‘ዘ ዎርክስ ኦፍ ኒው ሚሊኒየም ፋውንዴሽን’ የተባለው ተቋም ለ10,000 ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት የተከበረው የዚህ ፋውንዴሽን 25ኛ ዓመት ምስረታ በዓል የተጀመረው በጃስና ጎራ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ውስጥ በተካሄደው እና በፖላንድ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ አንቶኒዮ ጊዶ ፊሊፓዚ በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሆነ ተነግሯል።
ሊቀ ጳጳስ ፊሊፓዚ በሥርዓተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን ምስጋና እና ልግስና በግልም ሆነ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
'የሕይወትን ባሕል' መገንባት የተባለው በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተነሳሽነት
ሊቀ ጳጳስ ፊሊፓዚ የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎቹ በዛሬው ዓለም ከነገሰው ራስ ወዳድነት እና ብሄርተኝነት በተቃራኒ በመቆም “የሕይወትን ባህል” እንዲያራምዱ ያበረታቱ ሲሆን፥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ‘የሰው ልጅ ራሱን በታማኝነት ካላቀረበ በስተቀር እሱነቱን ሙሉ በሙሉ ማግኘት አይችልም’ ብለው ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት የምንኖር ከሆነ ይሄንን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻልም ጭምር አብራርተዋል።
ከመስዋእተ ቅዳሴው ሥነ ስርዓት በኋላ የነፃ ዕድል ተማሪዎቹ ተወካዮች “እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን በሰጠን ልዩ ጥሪ በሆነው የሕይወትን ጥሪ መንገድን በመከተል የፍቅር ሥልጣኔን መገንባት እንፈልጋለን” በማለት የፋውንዴሽኑን ማህበረሰብ በሙሉ ለቅድስት ድንግል ማርያም አደራ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ነፃ የትምህርት ዕድል
ፋውንዴሽኑ የተቋቋመው ትምህርታቸውን ለመከታተል የገንዘብ ችግር ያጋጠማቸውን ወጣቶች ለመደገፍ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው የገለጹት የቦርዱ ሊቀመንበር አባ ዳሪዮስ ኮቨልሲኪ፥ ሆኖም ግን ‘የገንዘብ ድጋፍ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ’ በመግለጽ፥ የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎቹ እርስ በእርስ ተገናኝተው እንዲወያዩ፣ ማህበረሰብ እንዲገነቡ እና በመንፈሳዊ ህይወት እንዲያድጉ አበረታተዋል።
በሰሜናዊ ፖላንድ ከምትገኘው ዳንስክ ከተማ የመጣችው የቀድሞ የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እና በጃዝ ድምጽ ጥናት የተመረቀችው ማርታ ዳይዊካ ፋውንዴሽኑ ሙያዊ የሙዚቃ ሥራ ለመጀመር እንዳስቻላት በመግለጽ፥ ያገኘችው ነፃ የትምህርት ዕድል በህይወቷ ውስጥ በሥነ ጥበብ፣ በግላዊ እና በመንፈሳዊ እድገቷ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ እንዳለው አስታውሳለች።
የጸሎት፣ የማህበረሰብ እና የሙዚቃ ቀን
የተቋሙ ምስረታ በዓል ወደ ጃስና ጎራ ገዳም በተደረገ መንፈሳዊ የእግር ጉዞ እና የመቁጠርያ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን፥ በገዳሙ ውስጥ ከተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ በኋላ ተሳታፊዎች በቼዝቶኮዋ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሀገረ ስብከቱ የአትክልት ስፍራ በመሰብሰብ የጋራ ምስክርነቶችን እና ትውስታዎችን በመጋራት ያሳለፉ ሲሆን፥ ምሽት ላይ የፋውንዴሽኑ መዘምራን እና ኦርኬስትራ በገዳሙ ውስጥ የሙዚቃ ዝግጅት አቅርበዋል።
የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ሕያው መታሰቢያ”
በ 1992 ዓ.ም. በፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ የተመሰረተው የአዲሱ ሚሊኒየም ፋውንዴሽን የተፈጠረው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከትናንሽ ከተማዎች እና ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ለመጡ ወጣቶች የአብሮነት ድጋፍ እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ፋውንዴሽኑ እስካሁን ድረስ በመላው ፖላንድ ወደ 10,000 ለሚጠጉ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል። ይሄንንም ሲያደርግ በነፃ የትምህርት ዕድል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ምስረታ እንዲሁም የበጎ ፈቃደኝነት ተሳትፎን በማጎልበት ጭምር እንደሆነ ተብራርቷል።
ነፃ የትምህርት እድሉ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፥ ከ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ፋውንዴሽኑ ከዩክሬን ለመጡ ወጣት ስደተኞች ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
ፋውንዴሽኑ ብዙውን ጊዜ “የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕያው መታሰቢያ” ተብሎ እንደሚጠራም ተነግሯል።