ግንቦት 2016 ዓ.ም.  “የዕዳ ቀውስ በደቡቡ የዓለም ንፍቀ ክበብ” በሚል ርዕስ በጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሚገኙ  ተሳታፊዎች ግንቦት 2016 ዓ.ም. “የዕዳ ቀውስ በደቡቡ የዓለም ንፍቀ ክበብ” በሚል ርዕስ በጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች  (Vatican Media)

ካሪታስ ዓለም አቀፉን የዕዳ ቀውስ ማስቆም ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ተነገረ

ዓለም አቀፉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበጎ አድራጎት ተቋም የሆነው ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ስላጣው ዓለም አቀፍ የእዳ ቀውስ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶችን ለማበረታታት የፋይናንሺያል ስርዓቶችን ማዋቀር የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት ለማድረግ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ዌቢናር ሊያዘጋጅ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቫቲካን ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የሲቪሉ ማህበረሰብ መሪዎች እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ኢኮኖሚስቶች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በድህነት ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርገውን የዓለም አቀፍ የእዳ ቀውስ እንዴት ማስቆም እንደሚቻል በዌቢናር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።

በካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ እና በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተዘጋጀው ይህ የውይይት መድረክ “የተስፋ ነጋዲያን፡ በእዳ፣ በአየር ንብረት እና በልማት ላይ የኢዮቤልዩ ዓመት ተነሳሽነቶች” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፥ ግንቦት 20 ከቀኑ 9 እስከ 11 ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ዕዳን ወደ ተስፋ መቀየር
ይህ ዌቢናር የተዘጋጀው “ዕዳን ወደ ተስፋ መቀየር” በሚል ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ያካሄደውን ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተከትሎ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት አውድ ውስጥ፥ የሃይማኖት መሪዎች እና የፖሊሲ ባለሙያዎች በዚህ ቅዱስ ዓመት ላይ በሚያደርጉት ስብሰባ ዓለም አቀፉን የዕዳ ቀውስ ለማስቆም የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የዘመቻው ዋና ዓላማ ከ 3.3 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ትምህርት እና ጤና አጠባበቅ የመሳሰሉ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ይልቅ እዳቸውን ለመክፈል በሚታገሉባቸው በበርካታ ሃገራት ላይ እየታየ ያለው፥ ነገር ግን ትኩረት ያላገኘውን፥ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የዕድገት ቀውስ የሆነው ዓለም አቀፍ የዕዳ ቀውስ ትኩረት እንዲያገኝ ታስቦ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ይህ ዌቢናር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነው ላውዳቶ ሲ' አሥረኛ ዓመት በሚከበርበት፥ እንዲሁም በ 2025 የዓለም የሰላም ቀን ላይ የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት “እንደ ልግስና ሳይሆን የፍትህ አንዱ አካል በማድረግ” በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕዳ ላለባቸው ሀገራት እፎይታ እንዲሰጥ ካቀረቡት ጥሪ ጋር የሚገጣጠም መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ለውይይት የሚቀርቡ ሃሳቦች ምንድናቸው?
ውይይቱ ላይ ከሚቀርቡ ተሳታፊዎች መካከል በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ እና የህዝብ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ማርቲን ጉዝማን፣ የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ፀሐፊ እህት አሌሳንድራ ስሜሪ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ጆርዳኖ ካቺያ ይገኙበታል ተብሏል።

ውይይቶቹ በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት የዕዳ ጫናን ለማቃለል እና የዓለም የገንዘብ ስርዓትን ለማሻሻል በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ እንደሚያተኩሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ተወያዮቹ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስተምህሮ በሆነው በሰብአዊ መብቶች እና በአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት ላይ የፋይናንስ ስርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊነት ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
 

28 May 2025, 14:30