ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሴቶች ላይ ጥቃትን ማድረስ እግዚአብሔርን ማሳዘን መሆኑን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ በሚል ዓላማ በየዓመቱ ኅዳር 16 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ቀን በማስታወስ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ዕለቱን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሰው ልጅ ስብዕና የሚለካው ለሴቶች በሚሰጥ ክብርና የአያያዝ መንገድ እንደሆነ አስታውሰው፣ በሴቶች ላይ ጥቃትን ማድረስ እግዚአብሔርን ማሳዘን እንደሆነም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ በሚል ዓላማ ከ1974 ዓ. ም. ጀምሮ ኅዳር 16 ቀን ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል። ኅዳር 16 ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1952 ዓ. ም. በዶሚኒካን ሪፑብሊክ መሪ ራፋኤል ትሩሂሎ ትእዛዝ በግፍ የተገደሉትን ሦስት የፖለቲካ አቀንቃኞች የሆኑ የሚራባል እህቶችን ለማስታወስ መመረጡ ይታወሳል።

ዋና ዓላማውም በዓለም ዙሪያ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ፣ ግንዛቤን በመጨመር ዓለም አቀፍ እርምጃዎችን ለመውሰድ፣ የመብት ተሟጋቾችን ቁጥር ለማሳደግ እና በሴቶች ላይ በሚደርሱ ችግሮች እና መፍትሄዎች ላይ ለመወያየት ዕድሎችን ለማመቻቸት መሆኑ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያቀርበው አኃዛዊ መረጃ በአማካይ በየ11 ደቂቃዎች ልዩነት አንዲት ሴት ወይም ልጃገረድ በገዛ ቤተሰቦቿ እጅ እንደምትገደል አመልክቷል።

ይህ አሳዛኝ ክስተት ይፋ የወጣው በተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ እፅ እና የወንጀል መከላከያ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርስ የግድያ ተግባር በተለምዶ እምነት በሚጥሉባቸው ሰዎች በኩል መሆኑን ገልጾ፣ ይህም ጾታን መሠረት ካደረጉ አሳዛኝ ጥቃቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጿል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ በሚል ዓላማ በየዓመቱ ኅዳር 16 የሚከበረው ዓለም አቀፍ ቀን፣ ቤት ውስጥ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመናገር ብቻ ሳይገደብ፣ ድምጻቸውን ወደ አደባባይ ለእንዲወጡ ለማድረግ እና ጉዳቶቻቸውን በሙሉ ለማውገዝም ጭምር እንደሆነ ታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ከሦስት ዓመት ገደማ ወዲህ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በቀዳሚነት በመከታተል ላይ ከሚገኙት ግለሰቦች የተገኙ መረጃዎች እና ሪፖርቶች፣ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ እየጨመሩ መሄዳቸውን አመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን የመምራት ሐዋርያዊ አደራን ከተቀበሉበት ጊዜ አንስቶ ሴት እህቶቻችንን ማክበር እንደሚያስፈልግ ዘወትር በመናገር፣ እንዲሁም በሴቶች ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረስ ወይም መበደል እግዚአብሔርን ማሳዘን መሆኑን በመግለጽ፣ ጉልበታቸውን ለሚበዘበዙ እና ጾታዊ ጥቃት ለሚፈጸምባቸው፣ ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ለተጋለጡት፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ ለሚወድቁት፣ በጦርነት አደጋ ውስጥ ለሚገኙት እና መድልዎ ለሚደረግባቸው ሴቶች በሙሉ በመጸለይ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

25 November 2022, 12:47