የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ኃላፊ በጋዛ እየደረሰ ያለው ግፍ በአስቸኳይ መቆም አለበት አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እሑድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ግቢ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ እንዲከበር ጥሪያቸውን በድጋሚ ያቀረቡ ሲሆን፥ የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አልስቴይር ዱተን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥሪ አስተጋብተዋል።
ሁላችንም ስቃዩን እንጋራለን
የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ሃላፊው ባለፈው ሳምንት፣ ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ. ም. ማለዳ በጋዛ ብቸኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሆነው የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ በእስራኤል ጦር የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ቅዱስ ጳውሎስ ‘አንዱ የአካላችን ክፍል ሲጎዳ ሁሉም ስቃዩ ይሰማዋል’ ማለቱን አስታውሰው፥ በጥቃቱ ከተገደሉት ሦስት ክርስቲያኖች መካከል ሁለቱ በዚያ እጅግ አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የምክር አገልግሎት እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ በሚሰጥበት በካሪታስ እየሩሳሌም ድንኳን ውስጥ እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ዋና ጸሃፊው በዓለም አቀፉ ካሪታስ ስም በአደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን እና ንዴት ገልጸው፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእስራኤል መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ በየዕለቱ የሚያደርሰውን ጥቃት እንዲያቆም በሃገሪቱ ላይ ጫና ማድረግ አስፈላጊነት እና አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።
የትኛውም ቦታ አስተማማኝ አይደለም
በጋዛ ውስጥ የሚገኙ 2.1 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ በተጋረጡበት እንዲሁም የምግብ እና የመጠለያ እጦትን እየተጋፈጡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አቶ ዱተን እንደተናገሩት ህዝቡ ለሰብአዊ ተደራሽነት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ጫፍ ላይ መድረሱን እንዲሁም በሚታወቅ እና በተገቢው መንገድ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የእስራኤል መንግስት በግንቦት ወር ዕርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ እንደሚፈቅድ ቢያስታውቅም፣ እገዳው የምግብ፣ የመድሃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች መጠን በጣም አናሳ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው፥ ከዚህም ባለፈ ዕርዳታው አልፎ አልፎ በሚመጣበት ጊዜ እንኳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታውን ለማግኘት ሰልፍ ላይ በነበሩበት ወቅት መገደላቸውን አስታውሰዋል።
‘በየቀኑ ሃያ ወይም ሰላሳ ሰዎች ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው እጅግ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ በጥይት እንደሚገደሉ’ ያስታወሱት ሃላፊው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ቃል በማስተጋባት እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ማዕከላት ያሉ የመጠሊያ ቦታዎች እና የተቀደሱ ሥፍራዎች እውቅና እና ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፍ ህግን በተፃረረ መልኩ
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር በሃምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ ‘ሰብአዊ ከተማ’ ብለው በጠሩት ራፋህ ከተማ ላይ በሚዘጋጅ ካምፕ እንዲያስገባ ያቀረቡትን እቅድ ያስታወሱት ሃላፊው፥ ይሄንን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ የሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት የታቀደውን ከተማ “የማጎሪያ ካምፕ” ብለው መጥራታቸውን እና ፍልስጤማውያንን ወደ ካምፑ እንዲገቡ ማስገደድ “የዘር ማጽዳት” ተግባር መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዱተን በራፋ ለፍልስጤማዊያን የተዘጋጀው አካባቢ ምንም አይነት መገልገያዎች፣ ማረፊያዎች፣ የንፅህና መጠበቂያ ቦታዎች ወይም መታጠቢያ ሥፍራዎች እንደሌለው ገልጸው፥ በአሁኑ ጊዜ በዚያ ቦታ ምንም ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን ህዝቡ ወደ ሥፍራው እንዲዛወር መታዘዛቸውን በማንሳት፥ ማንም ሰው እንዲሰደድ መገደድ እንደሌለበት ተከራክረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ድርጊት አባል ሀገራት በተደጋጋሚ የተስማሙበትን ዓለም አቀፍ ህግ የሚጻረር መሆኑን ያስጠነቀቁት አቶ ዱተን፥ በማከልም በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል እንደማይችል ከእስራኤል መንግሥት ጋር ግልጽ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ሌሎች መንግስታት እስራኤል በጋዛ ህዝብ ላይ እየፈጸመች ያለውን ግፍ እንድትቀጥል የሚያስችላትን ድጋፍ ማድረግ ማቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አስቸኳይ የእርዳታ ፍላጎት
በአሁኑ ወቅት በጋዛ ውስጥ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግን ማክበር በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ያስረዱት ሃላፊው፥ ከአራት ወር በፊት በተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት 600 የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት እንደቻሉ፥ ነገር ግን ከመጋቢት ወር ጀምሮ እርዳታ እንዳይገባ በመከልከሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገባ መታገዱን እና ወደ አከባቢው የሚገባው የእርዳታ ደረጃ ከዚህ በፊት ከነበረው በጣም ያነሰ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ሰብአዊ እርዳታን እንዴት ማከፋፈል እንደሚገባ ማወቁ ፍፁም ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ዱተን፥ ለአረጋውያን፣ ለነጠላ ወላጆች እና ወደ ሥፍራው ሄደው መቀበል ለማይችሉ ዜጎች ቅድሚያ በሚሰጥ መንገድ መከናወን እንደሚገባ ካሳሰቡ በኋላ፥ ይሁን እንጂ ካሪታስ ከዚህ ቀደም ይጠቀምባቸው የነበሩት የማከፋፈያ ጣቢያዎች በሙሉ በመታገዳቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ዕርዳታ ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን እና በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የምግብ ዕርዳታ የሚሰጥባቸው አራት ቦታዎች ብቻ መቅረታቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አቅርቦቶች ተደራሽነትም ውስን መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው በርካታ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎች እንደተዘጉ እና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትም በጣም ጥቂት መሆናቸውን ጠቁመው፥ በጋዛ የሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ቤተክርስቲያን ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት እና በኋላም ሕይወታቸው ካለፉ ሰዎች መካከል ሁለቱ በመሠረታዊ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ሕይወታቸው ማለፉን በአጽንዖት ገልጸዋል።
አቶ ዱተን በመጨረሻም የቦምብ ድብደባው እና የግፍ ተግባሩ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ አጠቃለዋል።