በኬፕ ቨርዴ የካቶሊክ ማህበራዊ ትምህርት በልማት እና በማህበራዊ ፍትህ ውስጥ ያለው ሚና ወሳኝ ነው ተባለ
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዚህ ጉባኤ ዋና ዓላማ በወንጌል እና በካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮ የተመሰረቱ የአካታችነት፣ የፍትሃዊነት፣ የሰላም እና የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን ማሳደግ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በውይይቱ ወቅት ከተነሱት ጭብጦች ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ እና ሚዛናዊ ልማት ላይ መሳተፍ የምትችልባቸው መንገዶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደተደረገበት ተገልጿል።
ዝግጅቱ የተካሄደው ኬፕ ቨርዴ በሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (Escola Universitária Católica de Cabo Verde) ውስጥ ሲሆን፥ በካቦ ቨርዴ የሳንቲያጎ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አርሊንዶ ፉርታዶ በመርሃ ግብሩ ላይ መገኘታቸው ተገልጿል።
በር.ሊ.ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ እና 14ኛ መካከል ያለችው ቤተክርስቲያን
የሀገረ ስብከቱ የፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቶ ኢማኑኤል ሚራንዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና ፍትህን በማስፈን ረገድ ያላትን ወሳኝ ሚና በመጥቀስ፥ በወንጌል ላይ በመመስረት ቤተክርስቲያን በህብረተሰቡ ውስጥ ንቁ ድምጽ ለመሆን ቁርጠኛ መሆኗን በአጽንዖት ተናግረዋል።
የኬፕ ቨርዴ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አባ ሆሴ ኤድዋርዶ አፎንሶ በበኩላቸው “ከሬረም ኖቫሩም እስከ ዲጂታል ዘመን፡ በሊዮ 13ኛ እና በሊዮ 14ኛ መካከል ያለው የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ” በሚል ርዕስ ወሳኝ ንግግር ማድረጋቸው ተገልጿል።
አባ ሆሴ አፎንሶ በተለይ በዲጂታል ዘመን እየተከሰቱ ያሉትን በርካታ ግጭቶች እና ፈጣን የህብረተሰብ ለውጦች ግምት ውስጥ በማስገባት የውይይቱን አስፈላጊነት ያስገነዘቡ ሲሆን፥ የካቶሊክ ማሕበራዊ ትምህርት በተለይ “አሁን ባለንበት የለውጥ ወቅት” የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ማጣቀሻ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበረ አስታውሰው፥ አክለውም የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ በማህበራዊ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚ እና በመገናኛ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ እውነታዎች መካከል ምላሾችን እና ትርጉም ያለው መመሪያን ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በጉባኤው የፖርቹጋል ብሄራዊ የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ፔድሮ ቫዝ ፓቶ ጉዳዩን አስመልክተው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው የነበረ ሲሆን፥ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን በቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ አስተምህሮ እይታ በመዳሰስ ለውይይቱ ጠቃሚ አስተዋፅኦ እንዳደረጉም ተገልጿል።