ፈልግ

የእንግሊዝ መንግሥት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዛወር የወሰደው ዕርምጃ የእንግሊዝ መንግሥት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዛወር የወሰደው ዕርምጃ  

ስደተኞችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማስገደድ የችግሩ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ተነገረ

በሕገወጥ መንገድ ወደ እንግሊዝ የገቡትን ስደተኞች ወደ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ለማጓጓዝ የእንግሊዝ መንግሥት በነደፈው ዕቅድ ላይ የተወያየ የእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ “ዕቅዱ ሰብዓዊነት ያለው ምላሽን የሚሰጥ ሳይሆን የስደተኞችን ስቃይ የሚያባብስ ነው” በማለት ተችቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእንግሊዝ መንግሥት በፈረንሳይ በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ግዛቱ ገብተው ለጥገኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ የሚጠባበቁ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማጓጓዝ የነደፈው ዕቅድ ከፍተኛ ትችቶችን እና ውዝግቦችን የፈጠረ መሆኑ ተነግሯል። ከእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል የተገኘው ዘገባ እንዳመለከተው፣ ጥገኝነት የጠየቁ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማስገደድ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት፥ የማኅበረሰብ መሠረት በሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የተወሰደ፣ ኃላፊነት የጎደለው ዕቅድ መሆኑን አስታውቋል።

ዕቅዱ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተወሰደ ሰብዓዊነት ያለው መፍትሄ ሳይሆን፣ ቀደም ብሎ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ሰቆቃን የሚያባብስ መሆኑን፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ ገልጸዋል። አክለውም፣ ወንጀል የሚቀረፈው ወንጀለኛውን በመጋፈጥ እንጂ ጉዳት የደረሰበትን ሰው በመቅጣት እንዳልሆነ ገልጸው፣ እቅዱ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ተስፋ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ችግሮችን የሚጨምር እንጂ ለስደት ለዳረጋቸው ማኅበራዊ ቀውስ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም ብለዋል።

የሰው ልጅ ትርፍ የሚገኝበት ሸቀጥ አይደለም

የስደትን ውስብስብነት በሚገባ የሚረዱት ብጹዓ ጳጳሳቱ፣ ኃላፊነቱን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል ገልጸው፣ የተቃውሞአቸው ዋና መነሻ፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮአዊ ክብር መሆኑን አስረድተዋል። “የክርስትና እምነታችን ለጥገኝነት ጠያቂዎች መልካም ምላሽ እንድንሰጥ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውንም እንድንጠብቅ እና እንድናስጠብቅ ይጠይቀናል” ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ “ጥገኝነት ጠያቂዎች ትርፍ የሚገኝባቸው ሸቀጦች ወይም ወደ ጎን የሚባሉ እና ማምለጫ የሚፈለግባቸው ችግሮች አይደሉም” በማለት አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት እንደተናገሩት፣ መኬድ ያለበት መንገድ፥ "ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ደኅንነታቸውን መጠበቅ፣ ማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ስደተኞች በማኅበራዊ ሕይወት እንዲታቀፉ ማገዝ ነው" በማለት መናገራቸውን ብጹዓን ጳጳሳቱ አስታውሰዋል።

ሥነ-ምግባር የጎደለው እርምጃ ነው

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጄስቲን ዌልቢ ከሌሎች የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር ፈርመው ይፋ ያደረጉት መልዕክት፣ “የመንግሥት እቅድ አሳፋሪ እና ሥነ-ምግባር የጎደለው ፖሊሲ ውጤት ነው” በማለት ገልጸውታል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጄስቲን ዌልቢ በመልዕክታቸው፥ "ለዘመናት ጠብቀው ያቆየዪዋቸው ክርስቲያናዊ እሴቶች መሸርሸራቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ ለዘመናት ሲደረግ እንደቆየው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በርኅራሄ ተቀብሎ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ እንደሚገባ ገልጸዋል። የእንግሊዝ መንግሥት በበኩሉ፣ “ዕቅዱ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞችን ተስፋ ለማስቆረጥ የተወሰደ እርምጃ ነው” በማለት የብጹዓን ጳጳሳቱን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል።

15 June 2022, 14:40