ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “በእግዚአብሔር መታመን ለማገልገል ያለንን ፍላጎት ያረጋግጣል።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት እሑድ መስከረም 9/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል። በላቲን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት ለዕለቱ በተመደበው በማር. ምዕ. 9: 30-37 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር መታመን ሌሎችን ለማገልገል ፍላጎት እንዳለ ያረጋግጣል ብለዋል። ክቡራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን ያቀረቡትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን ተርጉመን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከማር. ምዕ. 9: 30-37 የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ በመንገድ ላይ ሳሉ እርስ በእርስ ይከራከሩበት ስለነበረው ጉዳይ ላይ ነበር። ይህም በቁ. 34 ላይ የተጻፈው እና “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” የሚል ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ

ዛሬ በዘመናችንም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውን ንግግር እንዲህ በማለት ተናገራቸው። እንዲህም አለ። “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ማናቸውም ሰው የሁሉ መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት” አላቸው። (የማር. 9:35) “የመጀመሪያ መሆን ከፈለጋችሁ ከሁሉ የበታች በመሆን የሁሉ አገልጋይ መሆን ይኖርባችኋል አላቸው”። ጌታችን ኢየሱስ በዚህ አስደንጋጭ ንግግሩ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ በእርግጥ አስፈላጊ ሆነው የቆዩ መስፈርቶችን ሻራቸው። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ የሰው ልጅ ማንነት በሥራው፣ በባንክ ባስቀመጠው የገንዘብ መጠን አይለካም። ፈጽሞ በእነዚህ ነገሮች ላይ አይመካም። በእግዚአብሔር ዓይን የሰው ልጅ ትልቅነት የሚለካው በሌላ መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ዓይን የሰው ልጅ ትልቅነት የሚለካው በአገልግሎቱ ነው። ባለው የሃብት መጠንም ሳይሆን ካለው አውጥቶ በሚሰጠው ነው። የመጀመሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ? እንግዲህ ሌሎችን አገልግሉ፤ መንገዱ ይህ ነው።       

ዛሬ “አገልግሎት” የሚለው ቃል ብዙም አይሰማም ወይም ጎልቶ አይታይም። ነገር ግን በወንጌል ውስጥ ግልጽ እና ተጨባጭ ትርጉም አለው።  አገልጋይ ሲባል ጥሩ አገላለጽ የለውም። አገልጋይ ማለት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን ማለት ነው። ሕይወቱንም እንዲህ በማለት ገልጾታል፥ “የሰው ልጅ እንኳ ለማገልገል እና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (የማር. 10:45) ይህ ኢየሱስ ያለው ነው። ስለዚህ ኢየሱስን መከተል የምንፈልግ ከሆነ እርሱ የሄደበትን የአገልግሎት መንገድ መጓዝ አለብን። ለእርሱ ያለን ታማኝነት የሚገልጸው ለማገልገል ባለን ፍላጎት ነው። ይህም ብዙን ጊዜ ዋጋን እንደሚያስከፍለን እናውቃለን። ምክንያቱም ስቃይ ስላለበት ነው። ነገር ግን ለሌሎች ያለን እንክብካቤ እና አለኝታነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድግ ከሆነ ውስጣችንን ነጻ አድርገን ይበልጥ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል እንችላልን። ሌሎችን ብዙ ባገለገልን ቁጥር እግዚአብሔር በውስጣችን መኖሩን እንገነዘባለ። በተለይም ውለታን መመለስ የማይችሉትን፣ ድሆችን፣ ችግራቸውን እና ጥያቄያቸውን በርኅራሄ የምንቀበል ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ማወቅ እንችላለን።

ስለ አገልግሎት አስፈላጊነት ይህን ያህል ካልኩ፣ ኢየሱስ ይህንን ለማስረዳት አንድ ነገር በትክክል ፈጽሟል። የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራት ከሚጠቀማቸው ንግግሮች በላይ መሆናቸውን ተመልክተናል። ተግባሮቹስ የትኞቹ ናቸው? አንድ ሕጻን ልጅ አምጥቶ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ቦታ፣ በደቀ መዛሙርቱ መካከል አቆመው፤ (ማር. 9:36) ይህ ሕጻን እንደ ትንሽነቱ ምስኪንነትን አያመለክትም። ሕጻናት የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለማግኘት በትልልቆች ይመካሉ። ኢየሱስ ታዲያ እነዚያን ሕጻናት በማቀፍ፣ “እንደዚህ ካሉት ሕጻናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ብቻ ሳይሆን የላከኝንም ይቀበላል።” (ማር. 9:37) ከሁሉም በላይ ሊገለገሉ የሚገቡት ለተደረገላቸው ነገር ምንም ዓይነት ውለታን መክፈል የማይችሉ ናቸው። ውለታን መክፈ የማይችሉትን ማገልገል ያስፈልጋል። ዝቅተኞችን እና የተናቁትን ተቀብለን የምናስተናግድ ከሆነ ኢየሱስን ተቀብለን እናስተናግዳለን ማለት ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ በእነርሱ ውስጥ ይገኛልና። ዝቅተኞችን እና ድሆችን በምናገለግልበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ርኅራሄ እንቀበላለን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ቅዱስ ወንጌል የሚያቀርብልን ጥያቄ ተቀብለን እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ፣ በሌሎች ዘንድ የተናቁትን ለመቀበል ፍላጎት አለኝ? ወይስ እንደነዚያ ደቀ መዛሙርት የግል ፍላጎትን ለማሟላት እሻለሁ? ሕይወትን የምረዳው ሌሎች ባለፉበት እኔ ቦታን ለማግኝት መወዳደር ወይስ፣ መጀመሪያ መሆን ማገልገል እንደ ሆነ አምናለሁ? ባለኝ ጊዜ ድሆችን ወይም ውለታን መመለስ የማይችሉትን ማገልገል እፈልጋለሁ? ግድ የሚለኝ ድሆችን እና አቅመድ ደካሞችን ወይስ ዘመዶቼን እና ጓደኞቼን? እነዚህ ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሌሎችን ማገልገል ዝቅ የሚያደርገን ሳይሆን የሚያሳድገን መሆኑን መረዳት እንድንችል፣ ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ እንደሚገኝ ማወቅ እንድንችል፣ የእግዚአብሔር ትሁት አገልጋይ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

20 September 2021, 16:55