ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በሮም ለሚኖሩ የኮንጎ ማህበረሰብ ‘ሰላም ከእያንዳንዳችን ይጀምራል’ ማለታቸው ተገለጸ!

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በሮም ከተማ ለሚኖሩ የኮንጎ ተወላጆች በተሰናዳው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ስብከት ምእመናን ለተጎዳችው ነገር ግን ሕያው ለሆነችው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላም እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

በመብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እሁድ ሰኔ 26/2014 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ባደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በዲሞክራቲክ ኮንጎ በቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያናቸውና በሐገራቸው ሰላም እንዲኖር ተማጽነዋል። ቀደም ሲል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሊያደርጉ ዝግጅታቸውን አጠናቀው የነበረ ሲሆን በጉልበታቸው ላይ በደረሰው የጤና እክል ምክንያት የጉዞ መርዓ ግብር ለሌላ ጊዜ መዘዋወሩ ተገልጿል።

ተልዕኮ

የደስታችን ምንጭ የሆነው የእግዚአብሄር መንግሥት መቅረብ በፍርሃት እንደሚሞላን፣ እንደሚያስደንቀን እና ህይወታችንን እንደሚለውጥ አረጋግጦልናል ሲል ቅዱስ ሉቃስ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ መግለጹን ቅዱስነታቸው በወቅቱ አስታውሰዋል። ይህም ደቀመዛሙርቱን ወደ ሩቅ ቦታ እንዲሄዱ፣ ተልእኮ እንዲቀበሉ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት መቅረቡን እንዲያውጁና የጌታን ቃል እንዲሰብኩ ያደረጋቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

"እራሳችንን በዓለም ላይ ያለን ተግባር ምን እንደሆነ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ምን ማድረግ እንዳለብን ብንጠይቅ፣ የወንጌል መልስ ግልጽ ነው፤ መልሱም ተልእኮ ነው" ብለዋል።

እንደ ክርስቲያኖች አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመካከለኛነት ወይም ለብ ባለ ሁኔታ ስንኖር ረክተን መኖር አንችልም፣ ምክንያቱም እኛ የኢየሱስ ሚስዮናውያን ነን፣ እናም “ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና ለእያንዳንዳችን ባዘጋጀው ሦስት የሚስዮናውያን ድንቆች” ወደ ዓለም ተልከናል ብለዋል።

የመጀመሪያው አስገራሚ ነገር እኛ የእርሱ መሣሪያዎች ነን

ልንወስደው የሚገባን መሣሪያ በተግባር ሲታይ ምንም ነገር እይደለም ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የገለጹ ሲሆን “ቦርሳ የለም፣ ምንም ዋስትና የለም፣ ምንም እርዳታ የለም” ብለዋል።

“ብዙውን ጊዜ የቤተክርስቲያናችን ውጥኖች በትክክል የማይሰሩ ይመስለናል፣ ምክንያቱም መገልገያዎች፣ ገንዘብ እና መንገዶች ስለሌሉን ነው ብለን እናስብ ይሆናል፣ ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም። ማስተባበያው የመጣው ከራሱ ከኢየሱስ ነው ብለዋል።

ምእመናን በቁሳዊም ይሁን በሰው ድህነት ላይ እምነት እንዳይጥሉ በማሳሰብ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን የቀጠሉ ሲሆን “ነጻ እና ቀላል፣ ትንሽ እና ትሑት በሆንን መጠን መንፈስ ቅዱስ ተልዕኮውን እየመራ በሄደ ቁጥር የድንቅነቱ ዋና ተዋናይ ያደርገናል” በማለት ተናግሯል።

ብቸኛው መሰረታዊ "መሳሪያ" ወንድማማችነት ነው፣ ምክንያቱም "ከኅብረት ውጭ የሆነ ተልዕኮ የለም። ምንም አይነት አዋጅ ለሌሎች ሳይጨነቅ መታወጅ አይችልም ብለዋል።

ሁለተኛ ድንቅ ነገር መልእክቱ ነው

ሁለተኛው የተልእኮው አስገራሚ ነገር “መልእክቱ” ነው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለአዋጁ ለመዘጋጀት “ደቀ መዛሙርቱ የሚናገሩትን መማር፣ ይዘቱን በደንብ ማጥናት እና አሳማኝ እና ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል” ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ መሆኑን አምነዋል።

ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የሰጣቸው ሁለት ትንንሽ ሐረጎችን ብቻ ነው፡- “ወደምትገቡበት ቤት መጀመሪያ፣ “ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን!” በሉ ሁለተኛው “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” በማለት መናገሩን አስታውሰዋል።

ሰላም ለኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ በየትኛውም ቦታ ክርስቲያን የሰላም ባለቤት ነው፣ ይህ የእሱ ወይም የእሷ መለያ ምልክት ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ጥርጣሬዎችን የሚያሰራጩ፣ መለያየትን የሚፈጥሩ፣ ኅብረትን የሚያደናቅፉ እና ንብረታቸውን ከሁሉም ነገር የሚያስቀድሙ በኢየሱስ ስም የሚሠሩ አይደሉም ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “ቂም የሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን የሚነዙ ወይም ሌሎችን ችላ የሚሉ ለኢየሱስ አይሠሩም። ሰላሙንም አያመጡለትም’ ማለታቸው ተገልጿል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ዛሬ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ እንጸልይ፣ ለቆሰሉ እና ለተበዘበዙ ሰዎች መጸለይ ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት “በዚህ ዓላማ መሠረት ክርስቲያኖች የሰላም ምስክሮች እንዲሆኑ፣ ማንኛውንም የጥላቻና የበቀል ስሜት እንዲያሸንፉ እንጸልያለን። ሌሎችን ወደ ንቀት የሚመራ ከቡድን ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ይወገድ ዘንድ እንጸልይ” ብለዋል።

"ወንድሞች እና እህቶች ሰላም ከእኛ ይጀምራል፣ ከአንተና ከኔ ይጀምራል፣ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ነው ሰላም የሚጀምረው” ብለዋል።

"ሰላምን በልባችሁ ውስጥ አኑሩ፣ ስግብግብነትን አስወግዱ፣ ጥላቻን እና ቂምን አጥፉ፣ ሙስናን እና ማጭበርበርን ሽሹ፣ ሰላም የሚጀምረው ከዚህ ነው" ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን ምእመናን ወደ ቤታቸው ሰላም እንዲያመጡና የትዳር ጓደኞቻቸውን በማክበርና በመውደድ፣ ልጆቻቸውን፣ ሽማግሌዎችንና ጎረቤቶቻቸውን በማክበርና በመንከባከብ እንዲጀምሩ ጋብዘዋል።

“በሰላም ኑሩ፣ ሰላምን ፍጠሩ፣ እና ሰላም በቤታችሁ፣ በቤተክርስቲያናችሁ፣ በአገራችሁ ውስጥ ይኖራል” ብሏል።

“የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” የሚለው የመልእክቱ ሁለተኛ ክፍል ተስፋን እና መለወጥን ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እናም “እርሱ የሁሉ አባት ነው፣ ሁላችንም ወንድሞች እና እህቶች እንድንሆን ይፈልጋል” ያሉ ሲሆን “በዚህ እይታ የምንኖር ከሆነ ዓለም የሰላም ገነት እንጂ የጦር አውድማ አትሆንም ነበር” ብለዋል።

ሦስተኛው አስገራሚ መንገድ ዘይቤ የሚለው ነው።

ከመሳሪያው እና ከመልእክቱ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት ሦስተኛው የሚስዮናውያን ግርምት የእኛን ዘይቤ ይመለከታል፣ ይህም ኢየሱስ ሕዝቡን “በተኩላዎች መካከል እንደ በጎች” ሆነው ወደ ዓለም እንዲሄዱ መጠየቁን ያስታውሰናል ብለዋል።

ስለራሳችን እንድንጨነቅ እና ከሁሉም በልጠን እንድንገኝ በሚጠይቀን ዓለም ውስጥ፣ ክርስቶስ የሚፈልገው ተኩላን ሳይሆን በግ እንድንሆን ነው ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስረድተዋል። "ይህ ማለት የዋህ መሆን ማለት አይደለም ነገር ግን የሁሉም የበላይ መሆንን እና ጥቅም ማጋበስን፣ የስግብግብነትን እና የንብረት ባለቤትነትን መጸየፍ ማለት ነው" ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዓመፅን እንደማይቀበሉ፣ ማንንም እንደማይጎዱ እና ሁሉንም እንደሚወዱ ክርስቲያኖችን በማሳሰብ ስብከታቸውን ደምድመዋል። "ዛሬ ሚስዮናውያን እንድንሆን ጌታ ይርዳን" ሲሉም ተማጽኗል "ከወንድማችን እና ከእህታችን ጋር አብረን እንድንሄድ፤ በከንፈራችን የእግዚአብሔርን ሰላም እና ቅርበት ይዘን የዋህነትን እና በጎውን የኢየሱስን ቸርነት በልባችን ተሸክመን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ እርሱን በመማጸን እና እርሱን በመያዝ መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል።

03 July 2022, 12:19