ንጉሥ ዳዊት በገና ሲደረድር የምያሳይ ምስል ንጉሥ ዳዊት በገና ሲደረድር የምያሳይ ምስል 

በጸሎት ራሳችንን ወደ እግዚአብሔር ስናቀርብ የብቸኝነት ስሜት አይሰማንም!

እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤እ ርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና ዐምባዬ ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። በአንተ ጒልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ። እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤በከፍታዎችም ላይ ያቆመኛል (መዝሙር 18፡ 2-3, 29, 33)።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረነው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ ከንጉሥ ዳዊት ጋር እንገናኛለን። ከልጅነቱ ጀምሮ እንኳን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ፣ በእግዚአብሔር ሕዝብ እና በእምነታችን ታሪክ ማዕከላዊ ሚና ለመጫወት ለልዩ ተልእኮ ተመርጧል። በወንጌል ውስጥ ኢየሱስ “የዳዊት ልጅ” በመባል ብዙ ጊዜ ተጠርቷል፣ እንደ እርሱ ማለትም እንደ ኢየሱስ በእውነቱ እርሱም በቤተልሔም ነው የተወለደው። በተሰጡት ተፋዎች እና ትንቢቶች መሠረት መሲሁ ከዳዊት ዘር ይመጣል፣ እርሱም ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሄር ልብ ጋር የተጣጣመ ንጉሥ የሚመጣው የመዳን እቅዱን በታማኝነት የሚያፀና ነው።

የዳዊት ታሪክ የሚጀምረው በቤተልሔም አቅራቢያ በሚገኙ ኮረብቶች ላይ ሲሆን የአባቱን የእሴይ በጎች መንጋ ያግድ ነበር። እሱ አሁንም ገና ልጅ ነው ፣ የብዙ ወንድሞች የመጨረሻው ልጅ። እስከዚያም ድረስ ነቢዩ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ትእዛዝ በመመራት አዲሱን ንጉሥ ለመፈለግ በሄደበት ወቅት አባቱ ስለ ታናሽ ወንድ ልጁ የዘነጋ ይመስል ነበር (1 ሳሙ 16፡1-13 ይመልከቱ)። እርሱ በገላጣው ምድር ላይ ይሠራ ነበር፣ እርሱ የተፈጥሮ ጓደኛ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ነፍሱን ለማፅናናት የሚችል አንድ ጓደኛ ብቻ ነበረው ይህም በገና ነው፣ በእነዚያ ረጅም ቀናት ውስጥ ብቻውን በሚሆንበት ወቅት በገና መደርደር እና ለአምላኩ መዘመር የወድ ነበር።

ስለሆነም ዳዊት በመጀመሪያ እረኛ ነበር፣ እንስሳትን የሚጠብቅ ፣ አደጋ እንዳይመጣ የሚከላከል ሰው ፣ ምግብ የሚሰጣቸው እረኛ ነበር። ዳዊት በእግዚአብሔር ፈቃድ ህዝቡን መንከባከብ በሚጀምርበት ወቅት እርሱ የሚያደርጋቸው ነገሮች በጣም የተለዩ አልነበሩም፣ ምክንያቱም የእረኝነት ልምድ ነበረውና። ለዚህ ነው የእረኛ ምስሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደጋግሞ የሚከሰተው። ኢየሱስ እራሱን እንኳን “መልካም  እረኛ” ሲል ገልጿል፣ ባህሪው ከተቀጣሪ እረኛ የተለየ ነው፣ በበጎቹ ምትክ ሕይወቱን ይሰጣል ፣ ይመራቸዋል፣ እያንዳንዳቸውን በስም ያውቃቸዋል (ዮሐ 10 11-18 ይመልከቱ)።

ዳዊት ቀደም ሲል ከነበረው ሥራው ብዙ ተምሯል። ስለዚህ ነቢዩ ናታን ዳዊት በፈጸመው ከባድ ኃጢአት ሲገሠጽው (2 ሳሙ 12፡1-15 የመልከቱ) ዳዊት መጥፎ እረኛ እንደነበረ፣ አንድ የሚወደው በግ ብቻ ከነበረው ሰው የሚወደውን እንዲቷን በግ እንደዘረፈው ወዲያውኑ ተረድቷል፣ ከእንግዲህ ወዲህ ትሑት አገልጋይ አይደለም ፣ ነገር ግን በስልጣን ጥም ያበደ፣ በሌሎች ላይ የዘረፋ ድርጊት የፈጸመ ሰው ሆነ።

በዳዊት ሙያ ውስጥ የቀረበው ሁለተኛው ባሕርይ ገጣሚ የነበረው ባህርይ ነው። ከዚህ አነስተኛ ምልከታ ፣ ዳዊት ከህብረተሰቡ ተነጥለው ለረጅም ጊዜ ለመኖር በሚገደዱ ግለሰቦች ላይ እንደሚታየው ፣ ዳዊት መጥፎ ሰው አለመሆኑን እንገምታለን። እሱ ይልቁንም ሙዚቃ እና መዘመር የሚወድ አሳቢ ሰው ነበር። በገና ሁል ጊዜ ከእርሱ አይለይም ነበር፣ አንዳንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር የውዳሴ መዝሙር በማቅረብ ያመሰግነው ነበር (2 ሳሙ 6: 16 ይመልከቱ)፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሐዘኑን ለመግለጽ ወይም የገዛ ኃጢአቱን ለመናዘዝ (መዝ 51፡3 ይመልከቱ) ይዘምር ነበር።

በዐይኖቹ ፊት የቀረበው ዓለም የዝምታ ትዕይንት አልነበረም ፣ ከዓይኖቹ ፊት እንደተገለጡ ሁሉ አንድ ታላቅ ምስጢር አየ። ያ በትክክል ጸሎት የሚነሳበት ቦታ ነው፣ ሕይወት በድንገት የሚወሰድብን ነገር ሳይሆን ነገር ግን ቅኔዎችን ፣ ሙዚቃን ፣ ምስጋናን ፣ ውዳሴን ፣ ሐዘንን እና ምልጃን በውስጣችን የሚያነሳሳ አስገራሚ ምስጢር ነው። ስለዚህ እነዚህ ከዳዊት መዝሙር ቅንብር በስተጀርባ ታላቅ አርቲስት እንዲሆን የረዱት ባህሎች ናቸው። መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ለእስራኤል ንጉሥ እና ይብዛም ይነስም በሕይወቱ በጣም የተከበሩ ድርጊቶችን በግልፅ ያመለክታሉ።

ስለሆነም ዳዊት መልካም እረኛ የመሆን ሕልም ነበረው። አንዳንድ ጊዜ ያንን በተግባር ላይ ያውለዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚያ ያነስ ተግባር ይፈጽማል። ሆኖም በመዳን ታሪክ አውድ ውስጥ አስፈላጊ የሚሆነው ፣ እርሱ ብቻ የሚያወጀው እና የሚያስተዋውቀው ሌላ ንጉሣዊ ትንቢት ነው።

ቅዱስ እና ኃጢአተኛ፣ ስደተኛ እና አሳዳጅ ፣ ሰለባ እና ነፍሰ ገዳይ። ዳዊት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሆኖ ነበር። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ብዙውን ጊዜ እርስ በእርሱ የሚቃረኑ ክስተቶችን በእኛ ሕይወት ውስጥ ተመዝግበዋል፣ በህይወት ድራማ ውስጥ ሰዎች ሁሉ እርስ በርሱ የሚጣጣም ተግባራትን ባለማከናወናቸው የተነሳ ብዙውን ጊዜ ኃጢአት ይሰራሉ። በዳዊት ሕይወት ውስጥ አንድ ነጠላ ወርቃማ ክር አለ፣ ይህም ለተከሰቱት ነገሮች ሁሉ አንድነት የሰጠው ጸሎቱ ነው። ያ የማይጠፋው ድምፅ ይህ ነው። የደስታ ወይም የጩኸት ድምጾች ቢሰማው ሁል ጊዜ አንድ ዓይነት ጸሎት ነው የሚያደርገው፣ የሚቀይረው ዜማ ብቻ ነው። ይህንን በማድረግ ዳዊት ሁሉንም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር በመወያየት ማድረግ እንደ ሚገባን አስተምሮናል፣ ደስታ ፣ ጥፋተኝነት ፣ ፍቅር እንዲሁም ሥቃይ ፣ ወዳጅነት ወይም ሕመም። ሁሉም ነገር ሁልጊዜ ለአንተ ከአንተ የሚነገር እርሱ የሚሰማው ቃል ሊሆን ይችላል።

ብቸኝነትን የሚያውቀው ዳዊት በእውነቱ በጭራሽ ብቻውን አልነበረም! በመጨረሻ በህይወታቸው ውስጥ ቦታ ለሚሰጡት ሁሉ ፀሎት የሚሰጠው ኃይል ነው። በህይወት ውስጥ የእያንዳንዱ ወንድና ሴት እውነተኛ ጓደኛ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ቁርኝት ብዙ መካራዎ ቢደርስባቸውም እንኳን የመጠበቅ ችሎታ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰኔ 17/2012 ዓ.ም በቫቲካን ሆነው ካደርጉት የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

21 September 2023, 10:05