ፈልግ

ቱርክ የምታመርተው ሰው አልባ የመከላከያ አውሮፕላን ቱርክ የምታመርተው ሰው አልባ የመከላከያ አውሮፕላን  

ሰው ሠራሽ ልህቀትን በሰላማዊ መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቀረበ

ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት፣ የጦር መሣሪያን አስመልክቶ የተካሄደውን ጉባኤ የተካፈሉት የቅድስት መንበር ተወካይ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ የቫቲካንን አቋም መሠረት በማድረግ ባደረጉት ንግግር፣ እጅግ የላቀ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚመራው ድርጅት "የመላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ የጋራ ጥቅም" የሚያስከብር ዓለም አቀፍ አካል ሊኖር ይገባል በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዘመናችን ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እየዳበሩ ከመምጣታቸው የተነሳ ያለ ሰው ኢላማዎችን ለይተው መተኮስ የሚችሉ የሮቦት ወታደሮች መፈጠራቸው ይታወሳል። ዓለምን የሚያስጨንቅ፣ ሳይንሳዊ ልብወለድ የሚመስል ወታደራዊ ሳይንስ እድገት በሠራዊቱ ውስጥ በፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑ ሲታወቅ፣ ይህም በሰው ከሚመሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች የተለየ እንደሆነ ይነገራል። ቅድስት መንበርም በጉዳዩ ላይ አቋም በመያዝ በክልሎች መካከል ያለውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጠቃቀም ፍጹም ሰላማዊ ለሆነ ወታደራዊ ዓላማ ከመዋል ይልቅ ግልጽ የሆነ ሕግ ያለመኖሩ ያሳሰባት መሆኑን ገልጻለች።

አጠቃላይ ትጥቅ የማስፈታት ሂደት

ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ተገኝተው የቅድስት መንበርን አቋም የገለጹት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣ በጄኔቫ በተካሄደው ስድስተኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የተለመዱ የጦር መሣሪያዎች አጠቃቀምን የመከልከል ወይም የመገደብ ስምምነት ጎጂ እና የተዛቡ ተጽእኖዎችን ሊያከትል ይችላል በማለት ገልጸዋል። “ከፍተኛ ጥፋትን በሚያስከትሉ ራስ ገዝ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች” ዙሪያ የሚካሄዱ ውይይቶች፣ ሙሉ በሙሉ የጦር መሣሪያን ትጥቅ በማስፈታት ውጤታማ ዓለም አቀፍ ቁጥጥር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ለተግባራዊነቱ ከዚህ በፊት የታዩትን ፈቃደኝነቶችን አስታውሰው፣ በግጭቶች መካከል ተፈፃሚነት ያለውን ዓለም አቀፍ ህግ እና ደንብ ማዘጋጀት እና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር አሳስበዋል።

ጥፋት የሚያስከትሉ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች እና የሰው ቁጥጥር

ሮቦት-ወታደሮች “በሥነ ምግባራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች” ላይ ስጋትን እንደሚያስከትሉ የተናገሩት ብጹዕ አቡነ  ፑትዘር፣ በመሆኑም ከቅድስት መንበር አንጻር “በጦር መሣሪያ ሥርዓት ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው የሰው ልጅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ የድርጊታቸውን ውጤት ማየት እና መረዳት የሚችሉት የሰው ልጆች ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር፣  በጄኔቫ በተካሄደው ስድስተኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከላይ የተጠቀሱትን የሥነ ምግባር መርሆች ለመጠበቅ እና ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት ጋር መከበራቸውን ለማረጋገጥ በቂ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጠይቀዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ “ልዩ የህግ ደንቦች እና ማዕቀፎች በሌሉበት ወቅት ምርምሮችን፣ የጦር መሣሪያ ልማት እና አጠቃቀምን የሚመራው ሁልጊዜ የሰው ልጅ ነው” በማለት አስረድተዋል። በሶስተኛ ደረጃ፣ በጦር መሣሪያ ስርዓት ውስጥ የሰው ልጅ ቀዳሚ ሥፍራን ይዞ እንደሚገኝ እና ዋና ዓላማውን እና ውጤቱን መቃረን የሚቻለው ባህሪዎቹ ሁል ጊዜ በሰው ልጅ ቁጥጥር ውስጥ ሲገኙ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂን ለሰው ልጅ ጥቅም ማዋል

ስለዚህ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር በንግግራቸው፣ “ከፍተኛ ጥፋትን በሚያስከትሉ ራስ ገዝ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች” ዙሪያ መንግሥታት "የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዓለም አቀፍ ድርጅት ምስረታን ለማመቻቸት እና ሁሉም መንግሥታት በተቻለ መጠን ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ መረጃዎችን ለሰላማዊ የሰው ልጅ የጋራ ጥቅም የማዋል መብት ተረጋግጦ ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። በንግግራቸው መጨረሻ ላይም፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ በተስፋፋበት ባሁኑ ወቅት፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ዘርፍ ጠቅላላ የሰውን ልጅ እድገት እና ፍላጎት መሠረት ያደረገ ጠንካራ ምርጫ እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ፑትዘር ገልጸዋል።    

16 December 2021, 16:16