ፈልግ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ስርጭት በአፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ስርጭት በአፍሪካ  (AFP or licensors)

ለታዳጊ አገራት የአእምሮ ንብረት የባለቤትነት መብት እንዲሰጣቸው ተጠየቀ

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰናይ ድርጅት ከንግድ ጋር የተያያዘ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የአእምሮ ንብረት የባለቤትነት መብት ለታዳጊ አገራት እንዲሰጥ በማለት ጥያቄውን አቅርቧል። ጥሪው የቀረበው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማንም ሰው የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት ከማግኘት ወደ ኋላ እንዳይል በማለት ያቀረቡትን ማሳሰቢያ ተከትሎ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙ ታዳጊ አገራት የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርቧል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋራ ጥቅም ሲባል መረጃዎች እና የሕክምና ቴክኖሎጂዎች ለታዳጊ አገራት በነጻ ሊሰጡ እንደሚገባ ያቀረቡትን ማሳሰቢያ በመጥቀስ፣ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ከሰኔ 5 – 8/2014 ዓ. ም. እየተካሄደ ላለው 12ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ከዓለም ንግድ ድርጅት ጋር የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን በተመለከተ ከ18 ወራት በላይ ድርድር ሲያድርግ መቆየቱ ታውቋል። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እውነታ በዓለማችን ውስጥ በድሆች እና ለወረርሽኙ ተጋላጭ በሆኑት ሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል ውጤታማ፣ ሰፊ እና አጠቃላይ መፍትሄዎችን ለማግኘት እንደሚያግዝ ያለውን እምነት ገልጿል። ወረርሽኙ ሲከሰት የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን በደቡቡ የዓለማችን ክፍሎች ለሚገኙ አገራትም በመስጠት የወረርሽኙን መከላከያ ክትባቶች እንዲያመርቱ እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ የጤና ስርዓቶችን መገንባት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። አክሎም ክትባቶችን ለማምረት የሚያስችል ስልጠናን በመስጠት እና በማገዝ ፈጣን የእውቀት ሽግግር ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥረቱን ውጤታማ ማድረግ እንደማይቻል ግብረ ሰናይ ድርጅቱ አስታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ

በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ከሰኔ 5 – 8/2014 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ የሚገኝ 12ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለኮቪድ-19 ክትባት የአእምሮ ንብረት መብት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው፣ የተባበሩት መንግሥታት አካል የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆን እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቀዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በትዊተር ማኅበራዊ ድረ ገፃቸው ላይ ለፓን አሜሪካን እና ለፓን አፍሪካ ማኅበራዊ ፍትህ ዳኞች ኮሚቴ አባላት በላኩት መልዕክት፣ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለሁሉም ሰው በተለይም ለአፍሪካ ሕዝቦች ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማለት ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ ፍትሃዊ እና ደህንነታቸውን የተጠበቁ ውጤታማ ክትባቶችን ማግኘት ሕይወትን ከሞት አደጋ ለማትረፍ እንደሚያግዝ ገልጸው፣ የአፍሪካ አህጉር ወደ ኋላ መቅረት እንደሌለበት በማሳሰብ፣ ሁሉም ሰው ደኅንነቱ እስካልተጠበቀ ድረስ ማንም ሰው ከወረርሽኙ ሊተርፍ እንደማይችል አስረድተዋል። የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ከመጀመሩ በፊት ተደራዳሪዎች የዓለም ንግድ ድርጅት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት የሚሰጠውን ምላሽ ጨምሮ ሁለት ረቂቅ ጽሑፎች በማዘጋጀት ሥራቸውን ማጠናቀቃቸው ታውቋል።

ለእያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ መብት

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ጥሪ ያስተጋቡት፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አሎይስ ጆን፣ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሁኔታዎች ውስጥ በተለይም በወረርሽኙ ወቅት ሙሉ የጤና እንክብካቤ ማግኘት መሠረታዊ መብት እንደሆነ አስረድተው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ በጣለበት ጊዜ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ዜጎች ፍትሃዊ የሕይወት አድን ክትባቶችን ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ክትባት የተቀበሉ 17.6 በመቶው ብቻ ሲሆኑ፣ ቢያንስ የመጀመሪያ ክትባት የተቀበሉ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ብዛት 72.2 በመቶው መሆኑን መረጃው አስታውቋል።

የድሃ አገር ሕዝቦች ተረስተዋል

አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለበሽታው እና በሽታው ለሚያስከትላቸው ሌሎች ጉዳቶች የተጋለጡ ሲሆን፣ እነዚህ ሕዝቦች ፈጽሞ የተዘነጉ፣ የጤና እንክብካቤ የማይደረግላቸው፣ ክትባቶች እና አስፈላጊ የጤና መገልገያ መሣሪያዎች እና ኮቪድ-19ን እና አዳዲስ ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል ግብአት የሌላቸው መሆኑን ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰናይ ድርጅት መግለጫ አስታውቋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ መግለጫውን ሲያጠቃልል እንደገለጸው፣ የሚኒስትሮች ስብሰባ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳላሳየ ገልጾ፣ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት እንቅፋቶችን ለማስወገድ በሚሞክሩ አገሮች ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን እንደሚጥል፣ የኮቪድ-19 መድኃኒቶች ምርትን ይጨምር እንጂ ለኮቪድ-19 ቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሚያግዙ ሁሉንም የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት እንደማያካትት፣ የሕክምና እና የምርመራ ዘዴዎችን እንደማይሸፍን እና ሁሉንም አገሮች የማያካትት መሆኑን አመልክቷል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አሎይስ ጆን በመግለጫቸው፣ የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ሁሉም ሀገራት ውሳኔዎቻቸውን በሰብዓዊ መብት ማዕቀፍ ውስጥ በአስቸኳይ እንዲያስገቡ በማለት ጠይቀዋል። 

14 June 2022, 16:47