ፈልግ

በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ የረሃብ አደጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ የረሃብ አደጋ 

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት በተበከሉ ምግቦች ለበሽታ እንደሚጋለጡ ተነገረ

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ያልተበከሉ ጤናማ ምግቦችን ለተመጋቢው ማቅረብን ማረጋገጥ እንዳለበት፣ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ሰኔ 1/2014 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ዘገባው አስታውቋል። ድርጅቱ ከዚህ ጋር በማያያዝ በድህነት እና በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ጤናማ ባልሆኑ ምግቦች ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች እየተጎዱ መሆናቸውን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም ጤና ድርጅቱ አጥብቆ የሚናገረው የምግብ ደህንነት የሚያተኩረው በደንብ ባልተጠበቁ ምግቦች ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያን ከሚስከትሉ በሽታዎች ተመጋቢውን ለመከላከል ያለመ መሆኑን ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምግብ ማይክሮባዮሎጂ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፒዬር ሳንድሮ ኮኮንቼሊ አብራርተዋል።

ደኅንነታቸው ባልተጠበቁ ምግቦች አማካይነት ሊከሰቱ የሚችሉ ከ200 በላይ በሽታዎች መኖራቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ፒዬር ሳንድሮ፣ ከተበከለ ምግብ የሚመጡ የተለመዱ በሽታዎች ከመርዛማ ተህዋሲያን ወይም ባክቴሪያዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አስረድተው፣ ይህ የሚከሰተው ባደጉት የዓለም ክፍሎች ሳይሆን ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት መሆኑን ገልጸዋል።

ረቂቅ ተሕዋስያን የበሽታው ዋነኛ መንስኤዎች እንደሆኑ የገለጹት ፕሮፌሰር ፒዬር ሳንድሮ፣ በሽታን የሚያስከትሉ የተለያዩ መርዞችም መኖራቸውን ጠቁመው፣ ሁለቱም የበሽታው መንስኤዎች በተፈጥሮ እና  በተሳሳተ የማከማቻ ዘዴ ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን አስረድተዋል። የተመረዙ እህሎች የጉበት ነቀርሳን እና የሰውነት እብጠቶችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል። ብዙውን ጊዜ ኬሚካሎች ሆን ተብሎ በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ እንደሚጨመሩ የገለጹት ፕሮፌሰር ፒዬር ሳንድሮ፣ ከመከር ወደ ማዕድ የሚሸጋገሩ በሽታ አምጭ መርዞች በፀረ-ተባይ መድሃኒቶች ወይም በፕላስቲክ ውስጥ የሚካተቱ ውህዶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ፕሮፌሰሩ አክለውም በቅርብ ጊዜ በምርመራ እንደተረጋገጠው፣ በፕላስቲክ ላይ የሚጨመሩ ብዙ ዓይነት ተሕዋሲያን፣ ሻጋታዎችን ወይም ቫይረሶችን የሚፈጥሩ አንዳንድ ንጥረ ነገሮችን የሚመለከት ሲሆን፣ በተጠቃሚው ላይ አደገኛ የሆኑ በሽታዎችን መፍጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ

በየዓመቱ ከአሥር ሰው መካከል አንዱ በምግብ ወለድ በሽታ እንደሚጠቃ የዓለም ጤና ድርጅት በመረጃው ገልጿል። ይህም ማለት በዓመት 600 ሺህ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃው አስረድቷል። ይህ አሃዝ በጂኦግራፊያዊ አቀማመት ደረጃ አንድ ወጥ ምስል የለውም” በማለት የገለጹት ፒየር ሳንድሮ፣ በግልጽ ለማየት እንደተቻለው ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች ስንመለከት እንደ አውሮፓ እና ሌሎች በምግብ ወለድ በሽታዎች እምብዛም የማይጠቁት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። የመበከል አደጋን ለመቀነስ እስከ አሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ውጤታማ እንዳልሆኑ እና ተጨማሪ አዳዲስ አደጋዎች እየተከሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ድሃ የሆኑ የዓለማችን አካባቢዎች መኖራቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ፕዬር ሳንድሮ፣ በንጽህና አጠባበቅ ውስንነት የተነሳ የሽታው መስፋፋት በተመጋቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአደጋ የተጋለጡት ሕጻናት እና አረጋውያን ናቸው

ለአደጋው የሚጋለጡትን በዕድሜ ለይተው የተመለከቱት ፕሮፌሰር ፕዬር ሳንድሮ፣ ሁሉም ተመጋቢዎች በተመሳሳይ መልክ ለአደጋ እንደማይጋለጡ አስረድተው፣ ለበሽታው ይበልጥ የሚጋለጡት ዕድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እና አዛውንቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። ሕጻናት እና አዛውንቶች በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ የዕድሜ ውስጥ ከሚገኙት የበለጠ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት "FAO” እና የዓለም ጤና ድርጅት የተለያዩ ዘዴዎችን ዘርግተው፣ በሁሉም አካባቢዎች፣ እንስሳትን ከማርባት ጀምሮ እስከ መመገብ ድረስ ያለውን ሂደት በማጥናት ላይ መሆናቸው ገልጸዋል።

እነዚህ ቁጥጥሮች ምንም እንኳን በግልጽ ከባድ እና አስከፊ ውጤቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች ቢኖሯቸውም፣ ማመሳከሪያው ከሁሉም በላይ በእህል ገበያ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በዩክሬን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ሕዝቦች በተበከለ ምግብ ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች ይበልጥ የተጋለጡ እና በበሽታው የመያዝ ዕድሉ ሁልጊዜ ከፍተኛ መሆኑን፣ በጣሊያን የቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ማይክሮባዮሎጂ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፒዬር ሳንድሮ ኮኮንቼሊ አብራርተዋል።

09 June 2022, 16:25