የሐምሌ 20/2017 ዓ.ም 15ኛው ሣምንት እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ምንባባት
1. ኦ.ዘዳግም 30፡10-14
2. መዝ 68
3. ቆላስያስ 1፡15-20
4. ሉቃስ 10፡25-37
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ደጉ ሳምራዊ
እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው።ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?” ሲል መለሰለት።ሰውየውም መልሶ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው። ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ”አለው። ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ አለፈ። ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ቀርቦም ቊስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጪ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው። “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የሚናገረን፣ በሉቃ. 10፣25-37 እንደተጻፈው የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ያቀርብልናል። በዚህ የወንጌል ክፍል አንድ ሕግ አዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው። ኢየሱስም፣ በሕግ የተጻፈው ምን እንደሆነ እንዲያነብ በማሳሰብ እንዲህ ሲል መለሰለት። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” አለው (ሉቃ. 10፣27)። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው በሰዎች መካከል የተለያዩ ትርጉሞች ይሰጠው ነበር እና የሕግ አዋቂው መልሶ ኢየሱስን “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በምሳሌ መለሰለት። ምሳሌውም በሉቃ. 10,29 ላይ የተገለጸ ሲሆን ይህን ድንቅ ምሳሌ ከሉቃ. 10, ከቁ. ጀምሮ ያለውን እንድታነቡ አደራ እላለሁ። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ በምዕራፍ 10 ላይ የተገለጸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ምሳሌያዊ ንግግር በሌላ ሥፍራም ከተጠቀሱት ድንቅ ምሳሌዎች መካከል አንዱ እና የክርስትና ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን በምን መልኩ መምራት እንዳለበት የሚያመለክት ምሳሌ ነው። ምሳሌውንም ስላቀረበልን ወንጌላዊውን ቅዱስ ሉቃስ እናመሰግነዋለን።
የዚህ ወንጌል ክፍል ዋና ተዋናይ፣ በዘራፊዎች ተደብድቦ የወደቀውን አንድ ሰው ሊረዳ የቀረበ ደጉ ሳምራዊ ነው። አይሁዳዊያን ራሳቸውን በእግዚአብሔር የተመረጡ አድርገው ስለሚቆጥሩ ሳምራውያንን እንደ ባዕድ አድርገው እንደሚቆጥሯቸው እናውቃለን። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሳምራዊ የታሪኩ ቀዳሚ ተዋናይ አድርጎ ሲያቀርበው ያለ ምክንያት አልነበረም። ሳምራዊውን ያቀረበበት ምክንያት፣ እውነተኛ አምላካቸውን ባያዉቁትም፣ ወደ ምኩራብም ገብተው የማያውቁ ቢሆንም የተቸገረን፣ የወደቀን በማየት የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ፣ መልካምን ሠርተው በማለፍ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖሩ መሆናቸውን ለማስረዳት እና ሳምራዊያንን እንደ ባዕዳን ለሚቆጥሩት አይሁዳዊያን ትምህርት እንዲሆናቸው ስለፈለገ ነው።
ሳምራዊው ባለፈበት ተመሳሳይ መንገድ፣ ከእርሱ ትንሽ ቀደም ብሎ አንድ ካህንና ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ አልፈው ነበር። ነገር ግን የወደቀውን ሰው እያዩ ገለል ብለው አለፉት። ምናልባትም ደሙ እንዳያበላሻቸው ፈርተው ይሆናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚፈልጉ ከሆነ “በሌሎች ሰዎች ደም እንዳትበከሉ ተጠንቀቁ” የሚል ትዕዛዝ አላቸውና።
ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ምንም እምነት የሌለውን ሳምራዊ ሰው የመልካም ሥራ ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል። እኛም ብንሆን በአካባቢያችን ወይም በማሕበረሰባችን መካከል እምነት የሌላቸው፣ ነገር ግን ለሌሎች መልካም ሥራን በማበርከት የሚታወቁት ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ኢየሱስም እምነት የሌለውን ሰው ምሳሌ እንዲሆነን መርጧል። ይህም ሰው ወንድሙን በሙሉ ልቡ እና በሙሉ ሃይሉ እንደራሱ አድርጎ በመውደድ፣ ምንም እንኳ እግዚአብሔርን ባያውቀውም ፈቃዱን ፈጽሞ ተገኝቷል። ይህን በማድረጉ ምክንያት ትክክለኛ መንፈሳዊነትን እና እውነተኛ ሰብዓዊነትን በተግባር አሳይቷል።
ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ኢየሱስ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው” ብሎት ወደጠየቀው ወደ ሕግ አዋቂው ሰው ተመልሶ “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ብሎ ጠየቀው። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕግ አዋቂውን ጥያቄ እና የሁላችንም አስተሳሰብ ጭብጥ በመለወጥ፣ ባልንጀራችን በጎ ሥራችንን የምናበረክትለት ሰው ሳይሆን፣ በእርግጥም ባልንጀራዉ ማን መሆኑን ለይቶ ማወቅ የሚችለው ያ ጉዳት የደረሰበት ሰው መሆኑን እንድናስተውል ስለ ፈለገ ነው። በሉቃ. 10. 37 ላይም እንደተገለጸው ባልንጀራው ያ የራራለት ሰው መሆኑን ኢየሱስ ለሕግ ዐዋቂው በሰጠው መልስ አረጋግጧል። መልሱም “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” የሚል ነበር፣ ።
ርህራሄን ማሳየት መቻል የክርስትና ሕይወታችን መሠረታዊ ጉዳይ ነው። እርዳታን ለሚፈልግ ሰው የማትራራ ከሆነ፣ ልብህ የማይጨነቅ ከሆነ አንድ ያልተስተካከለ ነገር አለ ማለት ነው። ልብ ልንል ይገባል። ራሳችንን ለራስ ወዳድነት አሳልፈን መስጠት የለብንም። ርሕራሄን ማሳየት መቻል የአንድ ክርስቲያን የማንነት መግለጫ፣ በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መገለጫ ነው። የእግዚአብሔር አብ ርህራሄ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦልን እንመለከታለን። አንድ ሰው መንገድ ላይ ወድቆ ካገኘሄው፣ ምናልባት ስለ ጠጣ ሰክሮ ይሆናል ከማለት ይልቅ በእርግጥ ብዙ ከመጠጣት ሰክሮ ከሆነ፣ ወይም ልቤ ለተቸገር ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ደንድኖ ወይም ቀዝቅዞ ከሆነ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። የዚህ ጥያቄ መደምደሚያ ምህረትን ማድረግ ለሰው ልጆች የሚደረግ የእውነተኛ ፍቅር መገለጫ መሆኑን ያመለክታል። ምሕረትን በማድረግ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እና የእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር እንዲገለጥ እናደርጋለን። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ (ሉቃ. ምዕ. 6.36)። እግዚአብሔር አባታችን መሐሪ ነው፣ ምክንያቱም ርህሩህ ነውና። ርህራሄውንም በችግራችን ጊዜ ወደ እኛ በመቅረብ፣ ለበደላችን፣ ለመጥፎ ሥራዎቻችን እና አስተሳሰቦቻችን ምሕረትን በማድረግ ለእኛ ያለን ርህራሄ በተግባር ማሳየት ይችላል።
የባልንጀራ ፍቅር በጥሩ ምግባርና በተግባር መታየት አለበት፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ ለባልንጀራችን ዘወትር በተለይ በችግሩ እንድንረዳው ያስገድደናል፡፡ ባልንጀራችንን እንዴት አድርገን ልንወደው እንደሚገባን እንድናውቅ ይህንን የኢየሱስ ምሳሌ እናንብብ፡፡
«አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ እያሪኮ ሲወርድ በመንገድ ላይ ወንበዴዎች አግኝተው ልብሱን ገፈፉት፤ ከደበደቡትም በኋላ ሊሞት ሲያጣጥር ሳለ ጥለውት ሄዱ፡፡ አንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲሄድ ተደብድቦ የተጣለውን ሰውዬ ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ፡፡ እንዲሁም ከካህናት ወገን የሆነ አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ እርሱም ሰውየውን ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ፡፡ አንድ ሳምራዊ ግን በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውዬው ደርሶ ባየውም ጊዜ ራራለት፣ ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሉ ላይ አፈሰሰ፣ በጨርቅም ጠምጥሞ አሰረለት፡፡ ከዚያ በኋላ በገዛ ራሱ አህያ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፡፡ ከዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባክበው፡፡ በማግሥቱ ሁለት ብር አውጥቶ ለእንግዳ አሳዳሪው ባለቤት ሰጠና ይህን ሰው በጥንቃቄ አስታምልኝ፣ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግ በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ” (ሉቃ. 10፣30-38) አለው፡፡
ይህንን ሌቦችና ወንበዴዎች የደበደቡት ሰው በተለይ ካህኑና ሌዋዊ ሊረዱት ይገባ ነበር፣ ምክንያቱም እነዚህ የካህናት ወገን የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሕግን ሁሉ የሚያውቁ የሕግ አክብሮት ጥሩ አብነት እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸው የነበሩ ሲሆን ግን የሚገባቸውን አልፈጸሙም፡፡ ተራ የሆነው ሳምራዊ ግን ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገን ውደድ የሚለውን ትዕዛዝ ሲፈጽም ተገኘ፡፡ ባልንጀራው ተቸግሮ ሲያይ ራርቶለት ወደ እርሱ ቀርቦ እንደሚቻለው እንደ አቅሙ አገዘውና ብዙ በመንከባከብ ረዳው፡፡
እነዚያ ሁለቱ የፊተኞቹ ካህኑና ሌዋዊው ያን ምስኪን የተገፋ ሰው እያዩት የሄዱ ባልንጀራቸውን የሚረሱ ዘወር ብለው የማይመለከቱ ናቸው፡፡ በራሳቸው ፍቅር ተስበው ባልንጀራቸውን በመከራ ላይ እየረገጡት ያልፋሉ፡፡ ሰው እነርሱ በጭንቀት ላይ ሲወድቁ እንዲደርስላቸው ይፈልጋሉ፣ እነርሱ ግን ሰውን በችግሩ ወቅት ለመረዳት አይፈልጉም፡፡ ሳምራዊው ግን እውነተኛ የባልንጀራ ፍቅር ያላቸው የደጋግ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልንጀራቸውን የቅድስት ሥላሴ አምሳል መሆኑን ስለሚረዱ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚለውን ትዕዛዝ በንግግርና በተግባር ይፈጽሙታል፡፡ ባልንጀራቸውን ይወዱታል፣ እንደራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው አብልጠው ያስቡለታል፣ ስለ እርሱም ይሰዋሉ፡፡
ሌዋዊውና ካህኑ እንዳደረጉት ባልንጀራችንን በመከራው ጊዜ ረግጠነው አንለፈ፣ አንጨክንበት፣ የሳምራዊውን ፈለግ እንከተል፡፡ ባልንጀራችንን እንውደደው፡፡ ሁልጊዜ በይበልጥ ግን በችግር ላይ ሲወድቅ ዕርዳታ እናድርግለት፡፡
ከሁሉም በላይ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር ያለን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያለን ፍቅር እውነተኛ እንዲሆን፣ የርህራሄ ልብ እንዲኖረን እና በርህራሄ እንድናድግ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋዋን ትስጠን”።