ፈልግ

450 ስደተኞች በጀልባ ተሳፍረው ወደ ፖዛሎ ወደብ ሲደርሱ 450 ስደተኞች በጀልባ ተሳፍረው ወደ ፖዛሎ ወደብ ሲደርሱ   (ANSA)

አዳዲስ ስደተኞች ወደ ደቡብ ጣሊያን ወደቦች መድረሳቸው ተነገረ

በደቡብ ጣሊያን ከተማ በሆኑት የላምፔዱዛ እና ፖዛሎ ወደቦች ለሚደርሱት የሜዲትራኒያን ባሕር ስደተኞች የነፍስ አድን ዕርዳታ እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል። የሜዲትራኒያን ባሕር አቋርጠው ወደ ሲሲሊ ደሴት ለሚደርሱ ስደተኞች የዕርዳታ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል። “ኦሽን ቫይኪንግ” በተባለው የነፍስ አድን መርከብ ተሳፍረው ወደ ላምፔዱስ ወደብ ደርሰው ከነበሩ 294 ስደተኞች በተጨማሪ 85 ስደተኞች አውሮራ በተባለች ሌላ መርከብ ተሳፍረው ግንቦት 22/2014 ዓ. ም. ወደ ጣሊያን የወደብ ከተማ መድረሳቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመጡበት መርከብ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

85 ስደተኞችን አሳፍራ በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ ጣሊያን የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ላምፔዱስ የደረሰች አንድ የነፍስ አድን መርከብ ወደ ጣሊያን ክልል እንድትገባ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ፈቃድ ማግኘቷ ታውቋል። በመከቢቱ የነበሩት ስደተኞች በሙሉ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል። ስደተኞቹ አስፈላጊው የጤና ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ከ600 በላይ ሌሎች ስደተኞች ወደ ተጠለሉበት የስደተኞች መኖሪያ መወሰዳቸው ታውቋል። ወደ ደቡብ ጣሊያን ሲሲሊ ደሴት የደረሱት የመጨረሻዎቹ ስደተኞች ያለፈው እሑድ ምሽት የነፍስ አድን ዕርዳታ ተደርጎላቸው ወደ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ መደረጉ ታውቋል። ማክሰኞ ምሽት፣ ከደሴቲቱ በስተደቡብ 30 ማይል ርቀት ላይ 12 ሜትር ርዝመት ባለው ጀልባ ላይ የተሳፈሩ 120 ስደተኞችን የጸጥታ አስከባሪ ኃይል ተቀብሎ ማስተናገዱ ታውቋል።

በፖዛሎ ወደብ ለ294 ስደተኞች አቀባበል ተደርጎላቸዋል

“ኦሽን ቫይኪንግ” በተባለች ነፍስ አድን ዕርዳታ ሰጭ መርከብ ውስጥ ላይ ለአስር ቀናት የቆዩት 294 ስደተኞች ፖዛሎ ወደተባለ የጣሊያን የወደብ ከተማ የደረሱ ሲሆን፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠላቸው በኋላ አምስቱ በደረሰባቸው አደጋ ቆስለው ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል። ሌሎች አራት ስደተኛ እርጉዝ ሴቶችም ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል። የጣሊያን ባለስልጣናት ያለፈው እሑድ ምሽት የወደቦቹን አስተማማኝነት ባረጋገጡ በነጋታው ወደ ፖዛሎ ወደብ ስደተኞች መድረሳቸው ሲነገር፣ ለስደተኞቹ የመጀመሪያ ሰብዓዊ ዕርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ አማቱና ገልጸው፣ ሕይወትን ከሞት ማዳን ሁልጊዜ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባ ሥነ-ምግባራዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸው፣ የስደትን ችግር መጋፈጥ የጣሊያን መንግሥት እና የአውሮፓ አገራት ሃላፊነት መሆኑን በአስተያየታቸው አስረድተዋል።

  በፈረንጆቹ 2022፣ ከ18,000 በላይ ስደተኞች ወደ ጣሊያን ገብተዋል

የጣሊያን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሉቺያና ላሞርጌሰ፣ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ደጋግመው እንደተናገሩት፣ በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት በአፍሪካ አህጉር ላይ ስላስከተለው ጭንቀት፣ በተለይም እንደ ቱኒዚያ እና ግብፅ ያሉ አገሮች በአብዛኛው የሚመኩት ከውጭ በሚያስገቡት እህል እንደሆነ እና ከዩክሬን የሚመጣላቸው እህል፣ የምግብ አቅርቦት ፍላጎታቸውን እንደሚሸፍን ገልጸዋል። እህል ከዩክሬን እንዳይወጣ የወደቦች መዘጋት ቀድሞውኑ የነበረውን የእህል እጥረት እንዳባባሰው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸው፣ ለዚህም ማሳያው ከቅርብ ቀናት ወዲህ የታየው የስደተኞች ፍሰት መሆኑን ከገለጹ በኋላ ይህን ሰብዓዊ ቀውስ ለማስወገድ የአውሮፓ ሚና ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኳራንቲን መርከቦች አገልግሎት ላይ የአንድ ቀን ማቆሚያ

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተደነገገው የስደተኞች መርከብ ላይ ለይቶ ማቆያ ደንብ ሊነሳ መቃረቡ ታውቋል። ሞቃታማ በሆኑት ጊዜያት አገልግሎታቸውን ሲሰጡ የቆዩ አምስት መርከቦች እንደነበሩ ሲነገር፣ በአሁኑ ጊዜ ሁለት መርከቦች ብቻ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳሉ ታውቋል። ይህም በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያ ተልእኳቸው አጠናቅቀው ቱሪስቶችን በማጓጓዝ አገልግሎት ላይ እንደሚሰማሩ ታውቋል። በጣሊያን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል በውቀጣ ትእዛዝ መሠረት፣ በመርከቦች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የተደነገገው የለይቶ ማቆያ ሥፍራ ደንብ ከግንቦት 23/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደማይሆን ታውቋል። ይህ ማለት በነፍስ አድን መርከቦች በኩል ወደ ላምፔዱሳ እና ፖዛሎ የሚደርሱት ስደተኞች በሞቃታማው የበጋ ወቅት የጤና እንክብካቤ አገልግሎትን በየብስ እንደሚያገኙ ታውቋል።

02 June 2022, 16:43