የማርያም እህቶች በድህነት ምክንያት ትምህርት አቋርጠው ከነበሩ  የኪሳራዌ ልጃገረዶች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር እየተመገቡ የማርያም እህቶች በድህነት ምክንያት ትምህርት አቋርጠው ከነበሩ የኪሳራዌ ልጃገረዶች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር እየተመገቡ  

በታንዛኒያ የሚገኙ የማርያም እህቶች ማህበር ገዳማዊያት በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የተቸገሩ ወጣቶችን እየረዱ እንደሆነ ተነገረ

የገንዘብ ችግር በርካታ ህፃናትና ወጣቶችን ከትምህርት ገበታ ውጪ በሚያደርግባት ታንዛኒያ፥ የማርያም እህቶች ማህበር ነፃ፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው የመደበኛ ትምህርት እና የሙያ ስልጠና በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ምንም እንኳን ታንዛኒያ በምስራቅ አፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ብትሆንም አሁንም ድረስ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ሀገር ስትሆን፥ በርካታ ዜጎቿ የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚገጥሟቸው እና አብዛኛው የሃገሪቱ ተራ ቤተሰቦች ሁሉን አቀፍ ትምህርት ማግኘት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

እ.አ.አ. በ 1964 ዓ.ም. በሞንሲኞር አሎይሲየስ ሽዋርትዝ የተመሰረተው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቸገሩ ህጻናትን ለመርዳት ባላቸው ቁርጠኝነት የሚታወቁት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማርያም እህቶች ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ጉባኤ በችግር አረንቋ ውስጥ ከሚገኙ የታንዛኒያ ህጻናት ጋር የመስራት ተልእኮውን በመውሰድ ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የማርያም እህቶች ለእነዚህ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እና ለወደፊት ነባራዊ ፈተናዎች የሚያዘጋጃቸውን እድሎች ለመስጠት ቆርጠው የተነሱ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ በ 2011 ዓ.ም. በዳሬሰላም ሃገረ ስብከት ሥር በምትገኘው ኪሳራዌ ውስጥ በአብዛኛው ከድሃ ቤተሰቦች የተውጣጡ ልጃገረዶች የሚማሩበት ትምህርት ቤት በመክፈት ሥራ እንደጀመሩ ተገልጿል።

መጀመሪያ ላይ መሰረታዊ ትምህርቶችን ለመስጠት በማለም ሥራ የጀመረው ትምህርት ቤቱ፥ በ 2016 ዓ.ም. የማስፋፊያ ሥራዎችን በማድረግ እና የላቀ ደረጃ ያላቸውን ትምህርቶችን በማካተት፥ በአሁኑ ወቅት በዚህ ተቋም 1,029 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ሴት ተማሪዎቹ መደበኛ የአካዳሚክ ትምህርቶችን ጨምሮ መንግስት ከሚያወጣው ደረጃዎች ጋር የተጣጣመ አጠቃላይ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።

ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ጓደኞች ማፍራት፣ ስፖርት መጫወት እና አዳዲስ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን የሚያገኙበት እና ለወደፊት የሥራ ህይወት ተግባራዊ ክህሎቶችን የሚያገኙበት መደበኛ የልጅነት ጊዜያቸውን እንዲለማመዱ የሚያስችላቸው ምቹ ከባቢን እንደሚፈጥርላቸው ጭምር ተገልጿል።

ኪሉቪያ የህፃናት ማቆያ እና ማሰልጠኛ ማዕከል
በ 2016 ዓ.ም. የማርያም እህቶች ለ90 ታዳጊ ሕጻናት የመዋዕለ ሕፃናት እንክብካቤ የሚያገኙበት እና በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ያቋረጡ 110 ወጣት ሴቶች የሙያ ብቃት ሥልጠና የሚወስዱበት የኪሉቪያ የህፃናት ማቆያ እና ማሰልጠኛ ማዕከል የከፈቱ ሲሆን፥ ይህ ተቋም ወጣት ሴቶችን ለማብቃት እና ህፃናት ልጆችን ደግሞ ለቀጣይ ትምህርት ለማዘጋጀት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።

የዶዶማ ልጆች ከተማ
በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ገዳማዊያቱ በዶዶማ ከተማ ከድሃ ቤተሰብ የመጡ ወንድ ልጆችን የሚንከባከብ አዲስ የማደሪያ እና ጂምናዚየም ማዕከል አስመርቀው ሥራ ያስጀመሩ ሲሆን፥ በማስመረቂያ መርሃ ግብሩ ላይ ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ የታንዛኒያ የትምህርት ሚኒስትር፣ የዶዶማ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቢቱስ ኪንያያ፣ የታቦራ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፕሮታሴ ሩጋምብዋ እንዲሁም የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ተገኝተዋል።

ትምህርት ቤቱ ጥራት ያለው የትምህርት እና የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፥ ተማሪዎቹ ከማዕከሉ ተመርቀው ሲወጡ ትክክለኛ የሥራ እድል እንዲያገኙ ማዘጋጀትን ግብ ያደረገ በቴክኖሎጂ እና በዳቦ አዘገጃጀት ክህሎት የሚያስታጥቅ የኮምፒውተር ላብራቶሪ እና ዳቦ መጋገሪያ ቤት እንዳለው ጭምር ተብራርቷል።

ትብብር እና ተደራሽነ
የማርያም እህቶች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ሙሉ ድጋፍ ከሚያገኙበት ከታንዛኒያ የትምህርት፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት የሚሰሩ ሲሆን፥ ፕሮግራሞቻቸው በአሁኑ ጊዜ በመላው ታንዛኒያ 1,583 ህጻናትን እና ወጣት ሴቶችን በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በኪሳራዌ ከሚገኘው የሴቶች ትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ውስጥ አንዷ የሆኑት ሲስተር ሜሪ ጄን (ታሊንስ) ሴቶችን በትምህርት ማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ በአጽንኦት በመግለጽ፥ እንደ ታንዛኒያ ባሉ ባህላዊ ማህበረሰቦች ውስጥ ሴቶች አሁንም ድረስ ለቤት ውስጥ ሚና ብቻ እንደሚመረጡ፣ አልፎ ተርፎም ያለእድሜ ጋብቻን ጨምሮ የተለያዩ እገዳዎች እንደሚገጥሟቸው አስረድተዋል።

ሴት ልጆችን ማስተማር ጥቅሙ ሴቶቹ በህብረተሰቡ ውስጥ በሚከናወኑ በዬትኛውም ተግባራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ፣ የራሳቸው ገቢ እንዲያገኙ እና ቤተሰቦቻቸውን ከድህነት ለማውጣት እንዲችሉ ለማድረግ ወሳኝ እንደሆነም የተገለጸ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ ተማሪዎቹን ወደ ሥራ ዓለም እንዲሰማሩ የተለያዩ ክህሎቶችን በማስታጠቅ እና ከድህነት አዙሪት የማላቀቅ ዓላማ አንግበው ጥራት ያለው የትምህርት እና የሙያ ስልጠና ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ለገዳማዊያቱ ጥረት የወላጆች ተሳትፎ ቁልፍ ተግባር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ ዓመታዊ የወላጅ ጉብኝቶችን በማመቻቸት፣ የተለያዩ ቤተሰቦችን እንደገና የማገናኘት ተግባራትን በማከናወን እንዲሁም የማህበረሰብ ተሳትፎን በማበረታታት በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ሲስተር ሜሪ ገልጸዋል።

የማሪያም እህቶች ጉባኤ አጠቃላይ አካሄድ የሚያተኩረው ለተማሪዎቹ መሰረታዊ ትምህርት መስጠት ላይ እንደሆነ እንዲሁም እንደ ምግብ እና አልባሳትን የመሳሰሉ አስፈላጊ ፍላጎቶችን በሟሟላት ልጆቹ ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ማረጋገጥ እንደሆነ ተብራርቷል።

25 Jun 2025, 14:07