የቤተሰብ አንድነት፣ ድጋፍ፣ ፍቅር ልጆች እና ወላጆች የእእናት እና የአባት ጥምረትን የሚያሳይ ምስል የቤተሰብ አንድነት፣ ድጋፍ፣ ፍቅር ልጆች እና ወላጆች የእእናት እና የአባት ጥምረትን የሚያሳይ ምስል 

በጋብቻ ውስጥ ፍቅር አስፈላጊነት

ስለ ፍቅር ጭምር  ካልተናገርን፣ እስካሁን የተነገረው ነገር ሁሉ የጋብቻንና የቤተሰብን ወንጌል ለመግለጽ በቂ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም፣ እድገትን ሳናበረታታ፣ የጋብቻና የቤተሰብ ፍቅርን ሳናጠነክርና ሳናዳብር የታማኝነትና እርስ በርስ  የመሰጣጣትን መንገድ ልናበረታታ አንችልም፡፡ በእርግጥ፣ የምሥጢረ ተክሊል ጸጋ ዓላማ ከሁሉም በላይ ‹‹የጥንዶችን ፍቅር ፍጹም ለማድረግ ነው›› (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ 1641)። እዚህ ላይ ደግሞ፣ ‹‹ተራራን ከቦታው የሚነቅል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ያለኝን ሁሉ ለድሆች ብሰጥ፣ ሰውነቴም እንዲቃጠል ለእሳት ብዳርግ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም›› (1 ቆሮ. 13፡ 2-3) ማለት እንችላለን፡፡ ‹‹ፍቅር›› የሚለው ቃል ግን በተለምዶና ብዙውን ጊዜ ያለ አግባብ ሲነገር ይስተዋላል፡፡ (ንጽ. ቤነድክቶስ 16ኛ፣ ዴውስ ካሪታስ ኤስት የተሰኘ ሐዋርያዊ መልእክት፣ (እ.አ.አ. ታህሣሥ 25፣ 2005)፣ 2፡ ኤኤኤስ 98 (2006)፣ 218)::

የየዕለት ፍቅራችን

በቅዱስ ጳውሎስ መሳጭ ምንባብ ውስጥ የእውነተኛ ፍቅር አንዳንድ ባሕርያት እናያለን፡-

·      ፍቅር ታጋሽ ነው፤ፍቅር ቸር ነው፤

·      ፍቅር አይመቀኝም፣ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፡፡

·      ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፤

·      ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም፡፡

·      ፍቅር ሁል ጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል›› (1 ቆሮ. 13፡ 4-7)

ፍቅርን በጥንዶችና በልጆቻቸው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መለማመድና ማዳበር ይቻላል ፡፡ ይህን የጳውሎስን መልእክት ትርጉም እርሱም ለእያንዳንዱ ቤተ ሰብ ተጨባጭ ሕይወት ያለውን ጠቀሜታ በጥልቀት ማሰላሰል ያስፈልጋል፡፡

ፍቅር ይታገሣል

ፍቅር ታጋሽ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ‹‹ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል›› ከሚለው ጋር አይገናኝም፡፡ ምክንያቱም ያንን ሐሳብ በመጨረሻው ስንኝ ላይ ተገልጾ ስለምናገኝ ነው፡፡ ትርጉሙም እግዚአብሔር ‹‹ለቁጣ የዘገየ››(ዘጸ 34፡ 6፤ ዘኁ. 14፡18) በሚለው  በብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ውስጥ ተገልጾአል፡፡ ከዚያም፣ በስሜታዊነት የማይሠራውንና የማያስቀይመውን ሰው ባህርይ ይጠቅሳል፡፡ እኛም ይህንን ባሕርይ ቃል ኪዳን ባቆመውና  በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ እርሱን እንድንመስል በሚጠራን በእግዚአብሔር ውስጥ እናያለን፡፡ ስለዚህ፣ ይህን ቃል የተጠቀመውን የቅዱስ ጳውሎስን  ጽሑፍ ለንስሐ በር የሚከፍተውን፣ ነገር ግን፣  በምሕረት ሥራዎቹ ኃይሉን የሚገልጠውን የእግዚአብሔርን ትዕግሥት  በሚወድሰው  በመጽሐፈ ጥበብ ብርሃን ማንበብ ያስፈልጋል (ንጽ. 11፡23፤ 12፡ 2፤ 15-18)፡፡ ለኃጢአተኞች ምሕረትን የሚያሳየው የእግዚአብሔር ‹‹ትእግሥት›› የእውነተኛ ኃይሉ ምልክት ነው፡፡   

ታጋሽ መሆን ራሳችንን ሁልጊዜ ለእንግልት ማጋለጥ፣ አካላዊ ጥቃትን መታገሥ ወይም ሌሎች ሰዎች እንዲጠቀሙብን መፍቀድ ማለት አይደለም፡፡ ግንኙነቶች ወይም ሰዎች ፍጹም መሆን አለባቸው ብለን ስናስብ ወይም ራሳችንን የሁሉ ነገር ማእከል ስናደርግና ነገሮች እኛ በምንፈልገው መልኩ እንዲሄዱ ስንጠብቅ ችግሮች ያጋጥሙናል፡፡ ያን ጊዜ ሁሉ ነገር ትዕግሥት እንድናጣ፣ ሁሉ ነገር ጠብ አጫሪዎች እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ትዕግሥትን ካልተለማመድን፣ የንዴት ምላሽ ለመስጠት ሁልጊዜ ሰበብ እንፈልጋለን፡፡ በመጨረሻም፣ ከሰው ጋር አብረን መኖር የማንችል፣ ፀረ ሕዝብ፣ ስሜታችንን መቆጣጠር የማንችልና ቤተሰቦቻችንን የጦር ሜዳ የምናደርግ ሰዎች እንሆናለን፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል፣‹‹ መራሪነትን ሁሉ፣ ቁጣና ንዴትን ፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ››(ኤፌ. 4፡ 31) የሚለን፡፡ ትዕግሥት ሥር ሊሰድ የሚችለው፣ ሌሎች ሰዎችም በማንነታቸው በዚህ ዓለም ላይ የመኖር መብት እንዳላቸው ስንገነዘብ ነው፡፡ ወደ ኋላ ቢጎትቱኝ፣ ዕቅዶቼን ቢያቃውሱብኝ፣ ወይም በድርጊታቸው ወይም በሐሳባቸው ቢያናድዱኝ፣ ወይም እኔ በምፈልገው መልኩ ባይሆኑልኝ አይገደኝም፡፡ ፍቅር ምንጊዜም ቢሆን፣ ድርጊቱ ከእኔ ፍላጎት የተለየ ቢሆን እንኳ፣ ሌላውን ሰው  የዚህ ዓለም አካል አድርጎ ወደ መቀበል የሚያደርስ ጥልቅ  የርኅራኄ ገጽታ አለው፡፡

ፍቅር ሌሎችን ያገለግላል

ሌላው ጳውሎስ የተጠቀመበትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ ቦታ ብቻ የተጠቀሰው ቃል ቸርነት ነው፡፡ ይህም ቃል ርኅራኄውን በድርጊቱ የሚገልጸውን መልካም ሰው የሚያመለክት ነው፡፡ ጳውሎስ ‹‹ትእግሥት›› ሙሉ በሙሉ የግዴለሽነት ባህርይ ሳይሆን፣ በድርጊት ፣ ከሌሎች ጋር በሚደረግ ንቁና ፈጠራ በታከለበት ግንኙነት የታጀበ መሆኑን ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ ቃሉ ፍቅር ሌሎችን እንደሚጠቅምና እንደሚረዳ ያመለክታል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ፍቅር ‹‹ቸር›› ተብሎ ተተርጉሞአል፤ ፍቅር ሌሎችን ለመርዳት ምን ጊዜም ዝግጁ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ፍቅር ስሜት ብቻ እንዳልሆነ  ጳውሎስ ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ ፍቅር ‹‹ከመውደድ›› እና ‹‹መልካም ከማድረግ›› ጋር የተያያዘ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ቅዱስ እግናጥዮስ ዘሎዮላ እንደተናገረው፣ ‹‹ፍቅርን ይበልጥ ማሳየት የሚቻለው በቃላት ሳይሆን በሥራ ነው››(መንፈሳዊ ልምምዶች፣ ፍቅርን ለማግኘት ማሰላሰል (230))። ስለዚህ ፍቅር ፍሬያማነቱን  ያሳየናል፤  ያለ አንዳች የአጸፋ ክፍያ በነጻ የመስጠትና የአገልግሎት ደስታን ለማግኘት ብቻ ራሳችንን ሳንሰስት ለሌሎች የመስጠትን ደስታና ክቡርነት እንድንለማመድ  ያደርገናል፡፡

ፍቅር አይመቀኝም

ቅዱስ ጳውሎስ የቅናትና የምቀኝነት አስተሳሰብ ከፍቅር ጋር እንደሚቃረን ያስገነዝባል፡፡ ይህም ማለት፣ ፍቅር በሌላ ሰው መልካም ዕድል ለመቅናት ቦታ የለውም (ንጽ. የሐዋ. 7፡9፤ 17፡5)፡፡ ቅናት በሌላ ሰው ብልጽግና መተከዝ ነው፡፡ ለራሳችን ጥቅም ብቻ እንጂ ለሌሎች ደስታ አለመጨነቃችንን ያሳያል፡፡ ፍቅር ከራሳችን በላይ እንድንሆን ሲያደርገን፣ ቅናት ግን በራሳችን ውስጥ እንድንጠመድ ያደርገናል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ለሌላ ሰው ስኬት ዋጋ ይሰጣል፤ ሌላውን ሰው እንደ ስጋት አይቆጥረውም፤ ራሳችንን ከቅናት ምሬት ነጻ ያደርገናል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የተለያዩ ስጦታዎችና የሕይወት መንገድ እንዳሉት ይገነዘባል፡፡ ስለዚህ፣ የራሱን የደስታ መንገድ ይፈልጋል፣ ሌሎችም የራሳቸውን መንገድ እንዲፈልጉ ይፈቅዳል፡፡

በጥቅሉ፣ ፍቅር ማለት  ‹‹ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣  በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር  አትመኝ›› (ዘጸ. 20፡17) የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ የመጨረሻ ሁለቱን ትእዛዛት መፈጸም ነው፡፡ ፍቅር ለእያንዳንዱ ሰው ልባዊ ክብር መስጠትንና የእርሱንም የመደሰት መብት ማወቅን ይቀሰቅሳል፡፡ ይህን ሰው እወደዋለሁ፣ ሁሉን ነገር ‹‹ደስ እንዲለን›› (1 ጢሞ. 6፡ 17) በሚሰጠን በእግዚአብሔር ዐይን አየዋለሁ፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ ጥልቅ የሆነ የደስታና የሰላም ስሜት አገኛለሁ፡፡ ይኸው ጥልቅ ፍቅር አንዳንዶች የተትረፈረፈ ሀብት ሲኖራቸው ሌሎች ግን በጣም ትንሽ የሚያገኙበትን ኢ-ፍትሐዊነት እንዲጠላ ያደርገኛል፡፡ ከኅብረተሰብ የተገለሉት ደስታ የሚያገኙበትን መንገድ እንድፈልግ ያነሣሣኛል፡፡ ያ ቅናት ሳይሆን የእኩልነት ምኞት ነው፡፡

ፍቅር አይመካም

መታበይ  የሚለው ቃል ከንቱ ውዳሴን፣ እብሪትን፣ ጉረኛነትንና መንጠባረርን ያመለክታል፡፡ ስለ ራሳቸው ብዙ ከማውራት መቆጠብን ብቻ ሳይሆን ፣ በሌሎች ላይ ማተኮርን  የሚወዱ ሰዎች የትኩረት ምንጭ መሆን አያስፈልጋቸውም፡፡ ፍቅር አይታበይም የሚለው ተከታይ ቃልም ትርጉሙ ያው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በሌሎች ፊት ‹‹አንታበይም››፡፡ ከዚህ ሌላ ፣ መታበይ ጉረኝነትንና ከእውነታ መራቅንም ያሳያል፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ይበልጥ ‹‹መንፈሳውያን›› ወይም ‹‹ጠቢባን›› አድርገው ስለሚያስቡ ከማንነታቸው በላይ ገዝፈው ለመታየት ይፈልጋሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ግሥ በሌላ ወቅት ተጠቅሞ ሲናገር ‹‹እውቀት ያስታብያል፣ ፍቅር ግን ያንጻል›› (1 ቆሮ. 8፡1) ይላል፡፡ አንዳንዶች ከሌሎች የበለጠ እውቀት ስላላቸው  ራሳቸውን ትልቅ አድርገው ያስባሉ፤ የሌሎች የበላይ ለመሆን ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም፣ እውነት ትልቅ የሚያደርገን የሌሎችን ሐሳብ የሚረዳ፣ ለሌሎች የሚያስብና ደካሞችን የሚያቅፍ ፍቅር ነው፡፡ ቃሉ በሌላ ቦታም በራሳቸው መታበይ ‹‹የተወጠሩ›› (ንጽ. 1 ቆሮ. 4፡18) ነገር ግን በእውነተኛ የመንፈስ ‹‹ኃይል›› ሳይሆን፣ በባዶ ቃላት የተሞሉ   ሰዎችን ለመውቀስ ጥቅም ላይ ውሎአል (ንጽ. 1 ቆሮ. 4፡ 19)፡፡

ክርሰቲያኖች ስለ እምነት ያነሰ ዕውቀት ያላቸውን፣ ደካሞችን ወይም ስለ እምነታቸው ጥርጣሬ የገባቸው የቤተሰቦቻቸውን አባላት በመደገፍ ፍቅራቸውን ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ የተገላቢጦሽ ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ በቤተሰብ ውስጥ አዋቂ ናቸው የሚባሉ ምእመናን ከመጠን በላይ ትምክህተኞች ይሆናሉ፡፡ በአንጻሩ ፣ ፍቅር በትህትና የሚገለጽ ነው፡፡ ከልባችን ሌሎችን ለማወቅ፣ ይቅር ለማለትና ለማገልገል ከፈለግን፣ ትዕቢታችን ሊረግብና ትህትናችን ሊያድግ ይገባል፡፡ ኢየሱስ ሥልጣን በሰፈነበት ዓለም ውስጥ፣ እያንዳንዱ ሰው የሌላው የበላይ ለመሆን  ይፍጨረጨራል፣ ‹‹በእናንተ መካከል ግን ይህ መሆን የለበትም›› (ማቴ. 20፡ 26) በማለት ለደቀ መዛሙርት ተናገረ፡፡ የክርስቲያናዊ ፍቅር ውስጣዊ አመክንዮ የታላቅነት ወይም የሥልጣን ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም ‹‹ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን›› (ማቴ. 20፡ 27)፡፡  በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ፣ ከሁሉ ዐዋቂ ወይም የበላይ የመሆን የፉክክር አመክንዮ ፍቅርን ያጠፋል፡፡ ስለዚህ፣ ‹‹ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፣ ምክንያቱም፣ ‹እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል››› (1. ጴጥ. 5፡ 5) የሚለው  የቅዱስ ጴጥሮስ ተግሳጽ ለቤተሰብም ይሠራል።

ምንጭ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 81-98 ላይ የተወሰደመሆኑን እንገልጻለን።

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

 

 

 

15 Mar 2023, 14:38