የደቡብ አፍሪካ ወጣቶችን ተስፋ ወደ ኢዮቤልዩ ዓመት ማምጣት
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከተሳታፊ ወጣቶቹ አንዷ የሆነችው ግላድነስ ማሹምቡካ ሎቢና ስለ ጉዞ ዝግጅቱ ስትናገር “ቦርሳችንን አዘጋጅተን ጉዞውን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው” በማለት በደስታ ስሜቷን የገለጸች ሲሆን፥ ወደ ጣሊያን የሚጓዙበት ቀን ከመድረሱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለቫቲካን ዜና ስትናገር የደስታ ስሜቷ በስልክ ውስጥ ያስተጋባ ነበር።
የፕሪቶሪያ ሀገረ ስብከት የወጣቶች ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆነችው የ35 ዓመቷ ወጣት ከሃምሌ 21 – 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በሮም በሚካሄደው የወጣቶች ኢዮቤልዩ ላይ ለመታደም ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና እና እስዋቲኒ ከሚመጡት 160 ከሚጠጉ ወጣቶች መካከል አንዷ ስትሆን፥ በዚህ ዝግጅት ላይ ለመታደም በጉጉት እየጠበቀች እንደምትገኝ ገልፃለች።
ምንም እንኳን 70 በመቶ ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን ከ 30 ዓመት በታች በመሆናቸው አፍሪካን በዓለም ላይ ወጣቶች የሚበዙባት አህጉር ቢያደርጋትም፥ በርካታ ወጣቶች ወደ ሮም የሚደረገውን መንፈሳዊ ንግደት ለማሳካት የገንዘብ ችግር እንዳጋጠማቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህም ሆኖ ሀገረ ስብከቶቹ ይህንን ቅዱስ ዓመት በአገር ውስጥ እንዲለማመዱ ብዙ ተግባራትን እና ዝግጅቶችን ሲያዘጋጁ የቆዩ ሲሆን፥ ወደ ሮም ተሳክቶላቸው የሚጓዙት ወጣቶችም የሕብረተሰቡን ህልምና ምኞት ይዘው በአዲስ ኃይል ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በደቡብ አፍሪካ የኩዊንስ-ታዎን ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሲፊዎ ፖል ቫንቃ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‘ወጣቶቹ በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን’ ገልጸው፥ ደቡብ አፍሪካን፣ ቦትስዋናን እና እስዋቲኒን የሚሸፍነው የደቡብ አፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (SACBC) የወጣቶች ግንኙነት ላይ በትጋት እንደመስራቱ መጠን፣ ብጹእነታቸው የኢዮቤልዩ ዝግጅትን በቅርበት ሲከታተሉት እንደነበር በማንሳት፣ በደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ውስጥ 'የተስፋ ነጋዲያን' የሚለው የኢዩቤሊዩ ዓመት ጭብጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲከበር እንደነበር ገልፀው፥ ከ2000 እስከ 3000 የሚደርሱ ወጣቶች በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በአካባቢው የወጣቶች መንፈሳዊ ንግደት ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ለኢዮቤልዩ ዓመት ለማዘጋጀት የተለያዩ ዝግጅቶችን ማደራጀት
ግላድነስ በራሷ ሀገረ ስብከት ውስጥ የወጣቶች ኮሚሽኑ የተለያዩ ተግባራትን እና ፕሮጄክቶችን ያካተተ “ወደ ወጣቶች ኢዮቤልዩ የሚወስደው መንገድ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ተነሳሽነቶችን ማካሄዱን በመግለጽ፣ በአከባቢዋ ተመሳሳይ የጉጉት ስሜቶችን እንዳስተዋለች አብራርታለች።
እነዚህም ዝግጅቶች በፕሪቶሪያ ሀገረ ስብከት ዙሪያ የተደረጉ “የመንፈሳዊ ንግደት ምልክቶች” የሆኑትን መስዋእተ ቅዳሴ፣ የመቁጠሪያ እና ሌሎች መንፈሳዊ ዝግጅቶች፣ የኖቬና ጸሎቶች እና በቅዱስ ዓመቱ ላይ ያተኮሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች እና ‘የተስፋ ነጋዲያን’ በሚል መሪ ቃል ላይ የተመሰረቱ በየወሩ በሚደረጉ ስብሰባዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲደረጉ እንደነበር ገልፃለች።
እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መንፈሳዊ ነጋዲያን መሆን ምን ማለት እንደሆነ ከማሰላሰል ጀምሮ እንደ ሃገር ደቡብ አፍሪካን በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ማለትም በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት እና ሴት ልጅን የመግደል ወንጀል ላይ ያተኮሩ እንደነበር ተብራርቷል።
ግላድነስ እንደገለጸችው በእነዚህ ዝግጅቶች ለምሳሌ በፆታ ላይ በተመሰረተ ጥቃት እና ሴት ልጅ ላይ በሚፈጸም የግድያ ወንጀል ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን ለማስታወስ እንደ ተስፋ ነጋዲያን ልዩ የሆኑ ጸሎቶች እንደተካሄዱ ያስታወሰች ሲሆን፥ በዚህ የጸሎት ሥነ ስርዓት ለሰለባዎቹ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ወንጀለኞቹ እንዲለወጡ ጸሎት ሲደረግ እንደነበር አብራርታለች።
ከዚህም ባለፈ አንዳንድ ደብሮችም ለኢዮቤልዩ ዝግጅት የራሳቸውን ተነሳሽነቶች ማስጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህም ተግባራት ውስጥ አረጋውያንን በመርዳት የቅዱስ ዓመትን በተግባር ለመኖር የተደረገ ጥረት እንደሚገኝበት ተነግሯል።
‘ወጣቶች ለቤተክርስቲያኑ የበለጠ ለመስራት ሲተጉ ማየት በጣም አስደሳች ነገር መሆኑን’ የገለጸችው ግላድነስ፥ በጣም አስደናቂ ጉዞ እንደሚሆን ያላትን እምነት በቃለ ምልልሱ ወቅት ተናግራለች።
የወዳጆቻቸውን ተስፋ ይዘው ይጓዛሉ
ከዚህም ባለፈ እሷ እና የጉዞ አጋሮቿ በሮም በሚዘጋጀው ሥነ ስርዓት ላይ መገኘት የማይችሉትን ደቡብ አፍሪካውያን ወጣት ጓደኞቻቸውን ምኞት እና ተስፋ ይዘው እንደሚጓዙ በመግለጽ፥ በሃገረ ስብከቱ ከተደረጉት የመሰናዶ ዝግጅቶች መካከል አንዱ ወጣቶቹ ሕልማቸውንና ምኞታቸውን ‘የተስፋ ልብስ’ ተብሎ በተሰየመው ጨርቅ ላይ የሚጽፉበት መርሃ ግብር እንደተካሄደ እና ይሄንን ልብስ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደሚያቀርቡ እና ደቡብ አፍሪካ ለቀሩት ወጣቶች እንዲጸልዩላቸው መታቀዱን ጭምር ገልጻ፥ በዚህም እግዚአብሔር ምኞታቸውን፣ ህልማቸውን እና ተስፋቸውን እንደሚሰጣቸው ተስፋ እንደምታደርግ አብራርታለች።
እነዚህ የተለያዩ ተነሳሽነቶች ወደ ሮም ለመጓዝ የማይችሉትን በአገር ውስጥ የኢዮቤልዩ ልምድ እንዲኖር ለመርዳት መንገድ ለማሳየት እንደሆነ የጠቀሰችው ግላድነስ፥ “ወጣቶችን ለማበረታታት እና ወደ ሮም ለመጓዝ አቅም ባይኖራቸውም እንኳን ባሉበት ሥፍራ ሆነው 'የተስፋ ነጋዲያን' መሆን እንደሚችሉ ለማሳየት እየሞከርን ነው” በማለት ተናግራለች።
ያጋጠሙ ፈተናዎች
እንደ ደቡብ አፍሪካ ባለ አገር ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች በሚኖርባትና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ባለበት ሃገር፥ በርካቶቹ ወደ ሮም ለመጓዝ በቂ ገንዘብ መሰብሰብ እንዳልቻሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በቂ ገንዘብ ማሰባሰብ ባለመቻሉ ምክንያት ማንንም የማይልኩ አንዳንድ አህጉረ ስብከት እንዳሉ ያስታወሱት ብጹእ አቡነ ቫንቃ፣ የራሳቸው ሀገረ ስብከት እንኳን ሳይቀር በኢኮኖሚ ውስንነት ምክንያት ምዕመናንን ወደ ዝግጅቱ መላክ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ግላድነስም በበኩሏ ተመሳሳይ ጉዳዮችን በማስተጋባት፣ አብዛኛዎቹ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከመካከለኛ ቤተሰቦች የመጡ በመሆናቸው የገንዘብ እጥረት ከዋና ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን በማንሳት፥ በርካታ ወጣቶች ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ መቁጠሪያዎችን በመስራት እና በመሸጥ የመሳሰሉ የገቢ ማሰባሰብያ ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበር አስረድታለች።
ከገንዘብ እጥረቱም በተጨማሪ የዚህ ጉዞ ሌላ አስጨናቂ ተግዳሮት የነበረው የቪዛ ማመልከቻ ሂደቶች እንደነበር የጠቀሰችው ግላድነስ፥ ‘በጣም ረጅም፣ ጥብቅ የጊዜ ሰሌዳዎች እና አንዳንድ ኋላ ቀር አሰራሮችን ማለፍ ግድ እንደነበር’ አስታውሳ፣ ጉዟቸው አንድ ሳምንት እየቀረው እንኳን ከቡድኑ አባላት ግማሽ ያህሉ አሁንም ቪዛቸውን እየጠበቁ እንደሆነ ገልፃለች።
“ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ በቡድን መጓዝ ብዙ ትጋት እና የቡድን ስራ ይፈልጋል” ያለችው ግላድነስ፥ ነገር ግን ምንም አይነት ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙ እንደማያሸንፋቸው፣ እግዚአብሔር ከሂደቱ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከእነሱ ጋር እንደነበረ የሚያረጋግጡበት ይህ እንደሆነ ገልፃለች።
ችግሮች ቢኖሩም ወጣት እና ጉልበት ያለው ህዝብ
ግላድነስ የሃገሪቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወጣት መሆን ቀላል እንዳልሆነ ጠቅሳ፥ የሥራ አጥነት መጠን በጣም ከፍተኛ እንደሆነ እና ይህም የሃገሪቱን ወጣቶች እንደሚጎዳ ገልጻለች።
በያዝነው ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የወጣቶች ስራ አጥነት መጠን 46 በመቶ እንደነበር የደቡብ አፍሪካ የስታትስቲክስ ዲፓርትመንት ያስታወቀ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና የአእምሮ ጤና እክል የመሳሰሉ ሌሎች ችግሮችንም በሃገሪቱ መበራከታቸውን ግላድነስ አስታውሳለች።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው አማካይ ዕድሜ 30 ዓመት በመሆኑ እና ወጣቶች ሙሉ ጉልበት እና ህይወት ያላቸው በመሆኑ በርካታ እድሎች እንዳሉ በአጽንዖት በመግለጽ፥ ለአብነትም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያሉ በርካታ ወጣቶች ለወጣቶች ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የሚረዱ የሙያ ዝግጅቶችን ወይም ሌሎች ተነሳሽነቶችን ለማደራጀት በመሞከር ላይ እንደሚገኙ ጠቁማ፥ ከዚህም በተጨማሪ ዲሞክራሲ እና የመብት ነፃነት በመኖሩ እራሳቸውን መግለጽ እና እምነታቸውን በነፃነት መለማመድ እንደሚችሉ አስረድታለች።
ሃዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የላከውን መልዕክት በመጥቀስ “እንደ ወጣቶች የሚያጋጥሙን በርካታ ተግዳሮቶች አሉ” ያለችው ግላድነስ፥ “እኛ የተስፋ ነጋዲያን እንደመሆናችን መጠን መከራው ቢበዛም ተስፋ የማንቆርጥ መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ” ስትል ተናግራለች።
በአዲስ ጉልበት ወደ ሃገር ቤት መመለስ
ብጹእ አቡነ ቫንካ በበኩላቸው ወጣቶች ከተለያዩ መንፈሳዊ ጉዞዎች በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በአዲስ ጉልበት ተሞልተው እንደሚመለሱ በተለያየ አጋጣሚ ማየታቸውን አስታውሰው፥ ይህ የወጣቶች ኢዮቤልዩ ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ፥ ከእነዚህ መንፈሳዊ ጉዞዎች በኋላ ወጣቶቹ በአዲስ መንፈስ እና ጉልበት ታድሰው እንደሚመለሱ፥ እንዲሁም ወጣቶቹ ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል እና ባገኙት ጉልበት ሌሎቹ ለቤተክርስቲያኗ እንዲሰሩ እና ሃይማኖታቸውን እንዲወዱ በምንሰራው ሥራ ሊያግዙን ይችላሉ ብለዋል።
ግላድነስ በመጨረሻም “ቅዱስ አባታችን በሚያሳርጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለመሳተፍ እና ወደ ቅዱስ በሮች መንፈሳዊ ንግደት ለማድረግ፣ ብሎም በቅዱስ ጴጥሮስ እና በቅዱስ ጳውሎስ መቃብር ላይ ለመጸለይ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ እገኛለሁ” ካለች በኋላ፥ “በዚህም የአብዛኛዎቻችን ወጣቶች እምነት እንደሚታደስ ተስፋ አደርጋለው” በማለት አጠቃላለች።