በቤተልሔም ትልቅ ለቅሶና ዋይታ ተሰማ፡፡ መከራ የወረደባቸው ምስኪን እናቶች ልባቸው በሐዘን ተሰበረ፡፡ በምድር መንቀጥቀጥ እንደሚፈረካከስ እንደ ትልቅ ቋጥኝ ተሰነጠቀ (ማቴ. 2፣16-18) እነዚያ የደም እንባ ሲያፈሱና በሀዘን ዕብዶች ሲሆኑ ጨካኑ ሄሮድስ ግን “ክርስቶስ ገደልኩት” በሚል የሞኝነት ሐሳብ ቅዠት ይደሰት ነበር፡፡

ነገር ግን የፈጸመው ሕፃናትን የማስገደል ጭካኔ ሕሊናን የሚያሳርፍና የሚያስደስት አልነበረም፡፡ ሊደሰቱና ሊያርፉ የሚገባቸው የነበሩ እነዘያ ምስኪን ሐዘንተኛ እናቶች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ገና ለጋ ሕፃናት ልጆቻቸውን የዚህን ዓለም እድፍና ቆሻሻ ሳይነካቸው ወደ ሰማያዊ ብርሃን ክብር ትተዋቸው ሄደዋል፡፡ ብላሽና ከንቱ የሆነውን ዓለም ትኩር ብለው ተመልክተው በሽታው ሳይነካቸው ልብሳቸውን በበጉ ደም ነጭ አድርገው ወደ ዘለዓለም ብፅዕና ተሻገሩ፡፡

ቤተክርስቲያን እነዚያን በክርስቶስ ምክንያት በግፍ የተገደሉትን ንጹሐን ሕፃናት እንደ ሰማዕታት የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ልጆች አድርጋ ታስባቸዋለች፤ የቅዱሳንንም ክብር ትሰጣቸዋለች፡፡

የሄሮድስ ተመሳሳይ አቻ የሌለው ጭካኔ በጣም ያስደነግጠናል፡፡ “ምንም በደል የሌለባቸውን ንጹሐን ሕጻናት እንደዚህ አድርጐ ማስገደሉ ርህራኄ የተለየው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው” እያልን ሄሮድስን በፍጹም እንጠላዋለን። ነገር ግን እስቲ በጥሞና በማስተዋል ራሳችንን በደንብ እንመርምር፡፡ አኛም እንደዚሁ ወይም ከእሱ የባሰ እናደርግ ይሆናል; ማን ያውቃል; በእርግጥ ሄሮድስ ትናንት እንዳደረገው ሁሉ ጨካኔ የሞላበት የሚቀፍ አደራረግ ማንንም ሰው በግፍ ያልበደሉ ሕፃናትን በሰይፍ ወይም በጐራዴ አንገድልም፡፡ እንደዚህ ያለ አስከፊና አሰቃቂ ግድያ ፈጽመን አናውቅም፡፡ በመጥፎ አብነት የመሰናከያ ምክንያት እየፈጠርን ከክርስቶስ እየጠየቅን ለዲያብሎስ ሰይፍ በማቀበል ስንቶችን ንጹሐን ምእመናን እንገድል ይሆናል; የባሰው እንግዲህ የሥጋ ግዲያ ሳይሆን የመንፈስ ግዲያ ነው፡፡ በመንፈስ ማበላሸትና መበከል ትልቅ ክፋትና በደል ነው፡፡ ልጆች ሲያድጉ ክርስቲያናዊ ሥነ-ሥርዓት አለማስያዝ ሲሳሳቱ አይቶ አለማረም ሲያጠፉ አለመገሰጽ ስድብ መሰደብ በመልካም አብነት ፈንታ መጥፎ አብነት ማሳየት ንጹሕ ነፍሳቸውን መግደል ነው፡፡

ሕፃናት በመንፈስ ከተበላሹና ከተበከሉ በሥጋም ሳይቀር ይበላሻሉ፡፡ ብዙ ልጆች በወላጆቻው መጥፎ አብነት ይሰናከላሉ፡፡ በወላጆቻቸውም ሰበብ መንገድ ይይዛሉ፡፡ ስንት ትንንሾች በትልልቆች መጥፎ አብነት ወደ ክፋት ያደላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በመጥፎ መንፈስ ሲሞሉ እንዴት ያለ ክፉት ነው; እንዴት ያለ ብርቱ ጨካኔ ነው; ከእነዚህ በእኔ ከሚያምኑት አንዱን ያሰናከለ ወዮለት! የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል” እያለ ኢየሱስ በብርቱ ያስጠነቅቀናል፡፡ እንግዲህ ታናናሾችን በመንፈስ እንዳናበላሻቸው እንጠንቀቅ፡፡ በእነርሱ ፊት ምግባራችንንና ንግግራችንን እናርም፣ የበጐ ምግባር እንጂ የክፉ ምግባር አብነት እንዳናሳያቸው እንጠንቀቅ፡፡ የኃጢአታቸውና የዘለዓለም በገሃነም ኩነኔያቸው ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች እንዳንሆን መሰናከያ ከሆን እንቆጠብ፡፡

12 January 2022, 12:49