በሮም የሚገኘው ጳጳሳዊ አቶኒያየም ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 22 የላውዳቶ ሲ የሽልማት ሥነ-ሥርዓትን አዘጋጅቷል በሮም የሚገኘው ጳጳሳዊ አቶኒያየም ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 22 የላውዳቶ ሲ የሽልማት ሥነ-ሥርዓትን አዘጋጅቷል   (CREDIT: OFM)

የቆስጠንጥንያው ክርስቲያናዊ አንድነት ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ የላውዳቶ ሲ ሽልማትን ተቀበሉ

የፍራንቺስካዊያን ገዳም ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ባዘጋጀው የሽልማት መድረክ የቆስጠንጥንያው ክርስቲያናዊ አቢያተ ክርስቲያናት ፓትርያርክ ብጹእ አቡነ በርተሌሜዎስ፣ የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ሊዮናርዶ ቦፍ፣ የፓን አማዞንያን ክርስቲያናዊ ትስስር (REPAM) እና የላውዳቶ ሲ ንቅናቄ የ2025 የላውዳቶ ሲ ሽልማትን መቀበላቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘው ጳጳሳዊ አንቶኒያነም ዩኒቨርሲቲ ይሄንን በዓመት አንዴ ለሁለት ሰዎች እና ለሁለት ድርጅቶች የክብር ሽልማት የሚሰጠውን የላውዳቶ ሲ ሽልማት ሥነ-ስርዓት ያዘጋጀ ሲሆን፥ የመጀመሪያውን ሽልማት የተቀበሉት የቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ ባሳዩት ልዩ የስነ-ምህዳር አመራር፣ በተለይም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ላይ ላሳዩት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሆነ ተነግሯል።

የእሳቸው መንፈሳዊ ተነሳሽነት በጉልህ የታየው ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ማዕከል አድርጎ የነበረ ሲሆን፥ እነዚህም የላውዳቶ ሲ ሃዋሪያዊ መልዕክት ላይ እና በየዓመቱ መስከረም 1 የሚከበረውን “ለፍጥረት እንክብካቤ የዓለም የጸሎት ቀን” ተቋም ውስጥ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንደሆነ ተገልጿል።

በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሁለቱም ጥረቶች ላይ ፓትሪያርኩ በሚያሳዩት ትጋት በመነሳት ብዙ ጊዜ “አረንጓዴው ፓትርያርክ” ብለው ይጠሯቸው እንደነበር አዘጋጆቹ አስታውሰዋል።

የቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተለሜዎስ ሽልማቱን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 1 የሚከበረውን የሥነ ፍጥረት የጸሎት ቀን ክብረ በዓልን መቀበሏ የክርስቲያናዊ አንድነት መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።

'በኦርቶዶክስ ትውፊት ውስጥ ላለው ጥልቅ ተምሳሌታዊ ትርጉሙ እና ጥንታዊ ሥረ መሠረቱ ምስጋና ይግባውና የዕለቱ ተወዳጅነት እየጨመረ መምጣቱ በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከሥርዓተ አምልኮ የቀን መቁጠሪያዎቻቸው ጋር እንዲያዋህዱት እያበረታታ ነው' ሲሉ የገለጹ ሲሆን፥ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ይህንን የክርስቲያናዊ አንድነት ልማት በማጎልበት እና በመደገፍ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው በበዓሉ ላይ ተነስቷል።

ፓትሪያርኩ አክለውም እውነተኛ የሰው ልጅ መለወጥ ከሌለ፥ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ ሊፈታ እንደማይችል ጠቅሰው፥ “አካባቢን የሚጎዳ ማንኛውም ሰብዓዊ ድርጊት እንደ ከባድ ኃጢአት መቆጠር አለበት” ሲሉ ጠንከር ያለ መግለጫ ሰጥተዋል።

ታሪካዊ ክብረ በዓል
ከፓትሪያርኩ በተጨማሪ የሥነ መለኮት ምሁሩ ሊዮናርዶ ቦፍ፣ የፓን-አማዞንያን ክርስቲያናዊ አንድነት ትስስር እና የላውዳቶ ሲ ንቅናቄ የተሸለሙበት ይህ ሥነ-ሥርዓት ከሦስት ጉልህ ክብረ በዓላት ጋር የተገናኘ ሲሆን፥ እነዚህም የፍጥረታት ዝማሬ 800 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል፣ የላውዳቶ ሲ 10 ኛ ዓመት እና የ 1,700 ኛው የኒቂያ ጉባኤ ክብረ በዓላት እንደሆኑ ተገልጿል።

የፍራንቺስካዊያን ገዳም የበላይ ሃላፊ አባ ማሲሞ ፉሳሬሊ በበኩላቸው “እነዚህ ሽልማቶች እውቅና ብቻ ሳይሆኑ ለሥነ-ምህዳር መለወጥ ሁለንተናዊ ጥሪ ምልክቶች ናቸው” ያሉ ሲሆን፥ አክለውም “እያንዳንዱ ይሄንን ሽልማት የሚቀበል ሰው የዚህ የጋራ ቁርጠኝነት ልዩ ገጽታን ይወክላል” ብለዋል።

'መለወጥ ያስፈልጋል' 
ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ሽልማቱ የመላው የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ “ይህንን ዕውቅና ማግኘታችን ታላቅ ክብር ነው” ብለዋል።

እ.አ.አ. በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የአየር ንብረት ችግርን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰው፥ ይህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተባብሶ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በ 1989 ዓ.ም. ፓትርያርክ ዲሚትሪዮስ የአየር ንብረትን አስመልክተው ያስተላለፉትን ሃዋሪያዊ መልዕክት በመጥቀስ፥ “በአሁኑ ወቅት ተፈጥሮ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ሳይሆን በተጠቃሚው ማህበረሰብ ዋነኛ ፍልስፍና የሚመራውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሰው ልጅ ጊዜያዊ ምኞት ለማርካት እንደሆነ በቦታው የነበሩትን አስታውሰዋል።

ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ እ.አ.አ. በ 1991 ዓ.ም. ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ ለክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ስለ አየር ንብረት ቀውስ እና ከማህበራዊ ፍትህ ጋር ስላለው ግንኙነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የዚህን ቀውስ መንፈሳዊ ገጽታ በማጉላት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፥ ጉዳዩ መንፈሳዊ እይታ እንዲያገኝ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ፓትሪያርኩ በመቀጠልም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጅ ከፍጥረት ጋር ያለውን ግንኙነት አስፈላጊነት በግልጽ ተረድታለች ያሉ ሲሆን፥ ሆኖም በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎችም ሆኑ አንዳንድ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት እራሳቸው በፈጣሪ፣ በፍጥረት እና በሁሉም ፍጥረታት መካከል ያለውን ውስጣዊ እና የማይበጠስ ትስስር መረዳት ተስኗቸዋል” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

ከጌቶች እስከ ወንድማማቾች/ እህትማማቾች
ሊዮናርዶ ቦፍ በበኩላቸው ሽልማቱን ሲቀበሉ እንደተናገሩት ሁሉም ሰው ስለ አየር ንብረት ለውጥ እንዲያስብበት በማሳሰብ፥ “ታላቁ ፈተና ተፈጥሮን እሰከመጨረሻው ድረስ ከሚበዘብዙ ‘የጌቶች እና አለቆች’ አስተሳሰብ ወጥቶ እርስ በርሳቸውን እና ፍጥረትን ሁሉ እንደ ዘመድ የሚያዩ ወንድሞች እና እህቶች መሸጋገር እንደሆነ ከገለጹ በኋላ፥ “እንክብካቤ ማለት ለሁሉም ፍጥረታት የሚዘረጋ የክርስቲያን እንክብካቤ” ማለት እንደሆነ አብራርተዋል።

በኢኳዶር የፑዮ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ራፋኤል ኮብ ጋርሺያ የፓን አማዞንያን ክርስቲያናዊ ትስስርን በመወከል ሽልማቱን የተቀበሉ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው የኢዮቤልዩ ዓመትን አስመልክተው እንደተናገሩት “ሁላችንም አምላክ ቃል ወደገባልን ገነት የተስፋ ነጋዲያን ሆነን እንጓዛለን” ብለዋል።

የላውዳቶ ሲ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ሎርና ጎልድ ሽልማቱን በድርጅታቸው ስም የተቀበሉ ሲሆን፥ “ሙሉ በሙሉ የህሊና ቀውስ የሆነበት የሥነ ምህዳር ለውጥ ላይ መሆናችንን አስታውሰው፥ “እንደ እምነት ሰዎች፣ ይህንን የጨለማ ጊዜ ወደ መለኮታዊ እድል ለመቀየር አንድ መሆን አለብን” በማለት አሳስበዋል።
 

03 Jun 2025, 14:50