ፈልግ

ቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ  

የቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበርተኞች 19ኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ከአራቱ አህጉራት የተላኩ የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ገዳም ማኅበርተኞች በሮም 19ኛውን የማኅበራቸው ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የማኅበሩ አባላት በጉባኤያቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የወንጌል ተልዕኮ ለማሳካት በዛሬው ዓለም ውስጥ ያደረጓቸውን እርምጃዎች በማብራራት በቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ምኞት እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳቦች መካከል ያለውን ግንኙነት መመልከታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ማኅበር አባላት፣ በትላልቅ ከተሞች ዳርቻ የሠፈሩ ድሃ ሕዝቦችን ጨምሮ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን እና የድህነት ሕይወትን በመሸሽ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚሰደዱት እና በገጠራማው አካባቢዎች ለሚኖሩ አናሳ ማኅበረሰቦች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ መግለጫ ክፍል አመልክቷል።

የተስፋ ጭላንጭል ፍለጋ

በቁጥር ወደ ሰባ የሚሆኑ የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ማኅበር ልኡካን፣ 150 ዓመታትን ባስቆጠረው የማኅበሩ ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የተባለለትን 19ኛ ጠቅላላ ጉባኤን በመካፈል ላይ መሆናቸው ታውቋል። ማኅበሩ በክርስትያን ማኅበረሰብ መካከል፣ በሀገረ ስብከቶች፣ በትምህርት ማዕከላት፣ በቤተ ክርስቲያን እና ሕዝባዊ ተቋማት መካከል በመገኘት ሰላምን እና ፍትህን ለማስፈን እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል። የማኅበሩ አባላት የተስፋ ምልክቶችን፣ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚሹ ድክመቶችን በመለየት፣ ተልዕኮአቸውን በሚወጡባቸው አካባቢዎች ረጅም ስብሰባዎችን በማድረግ ልዩ ልዩ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ሲዘጋጅ መቆየታቸው ታውቋል። በጉባኤው መካከል ለውይይት ከቀረቡት ርዕሦች መካከል የአገልጋይነት ጭብጦች ማለትም ለተልዕኮው የተለዩ አገልግሎቶች፣ አዳዲስ ዕጩዎችን ማዘጋጀት፣ ኢኮኖሚያዊ ግብአቶች እና የማኅበሩ ደንብ ተሃድሶ የሚሉት ይገኙበታል። የማኅበሩ አባላት በእነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አንድ ወር የሚቆይ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ታውቋል። ጉባኤው እሑድ ግንቦት 28/2014 ዓ. ም. የማኅበሩ ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በይፋ መጀመሩ ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ወቅት የጉባኤው ተካፋይ የማኅበሩ አባላት ለግል ጥቅም ሳይሆን ለሕዝብ ጥቅም እንደሚሠሩ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ከማኅበሩ ጎን በመቆም በተልዕኮ፣ በአባላት ስልጠና፣ በኢኮኖሚ እና በዋና ጸሐፊነት መስክ በዋጋ ሊተመን የማይችል አገልግሎታቸውን ያበረከቱ አራት የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ማኅበር ታዛቢዎች፣ አስተባባሪ እና ሁለት ጸሃፊዎች መገኘታቸው ታውቋል።

ከቅዱስ ዳ. ኮምቦኒ ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር መስደድ

የማኅበሩ ተወካዮች በጉባኤው መጀመሪያ ቀናት እርስ በእርስ ከተዋወቁ በኋላ በጸሎት ተደግፈው በጉባኤው ላይ ለማቅረብ የተመኟቸውን ሃሳቦች “ከቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ጋር በመሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር መስደድ” የሚለውን የጉባኤውን መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ጉባኤ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ተልዕኮ ሁለት አምዶች የሚገኙበት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ. 15 ላይ በሕይወቱ ወሳኝ ወቅት ጓደኞቹ ዘወትር ከእርሱ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንዲኖራቸው በጋበዛቸው እና ቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በአፍሪካ ምድር ተልዕኮውን የጀመረ ደፋር ነቢይ እንደነበር የሚገልጹ መሆናቸው ታውቋል።

የአራቱ አህጉራት አስቸኳይ ጉዳዮችን በተመልከተ

የማኅበሩ ተወካዮች በመጀመሪያዎቹ የጉባኤ ቀናት ውስጥ ጊዜያዊ ሕግጋት ያጸደቁ ሲሆን በጊዜያዊ ሕጉ ላይ ተሰብስበውበት ለጋራ ጉዞ የሚረዱ ምክር ቤቶችን መርጠዋል። የውይይት መድረኩን የሚያስተባብር ማዕከላዊ አካል፣ የጉባኤውን እንቅስቃሴ መደበኛነት የሚቆጣጠር ልዩ አካል፣ በጉባኤው ወቅት የሚቀርቡ የጋራ ጸሎቶችን የሚያስተባብር አካል፣ ባሕላዊ የመዝናኛ ጊዜዎችን እና የማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎትን የሚያስተባብር አካልን መርጠዋል። የጉባኤውን ሂደት የሚከታተሉ አካላት ከተመረጡ በኋላ ወደ መጀመሪያው የማዳመጥ ምዕራፍ ለመግባት የሚያግዙ የጉባኤው መንገዶችን አባላት ማመቻቸታቸው ታውቋል። በተግባር በተከናወኑ ተልዕኮ ሪፖርቶች እና በአራቱም አህጉራት ውስጥ የሚታዩ የተለያዩ እውነታዎችን ለመመልከት ዓይንን እና ልብን ለመክፈት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ማግኛ ልዩ ጊዜን መመደባቸው ታውቋል። አድናቆት በተመላበት መንገድ የሕይወት ፍሬዎች ተግዳሮቶችን እና በሽታዎችን ለማከም፣ ለእድገት እና ለውጥ ወሳኝ እድሎች መሆናቸውን ተመልክተዋል።

ቅዱስ ወንጌልን ዋና መመሪያ ማድረግ

በጉባኤው ላይ ከብዙ ባሕሎች እና ሕዝቦች ፣ ቋንቋዎች እና ወጎች የተወጣጡ አባላት ሃሳባቸውን ማካፈላቸው የተነገረ ሲሆን፣ የማኅበሩ አባላቱ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደሚሉት፣ ዘመኑ የሚገኝበትን የለውጥ ደረጃ ያገናዘቡ፣ የቅዱስ ወንጌልን መመሪያ እና የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ድፍረት የተላበሱ ሃሳቦችን ሰንቀው የመጡ መሆናቸው ተመልክቷል። አንድ ወር ሙሉ በሚቆየው ጉባኤያቸው የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ሚስዮናውያን ከተለያዩ ሕዝቦች ጋር ተሸክመው የቆዩትን የምድራችንን ፈተናዎች፣ ማኅበራዊ ቀውሶች፣ አመጾች እና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች፣ የኑሮ አለመመጣጠን እና ወረርሽኙ ያመጣውን መዘዞችን በጋራ እንደሚመለከቱት ታውቋል። እነዚህን ምድራዊ ችግሮች በኢየሱስ ክርስቶስ ተልእኮ ወደ አኗኗር ዘይቤዎች ለመለወጥ የሚያስችሉ የመፍትሄ መንገዶችን ከረጅም የጋራ ውይይት ለማግኘት ምኞት ያላቸው መሆኑ ታውቋል። ላጋጠማቸው ቀውሶች መፍትሄ የሚፈለግላቸው ርዕሠ ጉዳዮች፥ አጠቃላይ ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ፣ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመወስድ የመላው ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ፣ የሰላም እና የፍትህ ዓለም መገንባት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚያስገነዝቡት፣ በኅብረት መጓዝ እና ማለም የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ጠንካራ መሠረት ላይ ሲቆሙ መሆኑ ተገልጿል።

13 June 2022, 16:52