አንድ ካቶሊካዊት እህት አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሲኖዶሳዊ አቀራረብን እያስተዋወቁ እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአሜሪካን የቅጣት ሥርዓት ሲታሰብ በታዋቂ ፊልሞች እና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩትን አስከፊ ሁኔታዎች እናስታውስ ይሆናል። ሆኖም አንድ ሰው በእነዚህ አከባቢዎች ውስጥ ስለ ፍትህ ክትትል ወይም ተግባራዊነት ሲሰማ ወደ አእምሮው የሚመጡት የመጀመሪያ ቃላት ቅጣት እና ተገቢ የሆነ ፍርድ ሊሆኑ ይችላሉ።
እርግጥ ነው ካቶሊካዊ የሆነው የፍትህ ግንዛቤያችን ከዚህ ጠባብ ትርጉም ባሻገር እንደ ማገገሚያ እና ተሃድሶ ያሉ ጽንሰ-ሀሳቦችን እና ግቦችን ይጨምራል። በወንጌል ላይ የተመሰረተው እውነተኛ ፍትህ የሚያተኩረው እውነተኛ ሰላም፣ እድገት አልፎ ተርፎም ኅብረትን ጭምር ያካተተ ነው። ይህ የፍትህ ራዕይ ሲኖዶሳዊ ሂደት ሲሆን፥ በተፈጥሮ ውስጥ ያለ እና ሊጠፋ የማይችል በእያንዳንዱ ሰው ሰብአዊ ክብር ላይ የተመሰረተ ነገር ነው።
ሆኖም ግን ያ የፍትህ ራዕይ፣ ከባድ ወንጀሎች በተፈፀመበት ጊዜ እንኳን ቢሆን የእያንዳንዱን ሰው ሰብአዊ ክብር እውቅና መስጠት አለመስጠቱን በዩናይትድ ስቴትስ ካለው የእስር እና የሞት ቅጣት ባህሪ አንፃር እንዴት ይታያል ለሚለው ጥያቄ ሲስተር ጃኔት ሲመልሱ፥ በሃገሪቱ ይህ ተግባራዊ እየሆነ ነው ብለው እንደማያስቡ ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት በመላው ኢሊኖይ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የማገገሚያ ፍትህ ስልጠናዎችን እየሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል።
በማረሚያ ቤት ውስጥ የተስፋ ዘር መዝራት
እህት ጃኔት ክሊንተን ግዛት፣ አዮዋ ስቴት ውስጥ የሚገኘው የፍራንቺስካዊያን ገዳም አባል ሲሆኑ፥ ከአስር ዓመታት በላይ በእንግዳ ተቀባይነት፣ በተስፋ እና በፈውስ ሰሰብአዊ ክብርን ለመመለስ በቺካጎ ውስጥ በሚገኘው ‘ክቡር ደም የእርቅ አገልግሎት’ (Precious Blood Ministry of Reconciliation - PBMR) በተሰኘው ቺካጎ በሚገኘው ድርጅት ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ።
በተለይ ለተስፋ የተሰጠን ልዩ የኢዮቤልዩ ዓመት እያከበርን በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት ሲስተር ጃኔት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በተስፋ የተሞላ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በካቶሊክ ሀይማኖታዊ ሥርዓት የተመሰረተው የክቡር ደም ሚስዮናውያን አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙትን ወንዶች እና ሴቶችን ጨምሮ በአመጽ እና በወንጀል ፍትህ ስርዓቱ የተጎዱ የማህበረሰብ አባላትን እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን፥ በዚህ አገልግሎት ውስጥ የሲስተር ጃኔት ልዩ ሚና ሰላም ላይ የሚሰራውን አንዱን የአገልግሎት ክፍልን መምራት እንደሆነ ተነግሯል።
‘የሰላም ሂደትን መልሶ የማቋቋም ልምምድ’ በመባልም ጭምር የሚታወቀው የሰላም ክበብ፣ ተሳታፊዎች ክብ ሰርተው እንዲቀመጡ እና የውይይት ጊዜን እንዲያሳልፉ የሚጋብዝ ሲሆን፥ ልክ እንደ ሲስተር ጃኔት ያሉ አስተባባሪዎች እያንዳንዱ ሰው ምላሽ የመስጠት እድል ያለው ተከታታይ ጥያቄዎችን በመጠቀም ውይይቱን ይመራሉ።
ሲስተር ጃኔት በቅርቡ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን እና ሰራተኞችን ዘና የሚያደርጉ የልምምድ ሂደቶችን እንዲጠቀሙ በማሰብ አዲስ የክበብ ሂደት ስልጠና ፕሮግራም የጀመሩ ሲሆን፥ ይህንን ፕሮግራም ለህግ ታራሚዎች ብቻ ሳይሆን በማረሚያ ቤት ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችም ጭምር እንደሚሰጥ እና በዚህም ሁኔታ የተለመደውን አሰራር በማሻሻል ባልተለመደ መልኩ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሲስተር ጃኔት በዚህ አገልግሎት ውስጥ ከታራሚዎች እና ሰራተኞች ጋር በተሰበሰቡ ቁጥር “ቆንጆ፣ አፍቃሪ፣ አስቂኝ እና ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው ሰዎች” ጋር የመገናኘት እድል እንደሚያገኙ እና በዚህም ውስጥ ብዙ ሳቅ እና ብዙ እንባ እንዳለ ገልጸው፥ በዚህ የክበብ ሂደት እውነተኛ ውይይት በኩል በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውን ሰብአዊነት ለመለየት የሚያስችል ቦታ እንደሚፈጥር እና ምንም እንኳን ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም የረዥም ጊዜ ተጽእኖ የማሳደር እና እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አቅም እንደሚገነባ ገልጸዋል።
ሲስተር ጃኔት እያንዳንዱ ስልጠና በአራት ቀናት ውስጥ እንደሚካሄድ እና ለማጠናቀቅ ቢያንስ 28 ሰዓታት እንደሚወስድ የገለጹ ሲሆን፥ በእነዚህ ጊዜያት በእስር ላይ የሚገኙትን እና በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞች መልካምነት፣ ውበት እና ክብር ለማወቅ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህ የውይይት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ያለፍርድ በታማኝነት እና በግልጽነት ሃሳቡን ለማካፈል በቂ ደህንነት ያለበት ቦታ ይፈጥራል ብለዋል።
በዚህ ልምምድ መጨረሻ ላይ የህግ ታራሚዎቹም ሆኑ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች በማረሚያ ቤት ውስጥ ወይም በማህበረሰባቸው ውስጥ እንደዚህ አይነት ትክክለኛ ውይይቶችን ለማመቻቸት የሚያስፈልጉትን ክህሎቶች እና መሳሪያዎች እንደሚያገኙ ተገልጿል።
“ውይይቶችን በህብረት፡ የሰበካዎች ውይይት ለግንኙነት እና ለግንዛቤ” የሚለው የካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ትስስር አመቻች መመሪያ የስልጠናዎቹ አጋር ሆኖ እንደሚያገለግል የገለጹት ሲስተር ጃኔት፥ አንድ የህግ ታራሚ በተለይ የዚህ ሞዴል እምቅ ተጽእኖን በጣም እንደወደደው ጠቁመው፥ በጉዳዩ ዙሪያ የራሱን አስደናቂ ምልከታ በማሳተም፥ የመጽሃፉን ቅጂዎች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ማሰራጨት እንደቻለ አስታውሰዋል።
ሲኖዶስ ከፈውስ እና ህብረት ጋር ያለው ግንኙነት
የዚህ አካሄድ ስኬት ማረጋገጫ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሲስተር ጃኔት ተባባሪ አሰልጣኝ የሆኑት ኤሪክ አንደርሰን ሲሆን፥ ኤሪክ ከአምስት ዓመት በፊት ታስሮ በነበረበት ተቋም ውስጥ ስልጠናውን ለማመቻቸት እየረዳ እንደሚገኝ እና የእሱ ታሪክ፣ እሱን ለሚያውቁ እና የተሻለ ወደፊት ለሚፈልጉ በርካታ ወንዶች፣ ከእሱ ጋር በክበብ ውስጥ ለመሳተፍ ገና ዝግጁ ያልሆኑትን እንኳን ሳይቀር ታላቅ መነሳሳት እንደፈጠረ ተገልጿል።
ሲስተር ጃኔት የክበቡ ሂደት በተለይ በማረሚያ ቤት ውስጥ ሲሆን ከባህል ጋር በጽኑ የሚቃረን መሆኑን እንደሚገነዘቡ፥ ሆኖም ግን መለወጥ እንደሚችል ጠቁመው፥ ለህግ ታራሚዎች እና የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች አሰቃቂ ሁኔታን እና ጭንቀትን ለመቀነስ እንዲሁም የበለጠ ፍትሃዊ እና ውጤታማ ስርዓት ለመፍጠር ከዚህ በተሻለ ሁኔታ መሥራት እንደሚቻል፥ በዚህ ረገድ እነዚህን ስልጠናዎች ማዘጋጀት አንድ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።
መለያየት በተፈጠረባቸው ግንኙነቶች እና በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች መካከል ሁላችንም እንደዚህ አይነት ጥልቅ ማዳመጥን፣ እውነተኛ ግንኙነትን እና መሰረታዊ የሆነ እውነትን በመናገር ወደ ፈውስ እና ህብረት የሚወስድ መንገድ መገንባት የሚችል ውይይት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ከማረሚያ ቤት ጀርባም ይሁን ሰበካ አዳራሽ ውስጥ ይህ ተግባር እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን የተጠራንበት የሲኖዶሳዊ ሥራ መሆኑን የገለጹት ሲስተር ጃኔት፥ ሲኖዶሳዊነትም ሆነ የተሃድሶ ፍትህ በቁስሎች እና በመከፋፈል ውስጥ፣ በእስር ቤት ውስጥም ሆነ በውጪ አብሮ የመጓዝ ራዕይ እና ሂደትን ያጠቃልላል ብለዋል።
ይህ ሥራ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ከሚያረጋግጡ ነገሮች ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሰው ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ የእርምት መምሪያ ቢሮው ለስልጠናዎቻቸው ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግ ሲያውቁ የራሳቸውን ሃብት በማሰባሰብ ለሲስተር ጃኔት ከ1,000 ዶላር በላይ የሆነ ቼክ መስጠታቸው አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል።
የሲስተር ጃኔት የክበብ ሂደት አስተምህሮ እና በተሃድሶ ፍትህ ልምምዶች አማካኝነት የተገኘው ለውጥ ዛሬ ላይ ተጨባጭ የተስፋ ምልክት መሆኑ ተገልጿል።