ፈልግ

እህት ሐና ሮዝ፣ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ፊት ተንበርክከው ሲማጸኑ እህት ሐና ሮዝ፣ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ፊት ተንበርክከው ሲማጸኑ 

የሚያንማር መነኩሴ ከታሊባን የጥቃት ዒላማዎች መካከል አንዷ እንደነበሩ ተገለጸ

ቢቢሲ የዜና አገልግሎት እ. አ. አ 2021 ይፋ ካደረጓቸው “100 ሴቶች” መካከል ግማሾቹ የታሊባን አሸባሪ ቡድን የጥቃት ዒላማ ያደረጓቸው የአፍጋኒስታን ዜጎች መሆናቸው ታውቋል። ከእነዚህ መካከል አንዷ በሚያንማር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኩሴ፣ እህት ሐና ሮዝ ኑ ታውንግ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቢቢሲ የዜና አገልግሎት “እ. አ. አ 2021 በዓለም ዙሪያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ 100 ሴቶች” በማለት ይፋ ባደረገው የስም ዝርዝር ውስጥ የሚያንማር ካቶሊካዊ መነኩሴ እህት ሐና ሮዝ ኑ ታውንግን ያካተተ ሲሆን፣ በቺን ግዛት ውስጥ የሚኖሩት እህት ሐና ሮዝ ኑ ታውንግ፣ እ. አ. አ የካቲት 28/2021 እርሳቸው በሚያገለግሉበት ክሊኒክ ውስጥ በተጠለሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጸጥታ ሃይሉ ጥቃት እንዳያደርስ በማለት ተንበርክከው በመማጸናቸው የሚገርም ድፍረት ማሳየታቸው ይታወሳል።

የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪዬር ደናግል ማኅበር አባል የሆኑት እህት ሐና ሮዝ፣ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች የተንበረከኩበትን ሥፍራውን እንዲለቁ ቢታዘዙም ሞትን በመምረጥ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚፈጸም የግድያ ተግባር እንዲቆም መማጸናቸው ይታወሳል። እህት ሐና ሮዝ በጸጥታ አስከባሪዎች ፊት ተንበርክከው ሲማጸኗቸው የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ቢቢሲን ጨምሮ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት በሰፊው ሲሰራጭ መቆየቱ ይታወሳል።

ትንሽ ድርጊት ቢሆንም ትልቅ ፍቅር የታየበት ነው

“ይህን እንዳደርግ መንፈስ ቅዱስ ብርታትን ሰጥቶኛል፣ ባርኮኛልም” ያሉት እህት ሐና ሮዝ፣ በዚያን ወቅት ሞት የሚጠብቃቸው ወጣቶች ማምለጫ ጊዜን እንዲያገኙ እና በእነርሱ ምትክ ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጸዋል። እህት ሐና ሮዝ የፈጸሙት ድርጊት ትንሽ ቢመስልም ትልቁ ፍቅር የተገለጸበት፣ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በመማረክ እውቅናን ያስገኛቸው መሆኑ ሲነገር፣ “በሚያንማር ያለውን ሁኔታ ዓለም እንዲያውቀው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል” ሲሉ እህት ሐና ሮዝ ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምላሽ

የእህት ሐና ሮዝ ተግባር ከገረማቸው፣ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የዓለም ሰዎች መካከል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አንዱ ሲሆኑ፣ በወቅቱ ባሰሙት መልዕክትም “እኔም በሚያንማር ጎዳናዎች ተንበርክኬ በንጹሃን ላይ የምትፈጽሙትን ግፍ አቁሙ!” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል። በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት መጽናናትን ያገኙት እህት ሐና ሮዝ፣ ፊደስ ለተሰኘ የቫቲካን ዜና ወኪል በሰጡት አስተያየት፣ በቅዱስነታቸው መልዕክት መደነቃቸውን ገልጸው፣ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ፊት ተምበርክኬ ያቀረብኩት ተማጽኖ ሰብዓዊነት በልቡ ያለው ክርስቲያን ሁሉ ተግባር ነው” በማለት አስረድተዋል።

የብጹዕ ካርዲናል ቦ ምላሽ

የሚያንማር ታዋቂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሻርል ቦ ያንጎን በበኩላቸው በእህት ሐና ሮዝ ምስክርነት ልባቸው ተነክቶ እንደነበር ይታወሳል። “በክፉ መንፈስ ፊት የታየውን ታላቅ የመስዋዕትነት ምስክርነት የዓለም ሕዝብ በአድናቆት ተመልክቶታል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሻርል፣ እ. አ. አ በመጋቢት ወር 2021 በተከበረው የመለኮታዊ ምሕረት ዓመታዊ በዓል ላይ ባሰሙት ስብከት፣ የእህት ሐና ሮዝ የፍቅር ምስክርነት ብዙዎች ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እንዲያደንቁ ያነሳሳቸው መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ የአፍጋኒስታን ሴቶችን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ

ከ100 ሴቶች መካከል ግማሾቹ የታሊባን አሸባሪ ቡድን የጥቃት ዒላማ የሆኑት የአፍጋኒስታን ዜጎች መሆናቸውን ያስታወቀው የቢቢሲ የዜና አገልግሎት በዘገባው፣ “100 ሴቶች” የሚለውን ዓመታዊ ዝግጅት፥ አፍጋኒስታን፣ ባሕል እና ትምህርት፣ መዝናኛ እና ስፖርት፣ ፖለቲካ እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች፣ ሳይንስ እና ጤና በሚሉ አምስት የተለያዩ ዘርፎች መመደቡ ታውቋል። ዘንድሮ ከተመረጡት መቶ ሴቶች መካከል የአፍጋኒስታን ሴቶች ግማሽ መሆናቸውን የገለጸው የዜና አገልግሎቱ፣ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ለደህንነታቸው ሲባል ያለ ስም እና ያለ ፎቶግራፍ መጠቀሳቸውን ገልጿል። እ. አ. አ. ከነሐሴ ወር 2021 ጀምሮ የታሊባን ታጣቂዎች እንደገና በማንሰራራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአፍጋኒስታን ሴቶች ሕይወት በመቀየር፣ ልጃገረዶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዳይማሩ፣ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲፈርስ በማድረግ ሴቶች በብዙ አጋጣሚዎች ወደ ሥራ እንዳይመለሱ ማገዱን የዜና አገልግሎቱ አስታውቋል። ከእነዚህ ሴቶች መካከል ዶክተሮች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሶች፣ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች፣ ተዋናዮች፣ መምህራን፣ የሕዋ ተመራማሪዎች፣ የቤተ መጽሐፍት ባለሙያዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የማኅበራዊ መገናኛ ባለሞያዎች እና የሕግ አማካሪዎች እንደሚገኙበት ገልጿል።

"100 ሴቶች" የተሰኘ ዕቅድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች የተጫወቷቸውን ሚናዎች የሚመረምር ባለ ብዙ ዘርፍ ተከታታይ ዓመታዊ የቢቢሲ ዝግጅት ሲሆን፣ የተቋቋመውም በሕንድ ዋና ከተማ ዴሊ እ. አ. አ. በ 2013 በአንዲት ሴት ላይ የተፈጸመውን አስነዋሪ የቡድን አስገድዶ መድፈር እና ግድያን ተከትሎ መሆኑ ታውቋል። "100 ሴቶች" የተሰኘ ዓመታዊ ዝግጅት የቢቢሲ ዜና አገልግሎት ባለስልጣናት እና ጋዜጠኞች፣ ሴቶችን የሚያጋጥሟቸው አብዛኞቹ ጉዳዮች ጥልቅ ሽፋንን ያላገኙ በመሆናቸው የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥባቸው በማለት የጀመሩት ተከታታይ ዝግጅት መሆኑ ታውቋል።

13 December 2021, 20:16