የኬንያ ካቶሊክ ጳጳሳት በሀገሪቱ ውጥረት እየጨመረ ባለበት ወቅት ዜጎች እንዲረጋጉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የኬንያ ብጹዓን ጳጳሳት ማክሰኞ ሰኔ 17/2017 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፥ በሀገሪቱ ያለው የሰው ልጅ ሕይወት እጅግ አሳሳቢ መሆኑ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው በመግለጫቸው ተናግረዋል።
የብጹዓን ጳጳሳቱ መግለጫው ይፋ የሆነው፥ የፋይናንስ ሕግን በመቃወም ባለፈው ዓመት በተደረጉ ሰልፎች የተገደሉትን ለማስታወስ ለረቡዕ ሰኔ 18/2017 ዓ. ም. የተጠራ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ እንደ ነበር ታውቋል።
ፊደስ የተሰኘ የቫቲካን ዜና ወኪል እንደዘገበው፥ የብጹዓን ጳጳሳቱ መግለጫ በሃገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምስጢራዊ መሰወር፣ የፍርድ ቤት ግድያዎች እና በኃይል የማስፈራራት ክስተቶች መደጋገማቸው ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጿል።
“ስሞች ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆች ናቸው!”
ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው የተገደሉትን ወይም የተሰወሩትን ሰዎች ስም በማስታወስ፥ እነዚህ ስሞች ብቻ ሳይሆኑ ጥበቃ እና ፍትህ የሚገባቸው ወንድሞች፣ እህቶች፣ ካህናት፣ ወንድ እና ሴት ልጆች እንዲሁም ጓደኞች ናቸው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለይም በቅርቡ በቦኒፌስ ካሪዩኪ ላይ የተፈፀመውን ግድያ በመግለጫቸው ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ “ተቃዋሚ ሰልፈኛው በፖሊስ መኮንን በቅርብ ርቀት በጥይት ተመትቶ ወድቋል” ብለዋል።
የ21 ዓመቱ ወጣት የተገደለው በደኅንነት ክፍል ውስጥ ለነበረው ጦማሪው አልበርት ኦጃዋንግ ሞት ፍትኅን በሚጠይቅበት ወቅት ነው።
መግለጫው በመቀጠልም፥ “የደኅንነት መኮንኖች ሕዝቡን ለመጠበቅ እንጂ ለመጉዳት መሐላ አልፈጸሙም” ሲል አትቷል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው፥ “በገጠማቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር መካከል ሕጋዊ ጥያቄዎቻቸውን እያቀረቡ ያሉ “ትውልደ ዜድ” የሚባሉ ወጣቶች ተቃውሞን ባለሥልጣናቱ እንዲያዳምጡ” በማለት ጠይቀዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም፥ እነዚህን ችግሮች የመፍታት ሕጋዊነት እና አሳሳቢነት በመገንዘብ፥ ወጣቶች ወደ ሁከት እና ብጥብጥ ውስጥ ሳዳይገቡ ነገር ግን ሰላማዊ ሠልፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ሰልፈኞቹ “ሰላማዊ፣ ቅን እና ደፋር ይሁኑ” በማለት ያሳሰቡት የኬንያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፥ ቤተ ክርስቲያን እንደምትወዳቸው እና እንደምታስብላቸው ገልጸው፥ “ለመጥፎ ዓላማ ሊያደርጉህ ከሚፈልጉ ተጠንቀቁ” ሲሉ አሳስበዋቸዋል።