በደማስቆ በሚገኝ የቅዱስ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በደማስቆ ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት 25 ሰዎች ሲሞቱ 63 ሰዎች ቆስለዋል። የቅድስት ሀገር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በጥቃቱ የተሰማውን ጥልቅ ቅሬታ በመግለጫው ገልጿል።
ሊነገር የማይችል የክፋት ድርጊት ነው!
በቅድስት ሀገር የሚገኝ የካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጉባኤ (ACOHL)፥ በኢየሩሳሌም፣ በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በዮርዳኖስ እና በቆጵሮስ የሚገኙ ካቶሊካዊ አስተዳደሮች ውስጥ ስልጣን ያላቸውን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን የሚያስተባብር እንደሆነ ይታወቃል።
ጉባኤው በመግለጫው፥ በንጹሐን ላይ እና በቅዱስ ሥፍራ የተፈጸመው ጥቃት በእምነትም ሆነ በሥነ-ምግባር አኳያ ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾ፥ “ለዚህ ዓመፅ ምክንያት የሆነው ሃይማኖት ነው ብሎ መውሰዱ ቅዱስ የሆነውን በሙሉ ማዛባት ወይም ማጣመም ነው” ሲል አስታውቋል።
“የተፈጸመው ጥቃት በቃል ሊገለጽ የማይችል የክፋት ድርጊት ነው!” ያለው መግለጫው፥ “በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እና በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው” ሲል አስረድቷል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአቡ ዳቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. የፈረሙትን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ የጠቀሰው መግለጫው፥ “ይህ ጥቃት በሰላም እና በመረጋጋት የማምለክ መብትን የሚጥስ ነው” ሲል አስረድቷል።
መግለጫው በመቀጠልም፥ “የአምልኮ ቦታዎችን ማለትም ምኩራቦችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጊዶችን ከአደጋ እና ከጥቃት መከላከል በሃይማኖቶች፣ በሰብዓዊ እሴቶች፣ በሕጎች እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጡ ግዴታዎች ናቸው” ብሎ፥ የአምልኮ ቦታዎችን ማጥቃት ወይም ማውደም፣ እንዲሁም ምዕመናንን በጥፋት መሣሪያዎች ለማስፈራራት የሚደረግ ሙከራ በሙሉ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ የወጣ ነው” ሲል አስረድቷል።
የሶርያ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሰላም ይኖር ዘንድ
ጉባኤው ከዚህም በላይ፥ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት በማውገዝ፥ በሃይማኖት ስም የሚካሄደውን ዓመፅ አሳማኝ ምክንያት አድርጎ ለማቅረብ የሚጥሩ አስተሳሰቦችን በመቃወም፥ ለአንጾኪያ እና ለመላው ምሥራቅ የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።
ጉባኤው ለዓመታት ያኅል በስደት ለሚገኝ የሶርያ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች አጋርነቱን ገልጾ፥ ተጎጂዎችን በጸሎት በማስታወስ ለቆሰሉት ፈውስን እና ለተጎጂ ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትን ተመኝቷል።
በተጨማሪም “የሶርያ ባለ ሥልጣናት በሀገሪቱ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ጥበቃ እንዲደረግላቸው፥ በአገራቸው ውስጥ በሰላም እና በነፃነት እንዲኖሩ ለማድረግ ሕይወታቸውን በሙሉ ለትውልድ አገራቸው እንዲሠሩ” በማለት አሳስቧል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው፥ እሑድ ሰኔ 15/2017 ዓ. ም. ከመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ያደረጉትን ንግግር ያስታወሰው መግለጫው፥ “የመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም የሶርያ ሕዝቦች በሰላም፣ እርስ በእርስ በመከባበር እና በመተሳሰብ በጋራ አብረው እንዲኖሩ፣ የጥላቻ እና የአክራሪነት ስሜቶች በቆራጥነት እንዲወገዱ” በማለት በጸሎት ደምድሟል።