ፈልግ

የማዘር ተሬዛ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል በሕንድ ውስጥ በአገልግሎት ላይ የማዘር ተሬዛ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል በሕንድ ውስጥ በአገልግሎት ላይ  (AFP or licensors)

የሕንድ መንግሥት የውጭ አገራት ዕርዳታዎች ወደ አገሩ እንዲገቡ መፍቀዱ ተገለጸ

የሕንድ መንግሥት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሕንድ የሚገኙ የማዘር ተሬዛ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል በአገሩ የሚገኙ ችግረኞችን ለመርዳት ከውጭ አገራት የሚያገኙትን ዕርዳታ መፍቀዱን አስታወቀ። የሕንድ መንግሥት፣ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል ዕርዳታውን ከውጭ አገራት ተቀብለው ለችግረኛው ማኅበረሰብ ማድረስ እንዲችሉ ፍቃድ መልሶ በመስጠት፣ ደናግሉ የዕርዳታ አገልግሎታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እ. አ. አ. ታኅሳስ 27/2021 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫው የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል ያቀረቡት የሥራ ፍቃድ እድሳት ጥያቄ ተቀባይነትን ሳያገኝ መቆየቱን ሚኒስትሯ ወ/ሮ አሚት ሻህ ገልጸዋል።

እ. አ. አ. በ1976 ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው የውጭ ዕርዳታዎች መቆጣጠሪያ ደንብ በሕንድ ሉዓላዊነት ፣ ታማኝነት እና የውስጥ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ወይም በማንኛውም የውጭ ሀገር የወዳጅነት ግንኙነት ላይ ተጽዕኖን እንዳያሳድር እና የጋራ ስምምነቶችን እንዳያደናቅፉ ያሚያረጋግጥ መሆኑ ታውቋል። መቆጣጠሪያ ደንቡ በሁሉም የዕርዳታ ማስተባበሪያዎች ዘንድ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ የዕርዳታ አገልግሎት ደንቡ ከውጭ አገራት የሚገኙ ልገሳዎች ለማኅበራዊ፣ ለትምህርት፣ ለሐይማኖት ማስፋፊያ፣ ለኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ አገልግሎቶች እንዲውል በማለት እ. አ. አ በ2010 እና በ2015 ዓ. ም. በድጋሚ ተሻሽሎ መቅረቡ ይታወሳል። የዕርዳታ ማስተባበሪያ ማኅበራትም ከሚመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚቀበሉት የሥራ ፍቃድ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደንቦችን የሚያከብር ከሆነ በየአምስት ዓመታት የሚታደስ መሆኑ ታውቋል። የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል የፍቃድ እድሳትም የእንግሊዝ መንግሥት ፓርላማ በሕንድ አገር ለሚገኙ መንግሥታዊ ላልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች በሚደረግ የዕርዳታ አቅርቦት ውሳኔ የሚመሠረት መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሠረት የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫው በሕንድ የሚገኙ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል በአገሪቱ ውስጥ የዕርዳታ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ ፍቃድ ከታደሰላቸው 16,908 መንግሥታዊ ያልሆኑ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆኑን አስታውቋል።          

የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል ደስታ

በሕንድ የቸርነት ሥራ ማኅበር ደናግል ቃል አቀባይ ወ/ሮ ሱኒታ ኩማር በመልዕክታቸው፣ የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበለትን የፍቃድ እድሳት ጥያቄ ተቀብሎ በጎ ምላሽ በመስጠቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የዕርዳታ አገልግሎት ጥያቄያቸው ይታገዳል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው የገለጹት የማኅበሩ ቃል አቀባዩዋ፣ ጥያቄያቸው ሳይዘገይ በጎ ምላሽ በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

“የድሆች ቅድስት”

የቸርነት ሥራ ማኅበር መሥራች የሆነችው ማዜር ተሬዛ ከአልባኒያዊ ወላጆቻቸው እ. አ. አ ነሐሴ 26/1910 ዓ. ም. በዛሬይቱ መቄዶኒያ ግዛት የተወለደች ሲሆን እ. አ. አ በ1929 ዓ. ም. በ18 ዓመት ዕድሜዋ በሕንድ ውስጥ ወደ ካልካታ ግዛት በመምጣት፣ ከአይርላንድ ከመጡ የሎሬቶ ማኅበር ደናግል ጋር ስትኖር ቆይታ እ. አ. አ በ1931 ዓ. ም. የማኅበሩ አባል መሆኗ ይታወሳል። በኋላም ከእግዚአብሔር ዘንድ ባገኘችው ልዩ ጥሪ መሠረት እ. አ. አ በ1950 ዓ. ም. የቸርነት ሥራ ደናግል ማኅበር መመሥረቷ ያታወሳል። በዚህ የቸርነት ሥራ ማኅበር አማካይነት በሕንድ አገር እና በሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች በመገኘት ለድሆች ባሳየችው ገደብ በለሽ የፍቅር እና የምሕረት አገልግሎት እ. አ. አ በ1979 ዓ. ም. የተሰጣትን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ምስጋናዎችን መቀበሏ ይታወሳል።

ማዘር ተሬዛ በሕንድ ካልካታ ግዛት እ. አ. አ መስከረም 5/1997 ዓ. ም. በ87 ዓመት ዕድሜዋ ያረፈች ሲሆን፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቫቲካን እ. አ. አ ጥቅምት 19/2003 ዓ. ም. በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ብጽዕናዋን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ቆይቶም እ. አ. አ መስከረም 4/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅድስናዋ በይፋ መታወጁ ይታወሳል።        

12 January 2022, 14:31