ፈልግ

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት መታሰቢያ 

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ሥነ-ምሕዳርን የተመከተ ቅስቀሳ መጀመሩ አስታወቀ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ታኅሳስ 3/2014 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚሉ ሁለት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች በማስታወስ፣ የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት በማክበር ላይ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት አስታውሰዋል። ድርጅቱ ባሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ አገራት የሚገኙትን 162 ቅርንጫፍ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያስተባብር መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሰው ልጅ ክብር እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን ማድረግ የሚሉ ሁለት ርዕሠ ጉዳዮች በዓለማች ከተከሰተ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ለምድራች ጠቅላላ ሥነ-ምሕዳር እንክብካቤን በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ ዓለም አቀፉ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት አሳስቧል። “Together We” ወይም “በኅብረት ሆነን” በሚለው መሪ ቃል የተንቀሳቀስው የዘንድሮ በዓል ዋና ዓላማ፣ ዓለማችንን ያጋጠሙ መጠነ ሰፊ ችግሮችን በኅብረት ማስወገድ እንደሚገባ በሮም ኡርባንያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ስብሰባ ማሳሰቡን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ከዚህ በፊት ባዘጋጃቸው መርሃ ግብሮች በቂ የምግብ ዋስትና እና ስደተኞችን መደገፍ የሚሉ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚሉ ሁለት የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች ውስጥ በተጠቀሰው በጠቅላላ ሥነ-ምሕዳር ላይ ትኩረት ማድረጉ ታውቋል። “የነገን ለማሳመር ዛሬ እንጣር” በሚለው በዘንድሮ መሪ ሃሳቡ፣ በአገራት ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅቶች በዓለም አቀፉ የካቶሊክ በጎ አድራጊ ድርጅት ሥር በመሰባሰብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።  

የማኅበረሰቦችን ግንዛቤ ማሳደግ

“Together We” ወይም “በኅብረት ሆነን” የሚለው መሪ ቃል ዕቅድ፣ እርስ በእርስ በመደጋገፍ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ሦስት ደረጃዎች የያዘ መሆኑን የዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አሎይስ ጆን ገልጸዋል። የመጀመሪያው በአካባቢ መራቆት እና በድህነት መካከል ባለው ትስስር ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አቶ አሎይስ ገልጸው፣ ግንዛቤ የሚሰጥባቸው ርዕሠ ጉዳዮችም በቂ ምግብ እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት፣ ድህነት፣ መገለል እና የኑሮ አለመመጣጠን የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ግንዛቤ መስጠት የሚጀምርባቸው አካባቢዎችም ገጠራማ አካባቢዎች እና ቁምስናዎች መሆናቸውን አክለው አስታውቀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች

እያንዳንዱ ግለሰብ የለውጥ ተዋናይ ሊሆን እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ለዚህም ዝግጁ በመሆን የጋራ መኖሪያ ምድራችን ደህንነት የማይጎዱ የአኗኗር ለውጦችን ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በኦሽንያ በሚገኙ ትንንሽ የደሴት ግዛቶች እየሆነ ያለውን ነገር ለምሳሌ የጠቀሱት የቶንጋ እና የኒዩ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሶአኔ ፓቲታ ፓይኒ ማፊ፣ የጋራ መኖሪያ ምድርን የመንከባከብ ጽንሰ-ሀሳብ በደሴቶቹ ተወላጆች ዘንድ ለብዙ ሺህ ዓመታት ግልፅ ሆኖ የኖረ እንደነበር ገልጸው፣ አካባቢዎቹ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀቶችን ባያመነጩም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ እንደ ጎርፍ ፣ አውሎ ነፋሶች እና የአፈር መሸርሸር አደጋዎች የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የድሆችን ጩኸት ማድመጥ

ሁለተኛው ዕቅድ የድሆች ጩኸት በመንግሥታት እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘንድ ተደማጭነትን እንዲያገኝ ማድረግ ሲሆን፣ ፍትሃዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር በሚደረግ የፖለቲካ ውሳኔዎች ውስጥ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎች ድምጽ እንዲካተት ጥረት ማድረግ መሆኑ ታውቋል። ከግንዛቤ ወደ ተግባር በሚሸጋገርበት ምዕራፍ ማለትም እ. አ. አ. በ 2024፣ ኅብረተሰቡ ያገኘውን ልምድ በማነፃፀር በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚካሄድ የአንድ ሳምንት ስብሰባ መልካም ልምዶችን የሚጋሩበት እንደሚሆን ተገልጿል።

የቸርነት ሥራ የስብከተ ወንጌል መግለጫ ነው

"ይህ እንቅስቃሴ ለ70 ዓመታት በዘለቀ ጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ ነው" ያሉት የዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አሎይስ ጆን፣ የ “ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” ዓመታዊ በዓልን በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እ. አ. አ. በ1951 ተመስርቶ ዛሬ በተለያዩ አገራት የሚገኙ 162 ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያስተባብር መሆኑን ገልጸዋል። "የምናገለግላቸውን ሰዎች ማስታወስ አለብን" ያሉት ክቡር አቶ አሎይስ ጆን፣ ድርጅታቸው የሚረዷቸው ሰዎች የግጭት ሰለባዎች፣ መበለቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ሰብዕናቸውን የተነፈጉ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በቫቲካን የውጪ ጉዳይ ጽህፈት ቤት የመንግሥታት ግንኙነት ክፍል ምክትል ዋና ጸሃፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍራንቼስካ ዲ ጆቫኒ በበኩላቸው፣ በጎ ተግባር አዲስ ዓለም የሚገነባበት እና ትክክለኛ የወንጌል ስርጭት የሚገለጽበት መንገድ ነው ብለዋል። 

ቸርነት የቤተክርስቲያን ዋና ተግባር ነው

ያለፉትን 70 የቸርነት አገልግሎት ዓመታትን ያስታወሱት፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በበኩላቸው፣ የዕርዳታ ድርጅታቸው በድህነት ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና ውርደት፣ የአመለካከት ስርዓቶች እና ፖሊሲዎች በሰዎች ላይ የሚጫኑትን ግድየለሽነት ኢፍትሃዊነት በሚገባ መመልከቱን ገልጸው፣ ነገር ግን በዚህ ሁሉ የእንክብካቤ፣ የኅብረት፣ የርኅራሄ እና የመለወጥ ኃይልን መስክሯል ብለዋል።  “የድሆችን ጥንካሬ፣ ጥበብ እና ክብር፣ ተስፋ እና ደስታን ተመልክተናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ “ቸርነት የቤተክርስቲያን፣ የዓለም እና የድሆች ቀዳሚ ተግባር ነው” በማለት አስረድተዋል።

ወረርሽኙ ለድህነት ማደግ ምክንያት ሆኗል

በጣሊያን የሚገኝ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በሪፖቱ እንዳታወቀው፣ በዓለማችን ውስጥ በኮቪድ-19 የተያዙ 235 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታን የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር 40 ከመቶ መጨመሩን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 160 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ ማግኘታቸውን፣ 82 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቃይ መሆናቸውን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቂዎች ቁጥርም በእጥፍ ማደጉን እና የእርስ በእርስ ግጭቶችም 12 ከመቶ ማደጉን የጣሊያን ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ፓውሎ ቤቼጋቶ አስታውሰዋል።  

15 December 2021, 13:17