ፈልግ

በማዳስካር ድርቅ ያስከተለው ሰብዓዊ እና አካባቢያዊ ቀውስ በማዳስካር ድርቅ ያስከተለው ሰብዓዊ እና አካባቢያዊ ቀውስ 

ቅድስት መንበር፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ማግኘት መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት መሆኑን አስታወቀች

ጀኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ማግኘት የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት መሆኑን አስታወቁ። “ውሃ ሸቀጥ ሳይሆን የሕይወት እና የጤና ምንጭ ሁለንተናዊ ምልክት ነው” ያሉት የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እና የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ለሁሉም ሰው ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባዘጋጀው 48 ጉባኤን የተካፈሉት፣ የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ተደራሽነት ማረጋገጥ “የሰውን ልጅ ክብር ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው” ብለው፣ ቅድስት መንበር ምን ጊዜም ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በንፁህ የመጠጥ ውሃ እና በንፅህና አጠባበቅ ሰብአዊ መብቶች ላይ ያቀረበውን ልዩ ሪፖርት ዋቢ ያደረጉት ብጹዕ አቡነ ጆን፣ የመጠጥ ውሃን ወደ ሸቀጥነት መቀየሩ ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ጋር ተዳምሮ የውሃ እጥረትን ያባባሰው መሆኑን አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ

የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የውሃ ክፍተቱን ያስፋፋው መሆኑን ያስረዱት አቡነ ጆን፣ “ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ማግኘት ለሰው ልጅ ህልውና እና የሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊነት አስፈላጊ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ “ቴክኖሎጂ ባደገበት ዘመናችንም ቢሆን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ አልተቻለም” ብለው፣ የአየር ንብረት ለውጡ እና አሁን ላይ የሚታየው የጤና ቀውስ፣ የውሃ ክፍተትን የበለጠ አባብሶታል” ብለዋል። አክለውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዚህ በፊት የነበረውን ዝቅተኛ የጤና እና የኤኮኖሚ አለመመጣጠንን በማሳደግ፣ በድሆች መካከል በውሃ እጥረት ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ የጨመረው መሆኑን አስረድተዋል።

የንጹህ ውሃ ተደራሽነት ቅድሚያ የሚሰጠው የጋራ ኃላፊነት ነው

እንዲሁም የዓለም ማህበረሰብ ምን ያህል እርስ በእርሱ እንደተገናኘ አፅንዖት የሰጡት ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ ለንጹህ ውሃ እና ዓለም አቀፍ የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነት አጽንዖትን ሰጥተው፣ እነዚህን ሁለቱን ለተጠቃሚው በበቂ ሁኔታ እንዲደርሱ ማድረግ አስቸኳይ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ርዕሠ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጋራ ኃላፊነትም ጭምር ነው ብለዋል።

የተቀናጀ ጥረት መኖሩ አስፈላጊ ነው

ስለሆነም፣ ሁሉም ሰው ንፁህ እና በቂ ውሃ እንዲያገኝ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል በማለት፣ በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባዘጋጀው 48ኛ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር ንግግራቸውን ደምድመዋል።

20 September 2021, 17:22