ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለምደርስባችሁ ተቃውሞ ሁሉ መልካም በማድረግ በጽኑ ውሳኔ ምላሽ ይስጡ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 19/2014 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 9፡51 -62 ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ለምደርስባችሁ ተቃውሞ ሁሉ መልካም በማድረግ በጽኑ ወሳኔ ምላሽ ስጡ ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ቃል

የሰማርያ ሰዎች ተቃውሞ

ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና “እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ ለማጥፋት አይደለምና” አላቸው፤ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።

ደቀ መዝሙርነት የሚያስከፍለው ዋጋ

በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጒድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው። ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው።

ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን ልቅበር” አለው። ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ። ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።   

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ እሁድ በስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ስለ አንድ ውሳኝ ነጥብ ይነግረናል። ይህም “ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ” (ሉቃ. 9፡51) ይላል። ስለዚህም ወደ ቅድስት ከተማ የሚያደርገውን "ታላቅ ጉዞ" ይጀምራል፤ ይህም ልዩ ውሳኔ የሚያስፈልገው የመጨረሻ ጉዞው ስለሆነ ነው። ደቀ መዛሙርቱ አሁንም ገና ዓለማዊ ስለነበሩ በጋለ ስሜት ተሞልተው፣ መምህሩ በድል አድራጊነት ሊገናኝ ነው ብለው አልመው ነበር። ይልቁኑ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ተቃውሞና ሞት እንደሚጠብቀው ያውቃል (ሉቃስ 9:22፣ 43-45)። ብዙ መከራ እንደሚደርስበት ያውቃል። ቆራጥ ውሳኔ የሚያስፈልገው ይህ ነው። እናም ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወሳኝ እርምጃዎችን በመውሰድ ወደፊት ሄደ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ከፈለግን ልንወስደው የሚገባን ተመሳሳይ ውሳኔ ነው። ይህ ውሳኔ ምንን ያካትታል? እኛ የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆን ያለብን፣ በቆራጥነት እንጂ እንደ አንዲት የማውቃት አረጊት ሴት እንደ ተናገረችው “በጽገሬዳ ቅጠል የተንቆጠቆጠ ውኃ ዓይነት ክርስቲያኖች” መሆን አይኖርብንም። አይ እንዲህ መሆን አይኖርብንም! ቆራጥ ክርስቲያኖች መሆን ነው የሚጠበቅብን። እናም ወንጌላዊው ሉቃስ ከዚህ በኋላ የተረከው ክፍል እንድንረዳ ይረዳናል።

ጉዟቸውን ጀመሩ። የሳምራውያን መንደር ኢየሱስ የጠላቶቻቸው ከተማ ወደ ነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ መሆኑን ባወቁ ጊዜ  ሊቀበሉት አልፈለጉም ነበር። ሐዋርያው ​​ያዕቆብና ዮሐንስ በጣም ተበሳጭተው ኢየሱስን ከሰማይ እሳት በማዝነብ እንዲቀጣቸው ጠየቁት። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ አለመቀበሉ ብቻ ሳይሆን ሁለቱን ወንድሞችም ገሠጻቸው። እነርሱ ኢየሱስን በበቀል ፍላጎታቸው ውስጥ ማሳተፍ ይፈልጋሉ እና እሱ በእዚህ ውስጥ መሳተፍ አልፈለገም (ሉቃስ 9፡52-55)። ኢየሱስ በምድር ላይ ሊያመጣው የመጣው “እሳት” ሌላ ነገር ነው (ሉቃስ 12፡49)። የአብ መሐሪ ፍቅር ነው። እናም ይህን እሳት እንዲያድግ ትዕግስት፣ ጽናት እና የንስሃ መንፈስ ያስፈልጋል።

ያዕቆብ እና ዮሐንስ፣ ይልቁንም ራሳቸውን በቁጣ ለማሸነፍ ፈቅደዋል። ይህ በእኛም ላይ የሚደርስብን፣ መልካም ነገር ስናደርግ ምናልባትም በመስዋዕትነት እንኳን ቢሆን፣ እንኳን ደህና መጣችሁ ከማለት ይልቅ የተዘጋ በር ስናገኝ ነው። ስለዚህ እንናደዳለን። ሰማያዊ ቅጣቶችን በማስፈራራት ራሱ አምላክን ለማሳተፍ እንሞክራለን። ኢየሱስ ይልቁንስ ሌላ መንገድ የወሰደው የቁጣ መንገድ ሳይሆን ወደ ፊት ለመጓዝ ቆራጥ ውሳኔ ነው፣ ይህም ወደ ጭካኔ ከመተርጎም ርቆ፣ እርጋታን፣ ትዕግሥትን፣ አርቆ አሳቢነትን እና መልካም ነገርን ከማድረግ ትንሽ ወደኋላ እንደማይል ያሳያል። ይህ የመሆን መንገድ ድክመትን አያመለክትም፣ እንዲህም አይደለም ነገር ግን በተቃራኒው እጅግ በጣም ጥሩ ውስጣዊ ጥንካሬን ያሳያል። ተቃውሞ ሲያጋጥመን በቁጣ እንድንሸነፍ መፍቀድ ቀላል ነው፣ በደመ ነፍስ የተሞላ ነው። ይልቁንስ አስቸጋሪው ነገር፣ ወንጌል እንደሚለው፣ “ወደ ሌላ መንደር ሄደ” (ሉቃስ 9፡ 56) ኢየሱስ እንዳደረገው በማድረግ ራስን መግዛት ነው። ይህ ማለት ተቃውሞ ሲያጋጥመን ያለምንም ነቀፋ ወደ ሌላ ቦታ መልካም ወደ መስራት መዞር አለብን ማለት ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ረጋ ያሉ፣ በተከናወነው መልካም ነገር የምንደሰት እና የሰውን ሞገስ የማንፈልግ ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል።

አሁን እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፣ በምን ደረጃ ላይ ነን? ምን ደረጃ ላይ ነው ሕይወቴ የምትገኘው? ተቃውሞ እና አለመግባባት ሲገጥመን ወደ ጌታ ዘወር እንላለን? በመልካም ሥራ ላይ ጽናት እንጠይቀዋለን? ወይንስ በጭብጨባ ማረጋገጫን እንሻለን፣ ሌሎች ሰዎች እኛ የምንለውን ካልሰሙን መራራና ቂም ቋጣሪዎች እንሆናለን? ብዙ ጊዜ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው፣ የሌሎችን ጭብጨባ እና ይሁንታ እንፈልጋለን፣ እና ነገሮችን ለጭብጨባ እንሰራለን። አይ እንዲህ ማደረግ ተገቢ አይደለም። ከአገልግሎት ውጪ መልካም መስራት አለብን እንጂ ጭብጨባን መፈለግ የለብንም። አንዳንድ ጊዜ የእኛ ግለት ለበጎ ዓላማ የፍትህ ስሜት ነው ብለን እናስባለን። ነገር ግን በእውነቱ ፣ ብዙ ጊዜ ከኩራት ፣ ከድክመት ፣ ከስሜታዊነት እና ከትዕግስት ማጣት ሌላ ምንም አይደለም። እንግዲያውስ ኢየሱስን ለመምሰል ብርታት እንጠይቀው፣ እርሱን በአገልግሎት ጎዳና ለመከተል፣ በቀል ፈላጊዎች ላለመሆን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙን አለመታገሥን፣ ራሳችንን ለበጎ ሥራ ​​ስናውል ሌሎችም ሳይረዱን ይህ ወይም እኛን ውድቅ በሚያደርጉበት ጊዜ እንኳን እኛ ተግባራችንን በዝምታ መቀጠል ይኖርብናል ማለት ነው።

ኢየሱስ በፍቅር እስከመጨረሻው ለመቀጠል የወሰነውን ውሳኔ እንድንከተል ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

26 June 2022, 11:03