ፈልግ

ዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ 'ዓለም አቀፍ ክስተት ነው፣ ቤተክርስቲያን አንድ ትልቅ ቤተሰብ መሆኗን ማረጋገጥ ተችሏል መባሉ ተገለጸ።

ከዓለም የቤተሰብ ስብሰባ በኋላ የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምክትል ጸሐፊ ዶ/ር ጋብሪኤላ ጋምቢኖ ከሰኔ 15 እስከ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም የተካሄደው አስረኛው የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ላይ ስለታዩት ስኬቶች በተለይም ዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን እንዴት አንድ ትልቅ ቤተሰብ እንደሆነች ማሳየት ተችሏል ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የምእመናን፣ ቤተሰብ እና ሕይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ በቪዲዮ የተደገፈ አንድ ዝግጅት ያፋ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ይህም ከሰኔ 15 እስከ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም በሮም ከተማ የተካሄደውን 10ኛው የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ አጠቃላይ ይዘት የሚገልጽ እንደ ነበረም ተገልጿል።

ዝግጅቱ በሮም ብቻ ሳይሆን በአህጉረ ስብከቶቻቸው እና በቤታቸው የተሳተፉትን የአለም ቤተሰቦች ሁሉ ያሳተፈ የሕበረት ወቅት ነበር ሲሉ በቫቲካን የምእመናን፣ የሕይወት እና የቤተሰብ ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምክትል ጸሐፊ ጋብሪኤላ ጋምቢኖ ተናግረዋል።

በቪዲዮው ዙሪያ ከቫቲካን ዜና ጋዜጠኛ ጋብሪኤላ ሴራሶ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ጋምቢኖ ዓለም አቀፉ ተሳትፎ የአንድነት ቤተ ክርስቲያን መልእክት እንዴት የበለጠ ትኩረት እንዳደረገ ገልጸው፣ ቤተሰቡም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለቤተሰብ የሰጡትን ኃላፊነት በመጥቀስ በዓለም ውስጥ ሚስዮናውያን የመሆን ተልእኮ እንደ ተሰጠው አክለው ገለጸዋል።

ዓለም አቀፋዊ አንድነት

ስብሰባው "ልዩ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተሞክሮ የታየበት" ነው ሲሉ ስለ ስብሰባው የገለጹት ዶ/ር ጋቢኖ ዝግጅቱ በመላው አለም የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን፣ አድባራትን እና ማህበረሰቦችን በእውነት ማሳተፍ መቻሉን ገልጸው ልምዳቸውን በሮም ከተካሄደው ስብሰባ ጋር ሙሉ በሙሉ የተቆራኘ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አክለው ገልጸዋል። ይህ ደግሞ እያንዳንዱን የበዓሉ ጭብጦች በማጉላት “ቤተሰብ መሆን” የሚለውን ሃሳብ እንዲጨምር ማደረጉንም ተናግረዋል።

ይህ ፌስቲቫል እንዳሳየን "በእውነቱ ከቤተሰብ እና ከቤተክርስቲያን እረኞች ጋር የተዋቀረች አንድነቷ የተጠበቀ ቤተክርስትያን የሆነች፣ የትብብር ሀላፊነትን እና ሕበረትን በእውነት በተግባር አይተናል። ይህ ደግሞ ለማጉላት በጣም አስፈላጊ ገጽታ ይመስለኛል" ሲል ጋምቢኖ ተናግረዋል።

የፍቅር ሐሴት

በመቀጠልም ፌስቲቫሉ በላቲን ቋንቋ አሞሪስ ላቲሲያ (የፍቅር ሐሴት) የተሰኘው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐዋርያዊ መልእክት የሚዘከርበት አመት ማብቃቱን አስታውሰው ይህም “ምንም ጥርጥር የለውም ሂደቶችን የከፈተ እና በዓለም ዙሪያ ትንሽ አስገራሚ ውጤቶችን የሰጠ መንገድ ነው” በማለት አክለው ተናግረዋል።

ጉዞው በእውነት መጀመሩን እና አሁን "በአንድነት መቀጠል እንዳለበት ገልጸው እንዲሁም ቅዱስ አባታችን በአለም የቤተሰብ ስብሰባ ወቅት የነገሩንንና በተለይም ቤተሰብ በዓለም ውስጥ ሚስዮናዊ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ድርሻ ነው’ ብለዋል።

መስቀል እያንዳንዱን ቤተሰብ ይወክላል

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቅዳሜ ሰኔ 18/2014 ዓ.ም በተካሄደው የቤተሰብ ስብሰባ መዝጊያ ቅዳሴ ላይ ሁሉም ቤተሰቦች በነፃነት እንዲኖሩ፣ ወላጆች በልጆቻቸው እንዲታመኑ፣ ባሎችና ሚስቶች በትዳር ጓደኛቸው ጥሪያቸውን እንዲያሳዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰው ጉዞው በስብሰባው መጀመሩን አክለው ገልጸዋል።

ዶ/ር ጋምቢኖ ይህ ምኞት "በጣም አስፈላጊ እና ተምሳሌታዊ ምልክት ሲሆን ይህም በቅዳሴው ላይ ለተገኙት የጳጳሳት ጉባኤ ተወካዮች እና የንቅናቄዎች ልዑካን ቤተሰቦች መስቀሎችን ማስረከብ ነበር" በማለት አስታውሰዋል። ዛሬ ልዑካኑ ወደ ቤታቸው የወሰዷቸው የዓለም ቤተሰቦች፣ ለዚህ ​​የተሰጣቸውን አደራ ትንሽ ለማሰብ ጊዜ ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ቤተሰቦች ቤተ ክርስቲያን ናቸው ሲሉ ዶ/ር ጋምቢኖ ንግግራቸውን የቀጠሉ ሲሆን በእዚህ ምክንያት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን "ለምሳሌ የጋብቻን ውበት እና ቤተሰብን ከልጆች፣ ወጣቶች ጋር በማወጅ ጋብቻን እና የቤተሰብን ሕይወት መመኘት እንዲማሩ ጠርቷቸዋል" ይህ ደግሞ በዚህ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተከናውኗል ብለዋል።

"በመጨረሻ ይህ ስብሰባ የቤተሰብን ብልጽግና እና ውበት ለመካፈል ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ማሳያ ነበር" ሲሉ ዶ/ር ጋምቢኖ ተናግረዋል።

በኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ የቤተሰብ መሰብሰብ

በመጨረሻም ዶ/ር ጋምቢኖ እ.አ.አ በ2025 የኢዮቤልዩ ዓመት አውድ ውስጥ የሚካሄደውን ቀጣዩን የቤተሰብ ስብሰባ በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን "በኢዮቤልዩ ውስጥ ስብሰባ ይሆናል፣ ነገር ግን አሁንም አስፈላጊ ቀጠሮ ይሆናል ምክንያቱም እንደገና ለመገናኘት እርስ በርስ ለመደማመጥ እና ከሁሉም በላይ አንድ ላይ ለመጸለይ እድል ይሆናል" ማለታቸው ተገልጿል።

01 July 2022, 14:42