ፈልግ

ካርዲናን ፓሮሊን፣ ከብሔራዊ የጦርነት አስወጋጅ ተቋም ለቅድስት መንበር የተሰጣትን ሽልማት ሲቀበሉ ካርዲናን ፓሮሊን፣ ከብሔራዊ የጦርነት አስወጋጅ ተቋም ለቅድስት መንበር የተሰጣትን ሽልማት ሲቀበሉ 

ካርዲናን ፓሮሊን፣ በተለያየ ችግር የሚሰቃዩትን ለመርዳት መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በዓለማችን ውስጥ በርካታ ሰዎች በድህነት ሕይወት ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰው፣ ከተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የሚወጡበትን መንገድ በመፈለግ እና የሚቻለውን ዕርዳታ በመለገስ ሁሉ ሰው መተባበር እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህን የተናገሩት፣ ሰኔ 1/2014 ዓ. ም. ቅድስት መንበር “በሕዝቦች መካከል መግባባትን እና ሰላምን ለማስፈን” ላደረገችው የማያቋርጥ አገልግሎት፣ ከጣሊያን ብሔራዊ የጦርነት አስወጋጅ ተቋም የተዘጋጀላትን ዓለም አቀፍ ሽልማት በተቀበሉበት ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ቅድስት መንበር በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቆም በሚደረግ ማንኛውም ጥረት የበኩሏን ድጋፍ የምታደርግ መሆኗን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ለቅድስት መንበር የተሰጣት ዓለም አቀፍ ሽልማቱ ጥረቷን የበለጠ እንድታሳድገው የሚያበረታታት መሆኑን ገልጸው፣ ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ጨምሮ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ዓለም አቀፍ ኅብረትን እንዳታሳድግ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣት የአገልግሎት ድርሻ መሆኑን አስታውቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም፣ ቅድስት መንበር በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታቀርባቸው የተለያዩ ድጋፎች የረዥም ዘመን ልምዷ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ፊትም በቁርጠኝነት አጠናክራው እንደምትጥልበት አረጋግጠዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው፣ አውሮፓን ያጋጠማት ቀውስ በምስራቅ የአውሮፓ አገር ዩክሬን የታየውን የጦርነት አደጋ ብቻ ሳይሆን፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በማስመልከት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮሶ ተደጋጋሚ ጥሪ ማስተላለፋቸውን አስታውሰው፣ ብዙ ገደቦች ቢኖሩትም የሁሉ ሰው ሕጋዊ ደኅንነት፣ መረጋጋት እና ሰላም ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስረድተዋል። የቫቲካን ዲፕሎማሲን በማስመልከት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በየጊዜው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙት ሰዎች ጋር ለመተባበር እና በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች ድጋፍ እና ተስፋ ለመስጠት ቅድስት መንበር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ሰላምን ለማምጣት የሚደረግ ዲፕሎማሲ

በሌሎች አገራት ለደረሰው ቀውስ ምክንያት የሆነውን የዩክሬን ጦርነት ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፣ ግጭቱን ለማስቆም በርካታ ወገኖች የሚያደርጉትን ጥረት አስታውሰው፣ ንጹሐን ሰዎች የሞቱበት፣ ቤት ንብረታቸውን ያጡበት ጦርነት በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል። በዚህ ሁኔታ መካከል የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጥረት ጦርነትን በመቃወም ሰላምን ለመገንባት የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።

በጣሊያን ብሔራዊ የጦርነት አስወጋጅ ተቋም መስራች እና ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሎሬንሶ ፌስቲቺችኒ፣ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የልምድ ልውውጦች ለማድረግ የቆመ ተቋም እንዲዋቀር ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው፣ ተቋሙ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አገልግሎት እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ትኩረትን የሚሰጥ መሆን እንዳለበት  አስረድተዋል። ክቡር አቶ ሎሬንሶ ፌስቲቺኒ፣ የቅድስት መንበር ተግባር የእምነት፣ የጥንካሬ እና የሰላም ቁርጠኝነትን ማሳደግ እንደሆነ ገልጸው፣ በማኅበራዊ ቀውስ ወቅት በሕዝቦች መካከል እርስ በእርስ መከባበር፣ በጋራ መወያየት እና በአደጋ ወቅት የሰው ልጆች በመደጋገፍ አብረው የሚሆኑበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሆነ አስረድተዋል።

በጣሊያን ብሔራዊ የጦርነት አስወጋጅ ተቋም መስራች እና ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ሎሬንሶ ፌስቲቺችኒ፣

በመጨረሻም፣ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ እና በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ በሚገኙ ሕዝቦች ላይ በየቀኑ የሚደርስ የከባድ ጦር መሣሪያዎች ጥቃት እንዲያቆም ጥሪያቸውን አቅርበው፣ የሁሉንም ሰው ሕሊና የሚፈታትን አሳዛኝ ክስተት ተወግዶ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ጥረታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰዎች ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ በአደራ አሳስበዋል።

 

09 June 2022, 16:09