ፈልግ

በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የተቀሰቀስው ጦርነት በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የተቀሰቀስው ጦርነት  (ANSA)

ቅድስት መንበር፣ ጦርነት እና የምግብ እጥረት ዓለም አቀፍ ስጋቶች መሆናቸውን አስታወቀች

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ፣ ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አረላኖ፣ በሮም ሰኔ 6/2014 ዓ. ም. በተጀመረው የድርጅቱ 170ኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሰላም እና የውይይት ጥሪን በድጋሚ አስታውሰው፣ በዓለማችን የሚታየው የምግብ ዋስትና ማጣት ቅድስት መንበርን ያሳሰባት መሆኑን ገልጸዋል። የዩክሬን የእህል ምርት ወደ ውጭ አገራት እንዳይላክ እንቅፋት መፈጠሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸው፣ በዓለማች ውስጥ ሁሉም ሰው በቂ ምግብ እንዲኖረው ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ወታደራዊ ጥቃት በአስቸኳይ ለማስቆም ፅኑ ቁርጠኛነቱን እንዲያሳይ የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድን በጉባኤው ላይ ጠይቋል። በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የተቀሰቀስው ጦርነት በዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና እና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ መኖሩን፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ የግብርና ልማት ፈንድ እና የምግብ ፕሮግራም የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ አረላኖ ተናግረዋል። ቋሚ ታዛቢው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ተማጸኖ ጠቅሰው ባሰሙት ንግግር፣ ጦርነት ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ፣ ይህም ጦርነት ከሚያስከትለው ስቃይ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ እና ደም አፋሳሽ የሆነው አሰቃቂ ግድያ እንዲቆም ለማድረግ ዋና መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ሰላም ከምግብ ዋስትና ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳለው የገለጹት ብጹዕ አቡነ አረላኖ፣ ዩክሬን የእህል ምርቷን ወደ ውጭ አገራት እንዳትልክ እንቅፋት መፈጠሩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን እና ይህም በዩክሬን የእርሻ ምርት አቅርቦት ጥገኛ በሆኑት ሀገራት ላይ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ አረላኖ በማከልም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን፣ የሰው ልጅ በቂ የዕለት እንጀራን በልቶ ማደር ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት አካል መሆኑን እና በበርካታ የዓለማችን አካባቢዎች መረጋጋት እንዲገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ግንቦት 24/2014 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸው “ስንዴን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ተገቢ አይደለም” በማለት ያቀረቡትን መልዕክት በማደስ ተናግረዋል

የምግብ ቀውስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ስጋት

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በግጭቶች ምክንያት የሚደርሰውን የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውድመት ለማስቆም መመሥረትቱን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ አረላኖ፣ የምግብ እጥረት ዋነኛ ምክንያቶች ብጥብጥ እና ሕዝባዊ አመጽ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። ስለሆነም ለሁሉም ሰው የሚበቃ የዕለት እንጀራ እንዲኖር እና አሳሳቢ የሆነው የምግብ እጥረት ሁኔታ እንዳይባባስ በቁርጠኝነት ተባብሮ መሥራት እንደሚያፈልግ አሳስበዋል። በአየር ንብረት ለውጥ እና በውሃ እጥረት ክፉኛ በተጠቁት ድሃ አገራት የሚታየው የማዳበሪያ እጥረት፣ የምግብ መጠን መቀነስን ሊያጎላ እንደሚችል፣ ይህም መላውን ሕዝብ ወደ አካባቢ መራቆት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አደጋን ሊመራ እንደሚችል ብጹዕ አቡነ አረላኖ ገልጸዋል። በዓለማችን ውስጥ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች የምግብ ቀውስን ሊያባብሱ እንደሚችሉ እና በምግብ ዋጋ መጨመር ምክንያት በመጭው የአውሮፓዊያኑ 2023 ዓ. ም. ዓለማችንን ከፍተኛ የምግብ እጥረት አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል

የምግብ እና እርሻ ድርጅት ተጨባጭ ተነሳሽነትን ሊያሳይ ይገባል

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት “FAO”፣ ላጋጠሙት ተግዳሮቶች ምላሽ መስጠት እንዳለበት፣ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እና የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ ተነሳሽነቱን ሊያሳይ እንደሚገባ ብጹዕ አቡነ አሬላኖ አሳስበው፣ በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱት ሕዝቦች በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ላይ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። "የብዙ ወንድሞችና እህቶች ስቃይ ሰላምን መልሰን እንድንገነባ፣ እንድናስከብር እና በስጦታ መልክ እንድናቀርብ ግድ ይለናል" ያሉት ብጹዕ አቡነ አሬላኖ፣ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄው በሁሉም ወገን የከፋ ጥፋትን የሚያስከትል የወታደራዊ ኃይል ከመጠቀም ይልቅ፣ ወገናዊ ጥቅምን በመካድ፣ ጥላቻን እና ሞትን በመሻር ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ መተባበር እንደሚያስፈልግ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ የግብርና ልማት ፈንድ እና የምግብ ፕሮግራም የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ አረላኖ ተናግረዋል።

ሮም በሚገኝ ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሰኞ ሰኔ 6/2014 ዓ. ም. የተከፈተው 170ኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ምክር ቤት ጉባኤ፣ ዓርብ ሰኔ 10/2014 ዓ. ም. እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

15 June 2022, 14:35