ፈልግ

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በቁምስና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በቁምስና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው 

ቫቲካን የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን መሰየም የሚያስችል ሥርዓት መዘጋጀቱን አስታወቀ

በቫቲካን የመለኮታዊ አምልኮ ሥርዓት እና የቅዱሳት ምስጢራት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ካቴኪስቶችን ወይም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን ለመሰየም የሚያግዝ ሥርዓት መዘጋጀቱን አስታውቋል። ሥርዓቱ በሥነ-መለኮታዊ አገልግሎቶች ላይ በማሰላሰል ወደ ልዩ የአገልግሎት ራዕይ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"የእምነታችንን ምልክት የሆነውን የክርስቶስ የእውነት እና የፍቅር አገልግሎት ተልዕኮን በመቀበል በሕይወት፣ በአኗኗር እና በቃል አውጁት።" በማለት የሚቀርበው ሥርዓት ከታኅሳስ 23/2014 ዓ. ም. ጀምሮ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዘንድ ከምዕመናን ወገን የሚቀርቡ ወንዶች እና ሴቶች “በጥልቅ እምነት እና ብስለት” ከጳጳሳቸው እጅ የካቴኪስትነት ወይም የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት አገልግሎት ተልዕኮን የሚቀበሉበት ሥርዓት መሆኑ ታውቋል።

ጥንታዊ ሥርዓት ነው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በግል ስልጣናቸው ይህን ጥንታዊ መንፈሳዊ አገልግሎት በይፋ ካቋቋሙ በኋላ  የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን ለመሰየም የሚያግዝ ሥርዓተ አምልኮን የያዘ መጽሐፍ በማጽደቅ እንዲታተም ማድረጋቸው ታውቋል። መጽሐፉ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በተለያዩ የጳጳሳት ጉባኤዎች ተተርጉሞ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤዎች የካቴኪስቶችን ማንነት በማስተዋወቅ እና ሚናቸውን በማብራራት፣ በቂ ስልጠናን እንዲያገኙ በማድረግ እና ምዕመናኑ የአገልግሎቱን ትርጉም እንዲገነዘቡ በመርዳት ከሌሎች የቤተክርስቲያን የአገልግሎቶት ሚናዎች ጋር እንዳይጋጩ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት የአገልግሎት ስያሜ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ወይም ለበዓሉ የተመረጡ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳን ንባባት በሚቀርቡበት ጊዜ ሊከናወን እንደሚችል ለሥርዓቱ የተዘጋጀው መጽሐፍ ይጠቅሳል። ሥርዓቱ ትክክለኛውን አካሄድ በመከተል፣ በእጩነት ለቀረበው ግለሰብ ምክሮችን በመስጠት፣ ከዚያም የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ቡራኬ በመስጠት ቅዱስ መስቀልን በመስጠት የሚፈጸም ይሆናል።

ተጨማሪ ደረጃዎች

የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት ሥርዓት በቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ላይ ጠቅላላ አስተንትኖን በማድረግ ተጨማሪ እርምጃዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ሲሆን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 2/2013 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት የግል ሐዋርያዊ ውሳኔ የቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖናን በማሻሻል ሴቶችም በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱሳት መጽሐፍት በማንበብ እና በመንበረ ታቦት እንዲያገለግል የሚፈቅድ ውሳኔ ግንቦት 2/2013 ዓ. ም. ይፋ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

በቫቲካን የመለኮታዊ አምልኮ ሥርዓት እና የቅዱሳት ምስጢራት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሐላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር ሮች ስለ ሥነ-ሥርዓቱ ማብራሪያ ከሚሰጥ መጽሐፍ ጋር በላኩት መልዕክታቸው፣ አዲሱ ሥርዓት በሌሎች ሥነ-መለኮታዊ አገልግሎቶች ላይ በማሰላሰል ወደ ልዩ የአገልግሎት ራዕይ ለመድረስ የሚያስችል ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። 

የአገልግሎቱ ይዘት

ከሁሉም በላይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር ሮች የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ማብራሪያ በመጥቀስ በላኩት መልዕክት፣ አዲሱ የአገልግሎት ይዘት በየአገራቱ በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስትያናት ውስጥ ቋሚ አገልግሎት የሚቀርብበትን መንገድ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል። ከሁሉም በላይ "በጋራ የጥምቀት ጸጋ ላይ የተመሠረተ የምእመናን የአገልግሎት ዘርፍ" በመሆኑ ከሌሎች ክህነታዊ አገልግሎቶች የተለየ ነው” በማለት አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር ሮች በማከልም “ካቴኪስቶች በጥምቀት በተቀበሉት ጸጋ በቤተክርስቲያን ውስጥ እምነትን እንዲያውጁ እና የስርጭት ኃላፊነትን እንዲወጡ፣ ለክህነት አገልግሎት ከተሾሙት ጋር በመተባበር እና በእነርሱ መሪነት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ የተጠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር ሮች አለ መግባባቶችን ለማስወገድ እንዲቻል “ካቴኪስት” የሚለው ቃል ከቤተ ክርስቲያን አውድ ጋር በተያያዘ የተለያዩ እውነታዎችን እንደሚያመለክት ገልጸው፣ “በሚመደቡበት የተልዕኮ ግዛቶች ውስጥ ያሉ ካቴኪስቶች”፣ በጥንት ዘመን በነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚሠሩት ይለያል” ብለዋል።

ካቴክስትነትን በብዙ ቅርጾቹ መለየት ይችላል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር "ሁለት ዋና መለያዎች አሉት ብለው፣ ትምህርተ ክርስቶስን የማስተማር የተለየ ተግባር ያላቸው ካቴኪስቶች እና በሌሎች የተለያዩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች የሚሳተፉ፣ ለምሳሌ የምዕመናንን ጸሎት መምራት፣ የታመሙትን መርዳት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ማስፈጸም፣ ሌሎች ካቴኪስቶችን ማሰልጠን፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ተነሳሽነቶችን ማስተባበር እና ድሆችን መርዳት የሚሉ ይገኝባቸዋል።

የካቴኪስት አገልግሎት እና ሌሎች የቤተክርስቲያን ሚናዎች

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር በመልዕክታቸው፣ የካቴኪስትነት ጥሪ “ተገቢ ማስተዋል” የሚያስፈልገው እንደሆነ ገልጸው፣ በሐዋርያዊ አገልግሎት የሚተባበሩት ሁሉ በካቴኪስቶች አገልግሎት ውስጥ በመደበኛነት መካተት እንደሌለባቸው ገልጸዋል። የተወሰኑ ክፍሎች በካቴኪስትነት አገልግሎት ባይሰማሩ ይመረጣል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር፣ እነዚህ ክፍሎችም ዲያቆናትን እና ለክህነት የታጩትን፣  ገዳማዊያንን እና ገዳማዊያትን፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት አስተማሪዎችን፣ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎችን እንዲያስተባብሩ ከጳጳስ ሳይሆን ከምዕመናን አደራ የተሰጣቸውን አባላትን የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።

ሕፃናትን እና ጎልማሶች የሚከታተሉትን የበተመለከተ፣ እነሱም ቢሆኑ በልዩ የአገልግሎት ዘርፍ የግድ መግባት አይጠበቅባቸውም ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር፣ ነገር ግን በእያንዳንዱ የትምህርተ ክርስቶስ ትምህርት ዓመት መጀመሪያ ላይ “ይህን አስፈላጊ ተግባር በአደራ” ማግኘት ይኖርባቸዋል ብለው፣ ነገር ግን ይህ ደንብ አንዳንዶች የሐዋርያዊ አገልግሎት ብቃታቸው እና ፍላጎታቸው ታይቶ በቅዱሳት መጽሐፍ ንባባት ወይም በካቴኪስትነት አገልግሎት መሳተፍን አይከልክልም ብለዋል። 

የካቴኪስቶችን ሚናዎች ለይቶ ማወቅ

የካቴኪስቶች የአገልግሎት ሚናቸውን ለይቶ ግልጽ ማድረግ የየአገራቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተግባር መሆኑን የገለጸው የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር መልዕክት፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በተጨማሪም ለእጩዎች ተስማሚ የሆኑ የስልጠና መርሃ ግብሮችን መወሰን እና ምዕመናኖቻቸው የዚህን አገልግሎት ትርጉም በሚገባ እንዲረዱት ለማድረግ መጠራታቸውን ገልጸዋል።

ሕገ ቀኖና፣ አንድ ምእመን “በአንድ ደብር ውስጥ በሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲሳተፍ” አደራ የሚል መሆኑን ብጹዕ አቡነ አርተር ገልጸው፣ ነገር ግን ካቴኪስት በካህን ወይም በዲያቆን ምትክ የሚመደብ አለመሆኑን ምዕመናን እንዲያውቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን የምእመናን ወገን በመሆን ጥምቀታቸውን ፍሬያማ በሆነ መንገድ በመኖር፣  የእረኝነት አገልግሎታቸው ለሁሉም ይደርስ ዘንድ የክኅነት ስልጣን ከተሰጣቸው የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጋር በመተባበር ኃላፊነታቸውን የሚካፈሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።  

“የካቴኪስትነት አገልግሎት ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ክፍት ነው” ያሉት የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር፣ "በጥልቅ እምነት እና በሰብዓዊ ብስለት፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች፣ ሌሎችን ተቀብለው ለማስናገድ ዝግጁ ለሆኑት፣ ለጋስ በመሆን የወንድማማች ሕይወት ለሚኖሩት፣ በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ሥነ-መለኮታዊ ስልጠናዎችን ለወሰዱት እና ቅዱስ ቁርባንን ለተቀበሉ የአገልግሎት ዘርፉ ክፍት መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ በካቴኪስትነት አገልግሎት ለመሳተፍ የሚፈልግ እጩ “በነጻነት የተጻፈ እና የተፈረመ” ማመልከቻ ለጳጳሱ ማቅረብ እንዳለበት በቫቲካን የመለኮታዊ አምልኮ ሥርዓት እና የቅዱሳት ምስጢራት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርተር ሮች በመልዕክታቸው ገልጸዋል።  

14 December 2021, 17:09