ፈልግ

የሕጻኑ ኢየሱስ የሕጻናት ሕክምና መስጫ ሆስፒታል የሕጻኑ ኢየሱስ የሕጻናት ሕክምና መስጫ ሆስፒታል  

የቫቲካን ሠራተኞች ኅብረታቸውን በስፖርታዊ ተሳትፎ እና በመረዳዳት ገለጹ

የቫቲካን ሠራተኞች የቤተሰብ በዓልን ሰኔ 5/2014 ዓ. ም. በስፖርታዊ ጨዋታዎች እና ትብብራቸውን በመግለጽ አክብረዋል። ዘንድሮ የተከበረው በዓል ዓላማ “ባምቢኖ ጄሱ” በመባል በሚታወቅ የሕጻኑ ኢየሱስ የሕጻናት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የተገነባውን የሕጻናት እንክብካቤ መስጫ ማዕከልን በገንዘብ ለማገዝ ሲሆን፣ የቤተሰብ ትብብር ሆስፒታሉ ለሕጻናት የሚያደርገውን የሕክምና አገልግሎት ለመደገፍ መሠረታዊ እንደሆነ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፒዮስ 11ኛ የስፖርት ማዕከል በተዘጋጀው ስፖርታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ቤተሰቦች፣ በሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የተቋቋመውን አዲሱን የሕፃናት ሕክምና መስጫ ማዕከልን በገንዘብ ለመርዳት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል። እሑድ ሰኔ 5/2014 ዓ. ም. የተዘጋጀውን የቤተሰብ በዓል ያስተባበረው በቫቲካን ሥር የሚገኝ የስፖርት ማኅበር መሆኑ ታውቋል።

ስፖርት ቤተሰብን ያስተባብራል

በእያንዳንዱ የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ የሚቀርበው የስፖርት ዝግጅት ቤተሰቦችን አንድ በማድረግ መረዳዳትን እና ከሁሉም በላይ አብሮነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ታውቋል። ዘንድሮ የተከበረውን የቤተሰብ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ስፖርታዊ ሥነ ሥርዓቱ ለሕጻናት የሕክምና እና የእንክብካቤ አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡ ሦስት ማኅበራትን በማስተባበር፣ አገልግሎታቸውን በቀጣይነት ለማሳደግ ያነሳሳቸው መሆኑ ታውቋል።

የዕለቱ መርሃ ግብር

እሑድ ሰኔ 5/2014 ዓ. ም. በተከበረው የቤተሰብ ስፖርታዊ በዓልን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት የቫቲካን ከተማ ረዳት ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ መሆናቸው ታውቋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት በመቀጠል በሁለት የሕጻናት ሕክምና አገልግሎት እና እንክብካቤ ማኅበራት መካከል የሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያ መካሄዱ ታውቋል። በሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከል ከተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ቀጥሎ ተጋጣሚ ቡድኖችን ጨምሮ በዓመቱ ውስጥ በቫቲካን በተካሄዱ የስፖርት ውድድሮች እና በሌሎች የተለያዩ ተግባራት ላይ ለተሳተፉት በሙሉ የተዘጋጀ የሽልማት ሥነ ሥርዓት መከናወኑ ታውቋል። በመጨረሻም በሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ውስጥ ለተቋቋመው አዲስ የሕጻናት እንክብካቤ መስጫ ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ታውቋል።

የሕፃኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ውክልና

በሥነ ምግባራዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል፣ ሦስት እውነታዎችን እንደ ግብ የተመለከታቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው በሆስፒታሉ ውስጥ በተለያዩ ሞያዎች ተሰማርተው የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ማስተባበር፣ በየቀኑ ለሕጻናት ፍቅርን በመግለጽ የሕክምና እና የእንክብካቤ አገልግሎትን በሚሰጡ የሕክምና ባለሞያዎች መልካም ፈቃድ የወንዶች እና የሴቶች ቡድንን ማደራጀት፣ ሐኪሞች ከሕክምና ሥራቸው በተጨማሪ ለእግር ኳስ ካላቸው ፍቅር በመነሳሳት እና እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ለተመሳሳይ ግብ በሚያደርጉት ጥረት አማካይነት ሕጻናት ሕሙማንን ለመርዳት መሆኑ ታውቋል።

ለጋሽ ድርጅቶች ተመስግነዋል

የሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ፋውንዴሽን ጠቅላይ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ አቫሎኔ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ የሚሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ ዘንድሮ በመጋቢት ወር ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የፓሊዶሮ የሕጻናት ሕክምና መስጫ ማዕከልን ለመርዳት መሆኑን ገልጸዋል። በማዕከሉ ውስጥ የሚያስፈልጉ አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎችን ዝግጁ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸ የገለጹት ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ አቫሎኔ እስካሁን 70 ከመቶ የሚሆን የገንዘብ ወጭ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ቀጥለውም የአልጋዎችን ቁጥር ለመጨመር እና የመኪና ማቆሚያ ቦታን ለማሻሻል ዕቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።

በቤተሰቦች መካከል የሚታይ መረዳዳት

የሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ፋውንዴሽን ጠቅላይ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ አቫሎኔ በማከልም፣ በየዓመቱ የሚከበረው የቤተሰብ በዓሉ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን የሚረዱ ሌሎች ቤተሰቦችን ለማግኘት ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል። አብሮነት አስፈላጊ እና ቤተሰቦችም በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመርዳት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ይኖርባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ አቫሎኔ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ የሚደረግ የገንዘብ ዕርዳታ ወላጆች ለታማሚ ልጆቻቸው የሚያደርጉትን ክትትል ለማገዝ እንደሚረዳቸው፣ ከዚህም በተጨማሪ በወላጅ ቤተሰብ መካከል መረጋጋትን ለማስፈን የሚረዳቸው መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉም ነገር ከስፖርታዊ ባሕል ጋር የተጣመረ ከሆነ የበለጠ ደስታን እና ሕይወትን እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

የወንድማማችነትን መንፈስ እናሳድግ

በቫቲካን ሥር የሚገኘው የስፖርት ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ ዶሜኒኩ ሩጄሮ በዕለቱ ባቀረቡት ዜማ፣ የቫቲካን ሠራተኞች የእግር ኳስ ቡድን ከሃምሳ ዓመት በፊት ሲመሰረት ውና ዓላማው ሠራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን በስፖርት ማሰባሰብ እንደሆነ አስታውሰው፣ በእያንዳንዱ የውድድር ሥነ ሥርዓት መጨረሻ ላይ የበጎ አድራጎት ተነሳሽነቶችን በመግለጽ ዓመታዊ የቤሰብ በዓሉን እንደሚያከብሩት አስረድተዋል። ዘንድሮ በተዘጋጀው ስፖርታዊ የቤተሰብ በዓል በኩል ከቅድስት መንበር አስተዳደራዊ መዋቅር እና ከተነሳሽነታቸው ጋር ግንኙነት ያለውን የሕፃኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ፋውንዴሽን ለመርዳት መፈለጋቸውን አቶ ዶሜኒኩ ሩጄሮ ገልጸዋል። የቫቲካን ሠራተኞች ቤተሰቦችም በቫቲካን ሥር ከሚገኝ የስፖርት ማኅበር እንቅስቃሴዎች ጋር በመተባበር ብዙውን ጊዜ የወላጆቹ ተነሳሽነት የሚገለጸው በወንድ እና በሴት ስፖርተኞች በኩል እንደሆነ እና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በመዞር የወንድማማችነትን መንፈስ ወደ ሁሉም የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያደርሱ መሆኑን አስረድተዋል።

13 June 2022, 16:57