የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት አባላት ር.ሊ.ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክልሉን እንዲጎበኙ በመጋበዝ ደብዳቤ ልከውላቸዋል የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት አባላት ር.ሊ.ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክልሉን እንዲጎበኙ በመጋበዝ ደብዳቤ ልከውላቸዋል  

የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት ለር.ሊ.ጳ. በፃፉት ደብዳቤ ብጹዕነታቸው እንዲጎበኟቸው ጠይቀዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት (CELAM) የቴሌግራም መልዕክት ከላኩ ከሁለት ቀናት በኋላ ብጹአን ጳጳሳቱ ለብጹእነታቸው ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ፥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳስነት መመረጣቸውን “የተስፋ ምልክት” ነው ሲሉ መልዕክት ልከውላቸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት (CELAM) 40ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አስመልክተው ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ደብዳቤ የፃፉ ሲሆን፥ በዚህም መልዕክታቸው 266ኛው የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፥ ብጹዕነታቸው ከሁለት ቀናት በፊት ለጉባኤው በላኩት የቴሌግራም መልእክት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

“እኛ በሪዮ ዲጄኔሮ የተሰበሰብን የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት 40ኛ መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ወንድማዊ ሰላምታ እና ልባዊ ምስጋናችንን ስናቀርብ ልባችን በደስታ በመሞላት ነው” ካሉ በኋላ፥ አገልግሎታችንን ለማበረታታት በላኩት መልእክት ወንድማዊ ሰላምታ እና ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መመረጥ የተስፋ ምልክት ነው
የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት ጳጳሳት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባስተላለፉት መልእክት በምርጫው ወቅት “የእግዚአብሔርን ተዓምራዊ ሥራ” እንዳስተዋሉ ገልጸው፥ በቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሥራዎች በመነሳሳት “የእርሳቸው መመረጥ የተስፋ ምልክት” እንደሆነ ገልጸዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ያላቸውን “ምሉዕ እና የልጅነት ግንኙነት” ማደሳቸውን በማረጋገጥ፥ እንደ ሚሲዮናዊ ቤተክርስቲያን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት በአጽንኦት ገልጸዋል።

አገልጋይ ቤተክርስቲያን የመሆንን ፈተና በትህትና እንደሚቀበሉ የገለጹት ብጹአን ጳጳሳቱ፥ “ማዕከሉን ከዳርቻው በማገናኘት የምታበለጽግ እና ቀለል ካለ ቦታ በእውነተኛነት ወንጌልን የምታውጅ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የመሆንን ፈተና በትህትና ተቀብለናል” ብለዋል።

ላቲን አሜሪካን እና ካሪቢያንን አይርሱ
የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት ብጹአን ጳጳሳት 40ኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እያደረጉ ባሉበት ወቅት፣ እንደ ጎረጎሳዊያኑ በ 1955 ዓ.ም. በሪዮ ዴ ጄኔሮ የተካሄደውን የላቲን አሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ 70ኛ ዓመት በማሰብ ያሳለፉ ሲሆን፥ በዚህም መሠረት ብጹአን ጳጳሳቱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ያላቸውን መሰጠት በድጋሚ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ብጹአን ጳጳሳቱ ክልሉ ውስጥ እየታየ ያለውን ፈታኝ የሶሺዮ-ፖለቲካዊ እውነታ በማስታወስ፥ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ብሎም ፍትሕን እና ሰላምን ለማበረታታት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትንቢታዊ ድምፅ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ጉባኤው በማከልም ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች የትጥቅ ግጭት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና የግዳጅ ስደት ሲገጥማቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አካባቢውን በጸሎቱ እንዲያስታውሱ ተማጽኗል።

ክብራቸው ተጠብቆ የሚኖሩበት መጪ ጊዜን የሚናፍቁ ስደተኞች፣ ማንነታቸውን እና መሬታቸውን የሚጠብቁ የአገሬው ተወላጆች፣ ሴቶች የጥቃት ሰለባ የማይሆኑባቸው፣ የተረሱ እና ለአደጋ የተጋለጡ ህጻናት የማይኖሩባት አከባቢ እንዲሆን ሁሉም የሚያጽናኑ እና ነጻ የሚያወጡ ቃላቶችን እና ምልክቶችን ከእኛ ይጠብቃሉ በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።

የብጹአን ጳጳሳቱ ደብዳቤ የቤተክርስቲያኗን ሚሲዮናዊ እና ሲኖዶሳዊ ተልእኮ ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፥ የላውዳቶ ሲ' ትሩፋትን በመከተል ፍጥረትን ሁሉ ለመንከባከብ ያላቸውን ቁርጠኝነት በአፅንዖት ገልጿል።

የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት ብጹአን ጳጳሳት በደብዳቤያቸው ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሚችሉት ጊዜ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያንን እንዲጎበኙ በመጋበዝ፥ “ህዝቦቻችን የእርሶን መገኘት እና ሐዋርያዊ በረከት ይናፍቃሉ” በማለት ደምድሟል።
 

02 Jun 2025, 14:39