ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "የሐዋርያዊ ምሕረት አመክንዮ"

አለመግባባትን ሁሉ ለማስወገድ፣ ቤተክርስቲያን በማናቸውም አኳኋን የጋብቻን ሙሉ ዓላማና የእግዚአብሔርን ክቡር ዕቅድ ከመግለጽ መቆጠብ እንደሌለባት ለመጠቆም እፈልጋለሁ። “የተጠመቁ ወጣቶች ምሥጢረ ተክሊል የፍቅር ተስፋቸውን እንደሚያለመልና በምሥጢሩ ውስጥ ባለው የክርስቶስ ጸጋና በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በሙላት ለመሳተፍ በመቻላቸው በሕይወታቸው እየጠነከሩ እንደሚሄዱ ያውቁ ዘንድ ማበረታታት ያስፈልጋል”። ቀዝቃዛ አመለካከት፣ ማናቸውም ዐይነት አንጻራዊነት፣ ወይም ያንን ዓላማ በመግለጽ ረገድ የሚታየው ያልተገባ ቁጥብነት በወንጌል ያለመተማመንና በቤተክርስቲያን በኩል ለራሳቸው ለወጣቶች ፍቅር የማጣት ምልክት ይሆናል። ልዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ግንዛቤ መኖሩን ማሳየት፣ የሙሉ ዓላማን መደብዘዝ ወይም ኢየሱስ ለሰው ልጅ ከሰጠው ያነሰ ነገር ማቅረብን ከቶ አያመለክትም። ዛሬ፣ ከሐዋርያዊ እንክብካቤ ውድቀቶች ይልቅ ጋብቻዎችን የማጠናከርና እንዳይፈርሱ የመከላከል ጥረት የበለጠ ዋጋ አለው።

ከዚሁ ጋር፣ ስነ ልቦናዊ፣ ታሪካዊና ስነ ሕይወታዊ የሆኑ አለዛቢ ሁኔታዎች ክብደት እንዳላቸው ስለምናውቅ፣ “ከወንጌላዊ አስተሳሰብ ሳይዛነፉ፣ በሂደት የሚከሰቱ ግላዊ የእድገት ደረጃዎችን በምሕረትና በትእግሥት መደገፍ” እንዲሁም “የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ለሚገፋፋን ለጌታ ምሕረት ቦታ መስጠት” ያስፈልጋል። ለጥርጣሬ ምንም ክፍተት የማይሰጥ ብርቱ ሐዋርያዊ እንክብካቤን የሚመርጡ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ፣ ቤተክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በሰብአዊ ድክመት ውስጥ ለሚዘራው ደግነት ትኩረት የምትሰጥ፣ እውነተኛ አስተምህሮዋን የምትገልጽ፣ “በሂደት ጫማዎችዋ በመንገድ ላይ ቢቆሽሹም እንኳ ሁሌም በተቻላት አቅም መልካም የምታደርግ” እናት እንድትሆን ኢየሱስ ይፈልጋል። የቤተክርስቲያን እረኞች የወንጌልን ሙሉ ሐሳብና የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለምእመናን ሲያቀርቡ፣ ድሆችን በቸርነት እንዲይዙና ነገሮችን ከማባባስ ወይም አላስፈላጊ የሆነ ከባድና ጥድፊያ የበዛበት ፍርድ ከመስጠት እንዲቆጠቡ መርዳት ይኖርባቸዋል። ወንጌል ራሱ እንዳንፈርድ ወይም እንዳንኮንን ይነግረናል (ማቴ. 7፡1፤ ሉቃ. 6፡ 37)። ኢየሱስ  “ከሰብአዊ መከራና ረብሻ የሚከላከሉልንን ግላዊና ማህበራዊ ጓዳዎች ፍለጋ አቁመን፣ ወደ ሌሎች ሰዎች የሕይወት እውነታ እንድንገባና የቸርነትን ኃይል እንድናውቅ ይፈልጋል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ሕይወታችን ድንቅ በሆነ ሁኔታ ይጠላለፋል”።

እነዚህ ሐሳቦች ለምሕረት ከተመደበው ቅዱስ ዓመት አኳያ መንፀባረቃቸው ዕድለኛነት ነው። ምክንያቱም ቤተሰቦችን በሚመለከቱ በርካታ ሁኔታዎች “ቤተክርስቲያን የወንጌል የልብ ትርታ የሆነውንና በራሱ መንገድ ወደ እያንዳንዱ ሰው አእምሮና ልብ ውስጥ መስረጽ የሚገባውን የእግዚአብሔርን ምሕረት የመስበክ ኃላፊነት አለባት። የክርስቶስ ሙሽራ በባሕሪያዋ ያለ አንዳች ልዩነት ወደ ሁሉም ሰው ዘንድ የሚቀርበውን የእግዚአብሔርን ልጅ ምሳሌ መከተል ይኖርባታል”። ኢየሱስ ራሱ የዘጠና ዘጠኙ ብቻ ሳይሆን የመቶዋቹ በጎች እረኛ እንደ ሆነ ታውቃለች። እርሱም በጎቹን ሁሉ ያውቃቸዋል። በዚህ ግንዛቤ መሠረት፣ የምሕረት ዘይት የእግዚአብሔር መንግሥት ከወዲሁ በመካከላችን የመሆኑ ምልክት ሆኖ ለሁሉም ሰው፣ ለምእመናንና ርቀው ላሉት ሁሉ ሊዳረስ ይችላል”።

“ምሕረት የአብ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱ እውነተኛ ልጆች እነማን እንደሆኑ የሚታወቁበት መለኪያ ነው። በአጭሩ፣ ምሕረት አስቀድሞ ስለ ተደረገልን እኛም ምሕረት ማሳየት ይጠበቅብናል”። ይህ ተራ የፍቅር ስሜት ወይም ሁልጊዜ ለእኛ መልካሙን ለሚመኝልን ለእግዚአብሔር ፍቅር የሚሰጥ ቀዝቃዛ ምላሽ አይደለም። ምክንያቱም “ምሕረት የቤተክርስቲያን ሕይወት መሠረት ነው። ሐዋርያዊ ሥራዋ ሁሉ ለምእመናን በምታሳየው ደግነት የተሞላ መሆን አለበት፤ በስብከትዋና ለዓለም በምታቀርበው ምሥክርነት ውስጥ ምሕረት መታጣት የለበትም”። አንዳንድ ጊዜ “የጸጋ አመቻቾች ሳንሆን አዳዮች እንመስላለን። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ዕቃ ማስቀመጫ አይደለችም፤ ሰዎች ሁሉ ከነችግሮቻቸው ቦታ የሚያገኙበት የአብ ቤት ናት”።

የግብረ ገብ ነገረ መለኮት አስተምህሮ እነዚህን ግምቶች ማካተት ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን የግብረ ገብ ትምህርት የተቀናጀ እንዲሆን ማሰቡ እውነት ቢሆንም፣ ከሁሉ ለሚበልጡና ይበልጥ መሠረታዊ ለሆኑ የወንጌል እሴቶች በተለይም ለእግዚአብሔር ነጻ የፍቅር ስጦታ ምላሽ ለሆነው ለምሕረት ቅድሚያ ለመስጠት ሁልጊዜ ልዩ ትኩረት ማድረግና ይህንንም ማበረታታት ይገባል። አንዳንድ ጊዜ በሐዋርያዊ ሥራችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ነጻ የፍቅር ስጦታ ቦታ መስጠት ይከብደናል። ስለ ምሕረት ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ስለምናስቀምጥ ተጨባጭ ትርጉሙንንና እውነተኛ ጠቀሜታውን ዋጋ እናሳጣለን። ያ ወንጌልን የማለዘብ ከሁሉ የከፋ መንገድ ነው። ለምሳሌ፣ ምሕረት ፍትህንና እውነትን እንደማያስቀር ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ ምሕረት የፍትህ ሙላትና የእግዚአብሔር እውነት ብሩህ መገለጫ ነው ማለት አለብን። በዚህ ምክንያት፣ ‹‹የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነትና በተለይም ምሕረቱን ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ ማናቸውም ነገረ መለኮታዊ ጽንሰ ሐሳብ ብቃት እንደሌለው›› ሁልጊዜ ማጤን ይኖርብናል።

ይህም ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አያያዝን በተመለከተ ቀዝቃዛና ውጣ ውረድ የበዛበት ግብረ ገብነትን ለማስወገድ የሚረዳ ማዕቀፍና ሁኔታን ያመቻችልናል። በመሐሪ ፍቅር የተሞላ፣ ለመረዳት፣ ይቅር ለማለት፣ አብሮ ለመጓዝ፣ ለተስፋና ከሁሉ በላይለውህደት ዝግጁ የሆነ ሐዋርያዊ ዕውቀት እንዲኖረን ያደርገናል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊሰፍንና “በኅብረተሰብ ጽንፍ ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ልባችንን እንድንከፍት” ሊያደርገን የሚገባው አስ ተሳሰብ ይህ ነው። ስለዚህ፣ በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ምእመናን ከመንፈሳዊ እረኞቻቸው ወይም ሕይወታቸውን ለጌታ ካስገዙ ሌሎች ምእመናን ጋር በልበ ሙሉነት እንዲነጋገሩ አበረታታቸዋለሁ። በእነርሱ ውስጥ የራሳቸውን ሐሳብ ወይም ምኞት የሚደግፍ ነገር ሁሌ ባያገኙም፣ ያሉበትን ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱና ለግላዊ ዕድገት የሚመቻቸውን መንገድ ለመፈለግ የሚረዳቸውን አንዳንድ ሐሳብ ሊያገኙ ይችላሉ። እንደዚሁም የቤተክርስቲያን እረኞች ችግራቸውንና ሐሳባቸውን ከልብ ለመረዳት፣ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተገቢ ስፍራ እንዲያውቁ ለመርዳት ምእመናንን በሙሉ ስሜትና የመንፈስ እርጋታ እንዲያዳምጡአቸው አደራ እላለሁ።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 307-312 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

 

21 Jun 2025, 16:36