ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “መጽናናት ለመንፈሳዊ ሕይወት ታላቅ ስጦታ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 14/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። ከጣሊያን ከተሞች ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት የመጡ ምዕመናን ተከታትለውታል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ሳምንታዊ አስተምህሮአቸው፣ መጽናናት ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚጠቅም ታላቅ ስጦታ መሆኑን አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን ጠቅላላ የትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን ለዕለቱ እንዲሆን ያስተነተኑበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሚከተለው እናቀርባለን፥

“ነፍሴ በጸጥታ እግዚአብሔርን ትጠብቅ የለምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና። እርሱ ብቻ አለቴና መድኃኒቴም ነው፥ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ በፍጹም አልታወክም። ነገር ግን፥ ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን በጸጥታ ጥብቂ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና።" (መዝ. 62: 2-3 ፣ 6)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ባለፈው ሳምንት ከተመለከትናቸው አንዳንድ የብቸኝነት ገጽታዎች ቀጥሎ ለማስተዋል እጅግ አስፈላጊ የሆነውን መጽናናት እንመለከታለን። መጽናናት እንደ ተራ ነገር መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም መጽናናት ከሌለ አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።

ለመሆኑ መንፈሳዊ መጽናናት ምንድነው? መንፈሳዊ መጽናናት ጥልቅ የሆነ የውስጣዊ ደስታ ልምድ ነው። መንፈሳዊ መጽናናት አንድ ሰው በሁሉም ነገር እግዚአብሔር መኖሩን እንዲመለከት ያስችለዋል። እምነትን እና ተስፋን ያጠናክራል። እንዲሁም መልካም የማድረግ ችሎታን ይጨምራል። መጽናናትን የሚለማመድ ሰው በችግር ጊዜ ተስፋ አይቆርጥም። ምክንያቱም ፈተናን በእጅጉ የሚበልጥ ጠንካራ ሰላምን ያገኛልና። ስለዚህ መጽናናት ለመንፈሳዊ ሕይወት እና ለጠቅላላ ሕይወት የሚረዳ ታላቅ ስጦታ ነው።

መጽናናት ጥልቅ ማንነታችንን የሚነካ እንቅስቃሴ ነው። ቅዱስ እግናጤዎስ በመንፈሳዊ ልምምዶቹ ቁ. 335 እንደተናገረው፣ መንፈሳዊ መጽናናት አንዴ ታይቶ ወዲያው የሚጠፋ ሳይሆን በስፖንጅ እንደተቋጠረ ውሃ ቀስ በቀስ የሚንጠባጠብ ነው። መንፈሳዊ መጽናናት ያለው ሰው ዘወትር የራሱን ነፃነት በሚያከብር መልኩ በእግዚአብሔር እንደተሸፈነ ይሰማዋል። ለማድረግ የፈቀድነውን ነገር እንድናደርግ የሚያስገድደን አይደለም። አልፎ ተርፎም ዛሬ ተገኝቶ ነገ የሚጠፋ ደስታ አይደለም። በተቃራኒው እንዳየነው ሕመም እንኳ ቢሆን፣ ለምሳሌ ለአንድ ሰው ኃጢአትም የመጽናናት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ቅዱስ አውግስጢኖስ ከእናቱ ሞኒካ ጋር ስለ ውብ ዘለዓለማዊ ሕይወት ልምድ የተናገረውን እንመልከት፤ ወይም ቅዱስ ፍራንችስኮስ ፍጹም ደስታን ያገኘበትን ወይም ለመሸከም እጅግ ከባድ የሆኑ ሁኔታዎችን እናስብ።እንደዚሁም ሌሎች በርካታ ቅዱሳን እና ቅዱሳትን ስናስብ ትልቅ ነገር ማድረግ የቻሉት ችሎታ ስላላቸው ሳይሆን መረጋጋትን በሚሰጥ ጣፋጭ የእግዚአብሔር ፍቅር ስለተሸነፉ ነው። መንፈሳዊ መጽናናት ቅዱስ እግናጤዎስ ስለ ቅዱሳን ሕይወት ባነበበ ጊዜ በልቡ ያስተዋለው ሰላም ነው። ኤዲት እስታይን ሕይወቷ ከተለወጠ በኋላ የተሰማት ሰላም ነው። ምስጢረ ጥምቀትን ከተቀበለች ከአንድ ዓመት በኋላ እንዲህ በማለት ጽፋዋለች፥ ‘ራሴን ለዚህ ውስጣዊ ስሜት ባስገዛሁ ጊዜ ያለ ምንም የፍላጎት ውጥረት ቀስ በቀስ በአዲስ ሕይወት መሞላት ጀመርኩ፤ ወደ አዳዲስ ስኬቶችም ገፋፋኝ፤ ይህ ወሳኝ የመንፈሳዊ ሕይወት ምንጭ ከአንድ እንቅስቃሴ ወይም ከእኔ ኃይል የመነጨ ይመስላል፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይፈጥር በውስጤ ብርቱ ሆኖ ተገኘ።’ (Psychology and spiritual sciences, Città Nuova, 1996, 116)

መጽናናት ከሁሉም በላይ ተስፋን ያስታውሰናል። ወደ ፊት ተመልክተን እንድንጓዝ ያደርገናል፤  ቅድስት ኤዲት እስታይን ከምስጢረ ጥምቀት እንዳገኘችው ጸጋ፣ ያልታሰቡ ተነሳሽነቶች እንዲኖረን ያስችለናል።

መንፈሳዊ መጽናናት ልንቆጣጠረው የማንችለው፣ በሚፈለገው እቅድ የሚመራ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ስጦታ ነው። ርቀቶችን አስወግዶ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ የሚያስችል ስጦታ ነው። የሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ ቅድስት ቴሬዛ በአሥራ አራት ዓመቷ፣ ሮም የሚገኝ የኢየሩሳሌም ቅዱስ መስቀል ቤተ ክርስቲያን በጐበኘችበት ወቅት በክብር የተቀመጠውን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወጋባቸው ሚስማሮች መካከል አንዱን ሚስማር ለመንካት ሙከራ አድርጋ ነበር። ቅድስት ቴሬዛ ይህን ድፍረትዋን እንደ ፍቅር እና በራስ የመተማመን ምንጭ እንደሆነ ትናገራለች። በጽሑፏም እንዲህ በማለት ገልጻዋለች፥ ‘እኔ በጣም ደፋር ነኝ፤ እግዚአብሔር ግን የልብን ስለሚመለከት ሃሳቤም ግልጽ እንደነበረ ያውቃል... ፤ ሁሉ ነገር እንደተፈቀደልኝ የማምን እና የአብን ሃብት እንደ ራሴ የምቆጥር ልጅ ሆኜ አብሬው ሠራሁ።’ (የግል ሕይወት ታሪክ ቁ. 183) አንዲት የአሥራ አራት ዓመት ልጃገረድ ስለ መንፈሳዊ መጽናናት ምንነት ይህን የመሰለ ውብ መግለጫ ትሰጠናለች፡-‘እግዚአብሔር ርኅሩኅ አምላክ ነው፤ በሕይወቱ እንድንሳተፍ፣ እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር እንድናደርግ ባለው ፍላጎቱ ድፍረትን ይሰጠናል። ምክንያቱም ከእርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ስላለን ቤቱ ቤታችን እንደሆነ ይሰማናል። በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን እንዳገኘን፣ እንዳፈቀረን እና በእርሱ መታደስን እንዳገኘን ይሰማናል።’ በዚህ የማጽናኛ ምክር አንድ ሰው በችግሮች መካከል ተስፋን አይቆርጥም። በእርግጥም ቅድስት ቴሬሳ ምንም እንኳን ገና ልጅ ብትሆንም በዚህ ድፍረቷ ወደ ቀርሜሎስ ገዳም መግባት የሚያስችል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፈቃድ ጠየቀች፣ ተሰጣትም።

ሐሰተኛ መጽናናቶች መኖራቸውን ማወቅ ይገባል። በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ በሰዎች ዘንድ የሚታዩ እውነተኛ እና እውነተኛ ያልሆኑ መጽናናቶች አሉ። እውነተኛ መጽናናት እንደ ውሃ ጠብታ አንድ ባንድ የሚወርድ ከሆነ ገር እና ቅርብ ነው። አስመሳይነት ያለበት መጽናናት ግን ከፍተኛ ድምጽ ያለው እና ብልጭ ድርግም የሚል ነው። እንደ ገለባ እሳት ነው፤ ወጥነት የለውም፤ ለሌሎች ግድ የለውም። ሐሰተኛ መጽናናት መጨረሻ ላይ ባዶአችንን ያስቀራል። ከህልውናችን ያርቀናል።

ስለዚህ አንድ ሰው በሚጽናናበት ጊዜ ማስተዋል ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱም ሐሰተኛ መጽናናትን እንደ ግብ ከወሰድነው ክፉ እና እግዚአብሔርን ወደ መርሳት አደጋ ሊያደርሰን ይችላል። ቅዱስ ቤርናርዶስ፥ ‘ሰው እግዚአብሔርን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ማጽናናት ይፈልጋል!’ እንዳለው ማለት ነው። ባለፈው ሳምንት አስተምህሮአችን እንደተመለከትነው አንድ ሕፃን ወላጆቹን የሚፈልገው ከእነርሱ ዘንድ ማግኘት የሚፈልገው ነገር ስላለ ብቻ እንጂ አይፈልጋቸውም። እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ዝምድና የሕፃንነት ዝምድና ዓይነት ከሆነ፣ እጅግ ውብ ስጦታ የሆነውን እግዚአብሔርን ራሱን የማጣት አደጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን።”

23 November 2022, 15:46