ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም የእምነታችን ምሳሌ መሆኗን ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከለኛው የአውሮፓ አገሮች፣ በሃንጋሪ እና በስሎቫኪይ ያደረጉትን 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በስሎቫኪያ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አጠቃልለዋል። በስሎቫኪያ ሳስቲን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ ብሔራዊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በመገኘት፣ በርካታ ምዕመናን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ክቡራን ካኅናት ደናግል የተገኙበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓትን መርተዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት የስሎቭኪያ ምዕመናን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመምሰል የትንቢታዊነት እና የርኅራሄ መንገድ እንዲከተሉ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ መስከረም 5/2014 ዓ. ም የተከበረውን ዓመታዊ የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል፣ ከ90 ብጹዓን ጳጳሳት፣ ከ500 በላይ ካህናት እና 60,000 ከሚሆኑ  ምዕመናን ጋር በኅብረት አክብረዋል። የመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት የተዘጋጀበት ሥፍራ ከዋና ከተማው ብራትስላቫ በስተሰሜን 71 ኪ. ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የስሎቫኪያ ባልደረባ የሆነች የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኝበት ቦታ መሆኑ ታውቋል።     

የቅድስት ማርያም እምነት የመንገዳችን መሪ ነው

“የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እምነት የትንቢት እና የርኅራሄ መንገድ ነው” ባሉት ርዕሥ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከሁሉም አስቀድሞ ማርያም በልቧ ውስጥ የያዘችው እምነት ለጓዞዋ የጠቀማት መሆኑን አስታውሰዋል። ከመልአኩ ገብርኤል ከተቀበለችው መልዕክት በኋላ እንደ አዳኙ እናት መመረጧን እንደ ልዩ መብት ሳትቆጥር፣ በትህትናዋ የተሰማትን ደስታ በከንቱ ሳታባክን እና ስለ ራሷም ሳትጨነቅ፣ እንደ ተልእኮ የተቀበለችውን ስጦታ በተግባር መግለጽ እንዳለባት በመገንዘብ ኤልሳቤጥን ልትጎበኛት መሄዷን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ከእግዚአብሔር ዘንድ የደረሳትን አስቸኳይ ጥሪ በመቀብል ፣ የእግዚአብሔርን የማዳን ፍቅር ለሰዎች ሁሉ ለማድረስ በሮቿን ከፍታ ለመውጣት ብርታትን ያገኘች መሆኑንም አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ቅድስት ድንግል ማርያም በቤቷ ውስጥ የተረጋጋ ቀን ከመዋል ይልቅ በመንገዷ ሊያጋጥማት የሚችል ማንኛውንም ነገር ለመጋፈጥ፣ በሰላምና በፀጥታ አርፋ ከመዋል ይልቅ በጉዞ ምክንያት ሊሰማት የሚችል ድካምን ለማስተናገድ እና በእግዚአብሔር ላይ ባላት እምነት ሊያጋጥም የሚችል ማንኛውንም አደጋ፣ ሕይወትን ለሌሎች የፍቅር ስጦታ አድርጋ በማቅረብ ለማሸነፍ መወሰኗን አስረድተዋል።

በዕለቱ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ለመውሰድ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዟን የሚያስታውስ እንደነበር ታውቋል። ከዚያም በኋላ የተቀሩት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የሄደባቸውን መንገዶች የተከተለ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል የመጀመሪያ በመሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር ከመቆም ጀምሮ እስከ መቃብሩ ድረስ መጓዟን አስታውሰዋል።     

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለስሎቫኪያ ምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የእምነታቸው ተምሳሌት በማድረግ፣ በክርስትና ሕይወት ጉዟቸው፣ በጽኑ እምነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ጉዞ ወይም ንግደት ባለማቋረጥ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲመስሉ አሳስበዋል። የስሎቫኪያ ምዕመናን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት የሚያደርጉት ንግደት፣ የእምነት ፈተናን አሸንፈው፣ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻቸው እና ለእህቶቻቸው ፍቅር የሚያቀርቡበት መንፈሳዊ ጉዞ መሆኑን አስገንዝበዋል። ምዕመናን ኢየሱስ ክርስቶስን መፈለግ በሚያቋርጡበት ጊዜ፣ ብጹዓን ጳጳሳት እና ካኅናትም ኢየሱስ ክርስቶስን መፈልግ በሚያቋርጡበት ጊዜ ቤተክርስቲያን ሕመም የሚያጋጥማት በመሆኑ፣ የስሎቫኪያ ካቶሊኮች በሙሉ በጉዞአቸው እንዲጸኑ አሳስበዋል።  

የቅድስት ማርያምን እምነት እንደ ትንቢታዊነት መመልከት

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እምነት እንደ ትንቢታዊነት የተመለከቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕይወቷ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን መኖር፣ የእግዚአብሔር ምህረታዊ ጣልቃ ገብነት ዝቅተኛውን ከፍ እንደሚያደርግ፣ ኃያላንንም እንደሚያዋርድ የሚያመለክት ትንቢታዊ ምልክት ነው በማለት አስርድተዋል። በንጽሕናዋ፣ በድንግልናዋ በፍቅር የተቀደሰች እና እንከን የለሽ እንድትሆን የተጠራች በመሆኗ፣ እኛም እንከን የለሽ ሆነን በፍቅር ለቅድስና የተጠራን መሆናችንን የምታረጋግጥ ምልክት ናት ብለዋል።

ስምዖን በትንቢቱ፣ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎች ውድቀት እና መነሳት የቅራኔ ምልክት ይሆናል ባለው ላይ በማሰላሰል ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ሕይወትን የበለጠ ጣፋጭ ለማድረግ እምነትን ወደ ጣፋጭነት መቀየር አይቻልም” ብለዋል። ጨለማ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሁል ጊዜ እንደሚዋጋ ፣ ኢየሱስም ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን ለማምጣት የመጣ መሆኑንና ነገር ግን የእኛን ውሳኔ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። ከኢየሱስ ጋር ስንጓዝ አቋማችንን አንድ ማድረግ እንዳለብን፣ እርሱን ስንቀበል ፣ ቅራኔዎቻችንን፣ ጣዖቶቻችንን እና ፈተናዎቻችንን በመግለጥ፣ ስንወድቅ የሚያነሳን፣ እጃችንን ይዞ ጉዞን እንደገና እንድንጀምር የሚያግዘን፣ የትንሳኤያችን አምላክ ይሆነናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የስሎቫኪያ ክርስቲያኖች፣ በአኗኗራቸው የወንጌልን ውበት ማሳየት የሚችሉ ክርስቲያኖች ያስፈልጓታል ብለው፣ ብጹዓን ጳጳሳትም ይህንን መንገድ እንዲከተሉ አሳስበዋል። ስሎቫኪያ “ጥላቻ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ የሚያስታርቁ አባቶች፣ ኅብረተሰቡ በውጥረት እና በጸብ ውስጥ ሲገኝ መረጋጋትን እና ወንድማማችነትን የሚሰብኩ የሕይወት ሞዴሎች፣ ግለኝነት እና ራስ ወዳድነት እያደገ ባለበት ዘመን የእንግዳ ተቀባይነት እና የአብሮነት ጣፋጭ መዓዛን የሚያመጡ፣ ሞት በበዛበት ዘመን ሕይወትን ከአደጋ የሚከላከሉ ክርስቲያኖች ያስፈልጋታል” ብለዋል።

ቅድስት ድንግል ማርያም ርህሩህ እናት ናት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሳስቲን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብሔራዊ ቤተ መቅደስ በሚገኝበት ሥፍራ ያቀረቡትን ስብከት ባጠቃለሉበት ወቅት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቃና ዘገሊላ የሠርግ ድግስ ላይ በቂ ወይን መኖሩን ማረጋገጧን፣ በልጇ መስቀል ሥር ሆና የማዳን ተልእኮ መካፈሏን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲሠቃይ፣ ማርያም በመንፈስ የተሰቃየች፣ እንባችንን የምታደርቅ ፣ የምታጽናናንና የክርስቶስን የመጨረሻ ድል የምታመለክት ርኅሩኅ እናት መሆኗን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዚያ ሁከት መካከል ራሴን ላድን ሳትል፣ ወይም ሐዘኔን የማቃልልበት መንገድ ልፈልግ ሳትል፣ እግዚአብሔር ሕመምን እና ሥቃይን እንደሚቀይር እና ሞትን ድል እንደሚያደርግ በማመን በሐዘን ተሞልታ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር መቆሟን አስታውሰዋል።

የስሎቫኪያ ክርስቲያኖች፣ ርህራሄ ያለበት እምነት እንዲኖራቸው፣ ራሳቸውን ከድሆች፣ በመከራ ተጎድተው ከሚሰቃዩት እና የስቃይ መስቀላቸውን እንዲሸከሙ ከተገደዱት ጋር እንዲወግኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። እምነት ረቂቅ ሆኖ የማይቀጥል ነገር ግን ከችግረኞች ጋር ኅብረትን በመፍጠር ሥጋን እንደሚለስ አስረድተው፣ እምነት የእግዚአብሔርን አካሄድ በመከተል የዓለማችንን ሥቃይ የሚያስታግስ፣ የታሪክ አፈርን ውሃ በማጠጣት ወደ ሕይወት የሚመልስ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ውስጥ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ የአገሪቱ ባልደረባ በሆነች ሐዘንተኛይቱ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘት የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን እንደሚያቀርቡ፣ በቅርቡ ባደረጉት ሕክምና ወቅት ለረዳቻቸው ቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋናን ለማቅረብ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ጨምሮ በሌሎች ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን በሙሉ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በአደራ ለማቅረብ መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መግለጻቸው ይታወሳል።

16 September 2021, 16:29