ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት በመመለስ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸውጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት በመመለስ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸውጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ውርጃ ሕይወት ማጥፋት ነው!”

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ያደረጉትን 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጸመው ወደ ሮም በመጓዝ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ከሃንጋሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ስላደረጉት ውይይት፣ ስለ ፀረ-ሴማዊነት ፣ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶች፣ ቅዱስ ቁርባንን ለፖለቲካ ባለስልጣናት መስጠት እና ውርጃን በተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መልስ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ውርጃን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ውርጃ ሕይወት ማጥፋት ነው! ስለሆነም ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም አቋሟን አትለውጥም፤ ብጹዓን ጳጳሳት የቤተክርስቲያን እረኞች በመሆናቸው ውርጃን አስመልክቶ ለሚሰነዘሩ ፖለቲካዊ አስተያየቶች ግልጽ አቋማቸውን ገልጸዋል። ውርጃ ነፍስ ማጥፋት ነው። ያለ ምንም ጥርጥር ውርጃን የሚፈጽም ነፍስን እያጠፋ ነው። በሕክምና ትምህርት ቤቶች ስለ ጽንስ የተጻፉ መጽሐፍትን ውሰዱ። ጽንስ ከተከሰተ ከሦስት ሳምንት በኋላ፣ እናትም ከማወቋ በፊት፣ የሕጻኑ ሁሉም አካላት ተፈጥረዋል። ዘረ-መልም እንዲሁ በስፍራው አለ። ታዲያ ይህ ሕጻን ሰው አይደለምን? በእርግጥ የሰው ሕይወት ነው! ለዚህ የሰው ሕይወት ክብር ሊሰጠው ይገባል። ይህ መመሪያ በጣም ግልጽ ነው። ይህን ለማይረዱ ሰዎች ሁለት ጥያቄዎችን ማቅረብ እፈልጋለሁ። አንድን ችግር ለመፍታት ተብሎ የሰውን ሕይወት ማጥፋት ተገቢ ነው? እንደ ሳይንሱ አገላለጽ ቢሆንም ጽንስ የሰው ሕይወት ነው።” በማለት መልስ ሰጥተዋል። ውርጃን በተመለከተ የቤተክርስቲያን አቋም ግልጽ እና የማያወላዳ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ቤተክርስቲያን ውርጃን ብትፈቅድ ኖሮ፣ በየቀኑ በርካታ የሰው ሕይወት እንዲገደል መፍቀድ ማለት ነው ብለዋል። በአገራቸው ውስጥ የሕዝብ ቁጥር መቀነሱን የገለጹላቸው የአገር መሪ መኖራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ውርጃን የሚፈቅድ ሕግ በመኖሩ ነው ብለው፣ በዚያች አገር በጥቂት ዓመታት ብቻ ስድስት ሚሊዮን ውርጃ መካሄዱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሃንጋሪ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ በሕዝቡ መካከል ጥልቅ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ስሜት መኖሩን እና አገሪቱ የበርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኗን አስረድተዋል። ሁኔታዎች ከተመቻቹ በሚቀጥሉ ጊዜያትም ሌላ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ ምኞታቸው እንደሆነ ለአገሪቱ ፕሬዚደንት መግለጻቸውን አስታውሰዋል። መላው አውሮፓን ያቀኑ የቀድሞ አባቶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አውሮፓ የቀድሞ አባቶችን መርህ እና ምኞት መከተል እንዳለበት ደጋግመው መናገራቸውን ገልጸዋል። አውሮፓ የአመራር ችግሮችን በማስወገድ፣ የቀድሞ ታሪኮቹን  በመመርመር የበለጠ ለመንከባከብ እና ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የአውሮፓ ሕብረትን ለቅኝ ግዛት ርዕዮተ ዓለም መጠቀሚያ መሣሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ መንግሥታት መኖራቸውን አስታውሰው፣ ይህም መልካም አለመሆኑን አስርድተዋል።

ለማኅበረሰቡ የሚሰጡ የተለያዩ ክትባቶችን በተመለከተ በስሎቫኪያ ውስጥ ባሉት ሀገረ ስብከቶች መካከል ልዩነት እንዳለ የሚነገረውን አስመልክተው በሰጡት መልስ፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ ክትባቶችን ሲወስድ መቆየቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ኩፍኝን ፣ ፖሊዮን እና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከል ክትባቶች ሲሰጡ እንደነበር አስረድተዋል። በማኅበረሰቡ መካከል የታዩት ልዩነቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወረርሽኞች ላይም “የክትባቶቹ የመፈወስ አቅማቸው ዝቅተኛ ነው” የሚል አስተሳሰብ ያስከተለው ፍርሃት መሆኑን አስረድተዋል። ልዩ የሕክምና ዕርዳታን በማግኘት ላይ ካሉት ሕሙማን በስተቀር በቫቲካን ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት በሙሉ ሁለቱንም ዙር የኮቪዲ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶችን የተቀበሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

17 September 2021, 16:06