ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካ ፎኮላሬ እንቅስቃሴ ጉባኤ አስተናገደች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተናገደችው የፓን አፍሪካ ዓለም አቀፍ የፎኮላሬ እንቅስቃሴ ጉባኤ ላይ ከ12 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 24 ብጹዓን ጳጳሳት እና ከጣሊያን የመጡ የማኅበሩ ዓለም አቀፍ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረመድኅን፥ የጅማ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በኢትዮጵያ የፎኮላሬ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ተጠሪ ለጉባኤው፥ “በስቃይ ውስጥ ተስፋ አለ” በማለት ባደረጉት ንግግር፥ እንቅስቃሴው ብዙ ክርስቲያኖች ተስፋ አጥተው በነበሩበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መመሥረቱን ገልጸዋል። በማከልም በጉባኤው ላይ የአንግሊካን ጳጳሳት መገኘታቸውን ተናግረው፥ “ይህም በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አብሮነት የሚያመላክት ትልቅ ምሳሌ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኪያራ ሉቢክ በተባለች ጣሊያናዊት ምእመን የተመሠረተው እንቅስቃሴው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ182 ሀገራት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትን፥ ጳጳሳትን፣ ካኅናትን፣ መነኮሳትን፣ ቤተሰቦችን፣ ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ ለጋራ ሰላም፣ ለአብሮነት፣ እና ለመንፈሳዊ መታደስ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ግለሰቦች ያቀፈ እንደሆነ ታውቋል።
ክርስቲያናዊ አንድነትን በማስተዋወቅ እና ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በተለይም ከእስልምና እና ከሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ጋር ውይይትን በማጎልበት የሚታወቀው ይህ እንቅስቃሴ፥ የጋራ መግባባትን፣ መከባበርን እና ፍቅርን በተግባር የሚገልጽ መሆኑ ተነግሯል። ተልዕኮው ድሆችን በተለይም በችግር ውስጥ ለወደቁ ወጣቶች እና ቤተሰቦች ርህራሄን በማድረግ፣ ተስፋን በመስጠት እና በማበረታታት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
በሕይወት ቃል ላይ ማስተንተን
ይህ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከ30 ዓመታት በፊት እንደ ነበር እና ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁትም አባ ክላውዲዮ፥ የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ማኅበር ካኅን እንደ ነበሩ፥ ብጹዕ አቡነ ልሳኑ ክርስቶስ ማቴዎስ፥ የባሕር ዳር-ደሴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አስረድተዋል።
የፎኮላሬ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የዘርዓ ክኅነት ተማሪ እንደ ነበሩ የሚያታወሱት ብጹዕ አቡነ ልሳኑ ክርስቶስ ማቴዎስ፥ ለወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎትን በሚያቀርቡበት ወቅት፥ “የሕይወት ቃል” በሚል ርዕሥ የሚቀርቡ የፎኮላሬ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ተከታታይ አስተንትኖዎች፥ “ፍቅርና ሰላም” በተሰኘ የቤተ ክርስቲያኒቱ ብቸኛ ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ እየታተመ ይወጣ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
በትምህርተ ክርስቶስ ላይ የተመሠረቱ የአስተንትኖ ጽሑፎቹ ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን አዳጊ ሕፃናት በእምነት ተመርተው እንዲያድጉ ለማስተማር አስፈላጊ መሣሪያ ሆነው ማገልገላቸውን አስረድተዋል።
“የተናቀው ኢየሱስ” በሚል ርዕሥ ይቀርብ የነበረው መልዕክት፥ በመንፈሳዊ ጉዞአቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ልሳኑ ክርስቶስ ማቴዎስ፥ ቅዱስ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ ሕይወት ለመምራት የነበራቸውን ቁርጠኝነት እንዳገዘው አስረድተዋል።
ብጹዕ አቡነ ልሳኑ ክርስቶስ ማቴዎስ፥ በአዲስ አበባ የመድኃኔዓለም ካቶሊካዊ ቁምስና ወጣቶች በፍቅር እና በአገልግሎት ላሳዩት ብርቱ ተሳትፎ አመስግነው፥ ተግባሮቻቸው የፎኮላሬ እንቅስቃሴ የአንድነት፣ የበጎ አድራጎት እና የንቁ ደቀ መዝሙርነት ዋና እሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአብሮነት፣ በፍቅር እና በሰብ ዓዊ ክብር ላይ የተመሠረተ መልዕክት
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል፥ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፥ በዓለማቀፉ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለጉባኤው ተሳታፊዎች ልባዊ ሰላምታቸውን እና አባታዊ ቡራኬያቸውን አቅርበዋል። ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግርም፥ የፎኮላሬ እንቅስቃሴ በተለያዩ ባሕሎች እና እምነቶች ለበለፀገች የአፍሪካ አኅጉር ሕዝቦች ያለውን ፋይዳ አፅንዖት ሰጥተው፥ በዛሬው ዓለም ውስጥ አንድነትን እና በሰላም አብሮ መኖርን ለማጎልበት እንዲህ ያሉ እሴቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አስምረውበታል።
ሞንሲኞር ማሲሞ ካተሪን፥ በአዲስ አበባ የሐዋርያዊ መንበር ዋና ጸሐፊ በጉባኤው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፎኮላሬ እንቅስቃሴ ጋር የነበራቸውን ጠንካራ ግንኙነትን እና መተሳሰብን አስታውሰው፥ ቅዱስነታቸው ለእንቅስቃሴው እና ለአባላቱ ከላኳቸው በርካታ መልዕክቶች መካከል፥ የእንቅስቃሴው ተልዕኮ ቀጣይነት እንዲኖረው ያደረጉትን ድጋፍ እና ማበረታቻ አስታውሰዋል።
ክቡር አባ ከተማ አስፋው፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተከናወኑ ሥራዎችን በማስመልከት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
የፎኮላሬ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚገኝ በቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና እየተመራ በአገሪቱ ባሉ ቋሚ አመራሮች እና አባላት የሚደገፍ መሆኑን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት የማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ ሃላፊ ወ/ት ቤዛዊት አሰፋ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ከላከችው ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።