በናይሮቢ ኪቤራ አውራጃ በሚገኘው በፎርት ጄሱስ በሚገኘው የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ተልእኮ በሆነው በቅዱስ ጆአንስ ሌጂዮ ማሪያ ቤተክርስቲያን ምእመናን የትንሳኤ በዓል ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በናይሮቢ ኪቤራ አውራጃ በሚገኘው በፎርት ጄሱስ በሚገኘው የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ተልእኮ በሆነው በቅዱስ ጆአንስ ሌጂዮ ማሪያ ቤተክርስቲያን ምእመናን የትንሳኤ በዓል ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ  

የቤኔዲክታዊያን እህቶች ማህበር በአመፅ ምክንያት በኬንያ የሚገኙ ተቋሞቻቸውን መዝጋታቸው ተነገረ

በኬንያ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ኬሪዮ ሸለቆ ሁለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህናት መገደላቸውን ተከትሎ፣ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ የቤኔዲክታዊያን ሚሲዮናዊያን እህቶች ገዳም በአከባቢው የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋሞቻቸውን መዝጋታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኬንያ ኬሪዮ ሸለቆ አካባቢ የተነሳውን ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥን ተከትሎ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ቤኔዲክታዊያን እህቶች ገዳም የአገልግሎት መስጫ ተቋሞቻቸውን በሮች መዝጋታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ ጉዳዩን አስመልክተው እንደገለጹት ተቋሞቻቸውን የዘጉት የካህናቱን ሞት ተከትሎ እንደሆነ እና ይሄም “ላልተወሰነ ጊዜ” መሆኑን በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል።

የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ እንደዘገበው፥ በአከባቢው የቤኔዲክታዊያን እህቶች ሚስዮናዊያን ገዳም የበላይ አለቃ የሆኑት እህት ሮዛ ፓስካል የውሳኔ መግለጫው ላይ መፈረማቸውን የጠቆመ ሲሆን፥ ሲስተር ሮዛ ጉዳዩን አስመልክተው እንደገለጹት ውሳኔው የተላለፈው ‘የአባ አሎይ ቤት ግድያ እና በአካባቢው እየደረሰ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ነው’ ሲሉ አስረድተዋል።

እህት ሮዛ አክለውም ብጥብጡ በሚስዮናውያን ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ “በእህቶቻችን ላይ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሏል” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ በአከባቢው በተነሳው ቀውስ ምክንያት ሰራተኞቻቸው ሥፍራው ለቀው ለመውጣት በመገደዳቸው፥ የቤኔዲክታዊያን ሚስዮናውያን እህቶች ለአከባቢው እጅግ አስፈላጊ የነበሩትን አገልግሎቶች ማስኬድ እንዳልተቻለም ጨምረው ገልጸዋል።

ወደፊት ምን ይከሰታል
እህት ሮዛ ፓስካል እንደተናገሩት በውሳኔው መሰረት “አካባቢው ለአገልግሎት ደህንነቱ የተጠበቀ እስኪሆን ድረስ የአገልግሎት ጣቢያዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ሆነው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም፥ የተቋሞቻቸው መዘጋት በክልሉ ውስጥ የሚሰሩ ገዳማዊያትን፣ ሰራተኞችን እና ለተለያየ አገልግሎት ተልዕኳቸውን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ታስቦ እንደሆነም ጭምር አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የገዳሙ ሃላፊ እንደገለጹት ይህ የቼሶንጎች ሚሽን ሆስፒታል መዘጋትንም የሚጨምረው ውሳኔ ሰላማዊ ዜጎችን ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ፥ ለአካባቢው ሰላም ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስገኝ መንግስት ላይ ጫና እንደሚያደርግ” ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአካባቢው እየታየ ያለው አለመረጋጋት
ተቋሞቹ የተዘጉት በስድስት ቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያ ካህናት መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በኢግዋሚቲ የሚገኘው የቅዱስ ሉዊስ ቤተክርስትያን ቁምስና ካህን አባ ጆን ንዴግዋ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. መንገድ ዳር ላይ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ወድቀው ከተገኙ በኋላ ሆስፒታል እንደደረሱ ህይወታቸው ያለፈው እና ከሰባት ቀናት በኋላ፣ ግንቦት 14 አባ አሎይስ ቼሩዮት በኬሪዮ ሸለቆ ውስጥ ሽፍቶች ባደረሱት ጥቃት በጥይት ተመትተው መገደላቸው ተነግሯል።

የኪሱሙ ሊቀ ጳጳስ እና የኬንያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት (KCCB) ብጹእ አቡነ ሞሪስ ሙሃቲያ ማኩምባ ትክክለኛውን ሁኔታ እና ዓላማ ለመግለጥ፣ እንዲሁም የካህናቶችን እና የመላው ኬንያውያንን የወደፊት ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል የካህናቶቹ አሟሟት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
 

04 Jun 2025, 15:30