ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ውስጥ ለተሰየሙት የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ንግግር ሲያደርጉ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ውስጥ ለተሰየሙት የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ንግግር ሲያደርጉ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በወንድማማችነት በመመራት ግንኙነቶችን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ጥር 2/2014 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ውስጥ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን እና ዲፕሎማቶችን ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለዲፕሎማቶቹ ባሰሙት ንግግር በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን በማሳደግ መልካም ግንኙነቶችን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህም ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ከምታቀርባቸው ሐዋርያዊ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል። በሕዝቦች፣ በባሕሎች እና በልዩ ልዩ የሐይማኖት መሪዎች መካከል ድልድይን በመገንባት መልካም ግንኙነቶችን መፍጠር የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዋና ዓላማ እና ጥረት መሆኑ ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ ሕዝቦች፣ ባሕሎች እና ልዩ ልዩ ሐይማኖቶች በግልጽ በሚታዩ እና በግልጽ በማይታዩ ምክንያቶች ተለያይተው እና ተራርቀው እንዲቆዩ ያደረጉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ደከመኝ ሳይሉ ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል። በሕዝቦች እና በባሕሎች መካከል ድልድይን መገንባት፣ በሐይማኖት መሪዎች መካከል እንዲሁም በፖለቲካ መሪዎች መካከልም ድልድዮችን መገባት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፍተኛ ጥረት መሆኑ ሲታወቅ በተለይም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዓለማችን በሁለት ጎራ ተከፍሎ በግልጽ እየታየ የመጣውን የልዩነት ግድግዳ ማፍረስ እጅግ አስቸኳይ ተግባር መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመገንዘባቸው፣ ዓለማችን ከዚህ ቀውስ ወጥቶ ወደ አንድነት ጎዳና እንዲመለስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ቅድስት መንበር የማስታረቅ ጥረታቸውን እንዲያደርጉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ሰኞ ጥር 2/2014 ዓ. ም. ለዲፕሎማሲ አካላት የዓለማችን ሰላም እና ጤና በማስመልከት ባሰሙት ንግግራቸው፣ ለአዲሱ ትውልድ ተስፋ ለማስጨበጥ ከተፈለገ የጋራ ውይይት እና መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህን እውን ለማድረግ መፍራት የለብንም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሕዝቦች መካከል የውይይት ባሕልን እና ወንድማማችነትን በማሳደግ ለሰላም ቦታን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በሕዝቦች መካከል ክፍተት እንዳለ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገሃድ ማድረጉን ለድፕሎማቶች ባሰሙት ንግግር ገልጸው፣ ይህን የመሰለ ማኅበራዊ ችግር ለማቃለል የተባበረ የጋራ እይታ ሊኖር እንደሚገባ አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “የህዝቦች ዕድገት” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ሰብዓዊነትን በማራመድ የምትታወቅ ቤተክርስቲያን፣ ሰላም እና የሕዝቦች ዕድገት፣ አካባቢያዊ ጥበቃ እና የሰው ልጅ መብት እርስ በእርስ የተገናኙ እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐስን ጳውሎስ ዳግማዊም በበኩላቸው፣ ቤተክርስቲያን ለሰው ልጅ የምታስብ እና የምትራራ መሆኗን ገልጸው፣ የሰው ልጅም ለቤተክርስያን ሕይወት ዋና መንገድ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። ከዚህ በፊት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፈለግ የተከተሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የፍቅር አስተምህሮችን በማጎልበት፣ ለሰው ልጆች ፍቅርን በማሳየት፣ በተለይም በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ለቆሰለው የሰው ልጅ በሙሉ፣ በቃልም ሆነ በተግባር ምስክርነትን መስጠት ከአገልግሎት ድርሻቸው መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

እ. አ. አ 2021 ዓ. ም. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለማችን ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ባስከተለበት ወቅትም ቢሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕዝቦች መካከል ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ ሲያመቻቹ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህን እውን ለማድረግ ዕቅዶችን መዘርጋት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጠንካራ የመገናኛ ድልድዮችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የምናቅደውን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማሳካት ባይቻልም፣ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ፍሬው የሚሰበሰብበት ትክክለኛ ወቅት ባይታወቅም “ሰላምን የሚያጠናክሩ እና የሚያሳድጉ ሰዎች ብጹዓን ናቸው” በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሰላምን ለማምጣት ከሚያደርጉት ጥረቶች መካከል ዋና ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀሰው በተገባደደው የአውሮፓዊያኑ ዓመት ብቻ እንዳልሆነ ተነግሯል። በኢራቅ ውስጥ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብዙዎች እንዲመክሩበት ያደረገ ቢሆንም፣ ነገር ግን  ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ትንቢታዊ መልዕክት የያዘ ሆኖ መገኘቱ ለቅዱስነታቸው ልዩ ክብርን ያስገኘ መሆኑ ታውቋል።

“ከጠላትነት ይልቅ ወንድማማችነት የበለጠ ጠንካራ ነው” በማለት በኢራቅ ውስጥ ለሞሱል ከተማ ሕዝብ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እውነተኛ ወንድማማችነትን ማሳየት እንደሚያስፈልግ፣ ሕዝቦችን ለማገናኘት የተገነባው ሰብዓዊ ድልድይ ሁሉን ሰው ሊያገናኝ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ሕዝቦች ምንም ያህል ቢራራቁ ሁልጊዜ ወንድማማቾች መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ የሰብዓዊነት ድልድይ ከሁሉም በላይ ተራርቀው የቆዩ ሕዝቦችን እንዲያገናኝ ማድረግ አለብን ብለዋል።

11 January 2022, 11:47