የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እህት በታይላንድ ከፍተኛውን የፀረ- ህገ ወጥ የሰው ዝውውር ሽልማት መቀበላቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቅዱስ ጳውሎስ ደ ቻርትረስ ገዳም አባል የሆኑት እህት ሜሪ-አግነስ ሱዋንና ቡአሳፕ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ብሔራዊ የፀረ- ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን በሚል በባንኮክ በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይ በታይላንድ የማህበራዊ ልማት እና የሰው ደህንነት ሚኒስቴር የክብር ሽልማት ተሸልመዋል።
ሽልማቱ ለእህት ማሪ የተሰጠው በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች እና ህጻናትን ለመታደግ ባሳዩት “ደፋር፣ ፈጠራ የታከለበት እና ቀጣይነት ያለው” ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቅረፍ ላደረጉት ጥረት ለማመስገን እንደሆነ ተገልጿል።
ዝግጅቱ በመላው ታይላንድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚሰሩ በእምነት ላይ የተመሰረቱ እና የዓለማዊ ቡድኖች ተወካዮችን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ከመርከበኞች ህብረት እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በሕገወጥ መንገድ የተዘዋወሩ አሳ አጥማጆችን እና የባህር ተሳፋሪዎችን ለማዳን እና ለመደገፍ በሚሰራው የቻንታ-ቡሪ ሀገረ ስብከት የባህር ተጓዦች አገልግሎት የመጡት እህት ስቴላ ማሪስ ይገኙበታል።
እህት ማሪ አግነስ ከሊካስ ኒውስ (LiCAS News) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በተለይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የ 2025 ኢዮቤልዩ ዓመት እያከበረች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍል በተስፋ እና በተጨባጭ እርምጃ መድረስ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
“የተስፋ ነጋዲያን እንድንሆን የተጠራንበት ይህ የኢዮቤልዩ ዓመት፥ በዳርቻ ላይ ለሚኖሩ፣ በተለይም ለብዝበዛ ተጋላጭ ለሆኑት ወጣት ሴቶች ትልቅ ተስፋን ይሰጣል” ያሉት እህት ማሪ፥ “መተማመንን መፍጠር አስፈላጊ ስለሆነ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ከምናገለገልባቸው ማህበረሰቦች ጋር በጥልቀት መተሳሰር አለብን ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።
የእርሳቸው ፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትግል አካሄድ በትምህርት፣ በማብቃት እና በማህበረሰብ አቀፍ አመራር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ ከሲስተር ማሪ ተነሳሽነቶች መካከል በ35 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 3,182 መምህራንን በማሰልጠን የፀረ-ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ ከ60,000 በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ በሰሜናዊ የድንበር ክልሎች በወጣቶች የሚመራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን መደገፍ፣ የረዥም ጊዜ ተሟጋችነትን ለመገንባት የህፃናት ታሊታ ኩም ትሥሥሮችን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ማቋቋምን የሚያካትት ነው ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ ገቢን ለማሳደግ የበርበሬ ምርቶችን ማምረትን ጨምሮ በሦስት ሰሜናዊ መንደሮች ውስጥ ለሴቶች መተዳደሪያ መርሃ ግብሮችን እንዳስጀመሩ እና ከ800 በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የክህሎት ማጎልበት እና የማህበረሰቡ አቅም ላይ ያተኮሩ አውደ ጥናቶችን እንዲሰጡ 40 የታሊታ ኩም በጎ ፈቃደኞችን አሰማርተዋል።
በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዲትን መበለት ከሞት ሲያስነሳ “አንቺ ሴት፣ ተነሺ” ብሎ በተናገረው ቃል ላይ ተንተርሶ የተሰየመው የ ‘ታሊታ ኩም እንቅስቃሴ’ በ 2001 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበላይ አለቆች ገዳማዊያት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ያቋቋሙት ዓለም አቀፍ ትሥሥር እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ትሥሥሩ ከ 90 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ እየሰራ ይገኛል።
ሲስተር ማሪ አግነስ ተልእኮውን ለማስቀጠል የምእመናን እና የሰፊዋ ቤተክርስትያን ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፥ “ይህ ሥራ በፍጹም በተናጠል የሚሰራ ሥራ ሳይሆን፥ የጋራ ቁርጠኝነት፣ እምነት እና ርህራሄ ውጤት ነው” ብለዋል።
እህት ማሪ ጠንካራ ሥራዎችን በመፈጸም የተሸለሙት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፀረ-ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰራው ሥራ እየተመናመነ በመጣበት ወቅት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ 2012 ዓ.ም. ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጋር የተገናኘ የወንጀል ምርመራ በ 11 በመቶ፣ የቅጣት ውሳኔዎች ደግሞ በ 27 በመቶ መቀነሱን ይፋ ማድረጉ እና ይህ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ በሰፊው እየታየ ያለ ውጤት መሆኑ ተገልጿል።
የሲስተር ማሪ አግነስ ብሄራዊ ሽልማት በዓለም ላይ ካሉት ቀጣይነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ተግዳሮቶች መካከል አንዱን ለመጋፈጥ በእምነት ላይ የተመሰረቱ መሰረታዊ እርምጃዎች ያላቸውን ኃይል የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው ተብሏል።