የአመስያ አባል ሀገራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደትን መቀነስ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ   የአመስያ አባል ሀገራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደትን መቀነስ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ  

የአመስያ አባል ሀገራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደትን መቀነስ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተናጋጅነት የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ ህብረት (AMECEA) አባል ሀገራት የተሳተፉበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ስደትን ለመቀነስ በመደረግ ላይ ያለውን የጋራ ጥረት ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ከሐምሌ 14 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው የቅዱስ ዶን ቦስኮ የሱባኤ ማዕከል ተካሂዷል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተናጋጅነት የተካሄደው ይህ ስልጠና እየተባባሰ ያለውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የሚደረገውን ትግል የአባል ሀገራቱ የመንፈሳዊ አጀንዳ አካል ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው በሀገራቸው ውስጥ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በጥልቀት በመመርመር እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያለውን ሰፊ እይታ መቃኘት መቻላቸው ተገልጿል። ተሳታፊዎቹ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮችን በመለየት እና በተግባር የሚታዩ ጣልቃገብነቶች በመገምገም እንዲሁም ወደፊት ለመራመድ የሚያስችሉ እና መሻሻል የሚገባቸውን ምክረ ሃሳቦች በማቅረብ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ካህናት እና ምዕመናን ወክለው የመጡበትን ሃገር የስደት እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘የተስፋው ነጋዲያን’ ብለው ያወጁት የ2025 ዓመት የተስፋ ኢዩቤሊዩ ዓመት በመሆኑ በስደት እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚጠቁ ወጣቶችን መታደግ እና ትምህርት መስጠት የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት አድርገዋል።  

የአመስያ ሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ጳውሎስ የችግሩን አጣዳፊነት አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፣ “ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አሁን ላይ በተለይ በአመስያ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ሆኗል” ያሉ ሲሆን፥ ይህ ቀውስ በዘላቂነት የሚያደርሰውን ጉዳት ለጳጳሳት ጉባኤዎች እና ለአብያተ ክርስቲያናት ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፥ ብዙ አፍሪካውያን ወጣቶች በዚህ ጉዳይ እየተሰቃዩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ተሳታፊዎቹ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ለስደተኞች ሐዋርያዊ አገልግሎት በመስጠት ረገድ አቅምን ማጎልበት፣ በስደተኞች ማዕከላት ተወካይ ካህናት መሾምና በጳጳሳት ጉባኤዎች ውስጥ ዘርፉን የሚያስተባብሩ ክፍሎች እንዲቋቋሙ ጠይቀዋል።

“በምስራቅ አፍሪካ ይህ ትልቅ ፈተና ነው ያሉት” ክቡር አባ ጳውሎስ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዘመናዊ የባርነት እና የቅኝ ግዛት መንገድ ነው” ማለታቸውን በማስታወስ፣ ስደተኞችን ለአገራት ስጋት በማድረግ መፍራት እንደማይገባ አሳስበው፥ እነዚህ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ዋጋ እና መክሊት እንዳላቸው፣ አብርሃምን የጎበኘው እንግዳ ወደ ቤቱ በረከትን እንዳመጣ ሁሉ ስደተኞችም ለሀገራት የሚያመጡትን ዋጋ እና መክሊት መመልከት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

‘በርካታ ሰዎች የተሻለ ዕድል ፍለጋ በሚሰደዱበት ወቅት በመንገድ ላይ ህይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲያጡ ተመልክተናል’ ያሉት ክቡር አባ ጳውሎስ፣ የአውደ ጥናቱ መሪ ሃሳብ ከኢዮቤልዩ "የተስፋ ዓመት" ጋር በማያያዝ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. የስደተኞች ኢዮቤልዩ እንደሚከበር አስታውሰው ይህ መሪ ሃሳብ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት እድል እንደሚፈጥር አጽንኦት በመስጠት፥ ሁሉም በየደረጃው በትብብር ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት መስራት ይኖርበታል በማለት አሳስበዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ እና በሥራ ማጣት ምክንያት በርካታ ወጣቶች ከሃገራቸው እንደሚሰደዱ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህም ስደተኛ ተቀባይ ሃገራት በበጎ የሚመለከቱት ጉዳይ አለመሆኑ አሳሳቢ እንደሆነም ጭምር ተመላክቷል።

 ከዚህም ባለፈ ሦስት ቀናትን በቆየው በዚህ የውይይት መድረክ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና መንስኤዎች፣ ቤተክርስቲያኗ ችግሩን ለመገንዘብ እና ለመከላከል የምትጠቀምባቸውን መሳሪያዎች መለየት እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች እና የድርጊት መርሃ ግብሮች የተቀመጡበት ውይይት እንደነበር አባ ጳውሎስ አብራርተዋል።

በውይይቱ ወቅት ዘርፉን በማስመልከት የወጡ ፖሊሲዎች እና ማዕቀፎች በሀገር አቀፍ፣ በክልላዊ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዳሰሱ ሲሆን፥ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ውጤታማ እርምጃዎችን የሚያደናቅፉ ወቅታዊ ክፍተቶችን እና የተበታተኑ አሠራሮችን መፍታት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት የሥልጠናው ተሳታፊዎች፥ ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መስፋፋት መንስኤ የሆኑትን ምክንያቶች በጥልቀት ተወያይተው የተሻሻለ የትብብር አማራጮች ቀርበውበታል።

ከዚህም ባሻገር በሥልጠናው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ዘርፈ ብዙ አካሄዶችን በማጉላት በርካታ ቁልፍ የውሳኔ ሃሳቦች የቀረቡበት ሲሆን፥ በስደት እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሃዋሪያዊ እና ማህበራዊ አስተምህሮ ምን ይላል በሚለው ሃሳብ ላይ ውይይት ያደረጉት ተሳታፊዎቹ፥ በውይይታቸው ወቅት ያሰባሰቡትን አጀንዳዎች በማጠናከር ለብጹአን ጳጳሳት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ጥቅምት ወር ላይ የስደተኞች እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚመለከት ኢዩቤልዩ እንደሚከበር ያስታወሱት አባ ጳውሎስ፥ በዚህም ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለስደት እና የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ተስፋን የሚሰጥ እንዲሁም ስደተኞችን የሚቀበሉ ሃገራትን የሚያበረታታ የኢዩቤልዩ የተስፋ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ ህብረት ቡድን አባላት በቆይታቸው ወቅት ከብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ከብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና ከክቡር አባ ከተማ አስፋው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ እንዲሁም ከጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ጋር ጉብኝት እና ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት እና ሰብአዊ ክብርን ለማጎልበት ብሎም በክልሉ በሚደረጉ ጥረቶች መካከል ትብብርን ለመፍጠር ያለመው የውውይት መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ ሃገራት የስደት፣ ፍትህ እና ሰላም እንዲሁም ከካሪታስ ቢሮዎች የተውጣጡ አባላት ተገኝተዋል።

 

 

28 Jul 2025, 14:41