መንትያ ወንድማማቾቹ ለምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት “ድምፅ ለመሆን” አዲስ የድህረ ገጽ መድረክ ማዘጋጀታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዚህ ሳምንት የሚከበረው የዲጂታል ሚስዮናውያን እና የካቶሊክ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ እና የወጣቶች ኢዮቤልዩ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት ወደ ሮም ከተጓዙት በሺዎች ከሚቆጠሩት ወጣቶች መካከል ከሊባኖስ የመጡት መንትያ ወንድማማቾች ቻርቤል እና ጆቫኒ ሊቴፍ ይገኙበታል።
የማህበራዊ ድህረ ገጽ መተግበሪያ በሆነው እና ‘ኢስተርን ክርስቲያንስ’ (eastern_christians) ብለው በሰየሙት የኢንስታግራም ገፃቸው ከ600,000 በላይ ተከታዮች ያሏቸው ሁለቱ ወንድማማቾች ይሄንን ገፃቸውን በዋናነት በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች መረጃ ለማካፈል እንደሚጠቀሙበት የገለጹ ሲሆን፥ ራሳቸውን እንደ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከመመልከት ይልቅ፣ የዘመናት ተልእኮ ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
የ2,000 ዓመት ተልዕኮን ማስቀጠል
ጆቫኒ ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ጆሴፍ ቱሎክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት እንደተናገረው ተልዕኳቸው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተጀመረ በመጥቀስ፥ ‘ይሄንን ተልዕኮ ማጠናከር እና ማስተላለፍ የሁሉም ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነ፣ እነሱም ይህን ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ፥ “ለእምነታችን እና ለህብረተሰባችን የበኩላችንን አስተዋፅኦ የምናደርግበት ጊዜ አሁን ባለንበት የኛ ትውልድ ነው” ሲል አበክሮ ተናግሯል።
“በመካከለኛው ምስራቅ ክርስቲያን ሆነህ ስትወለድ የተለያየ ተልዕኮ ይዘህ ነው የምትወለደው” ያለው ቻርቤል በበኩሉ፥ ባህላቸው፣ ማንነታቸው እና ትውፊታቸው ከጥንት ክርስቲያኖች ጀምሮ ለትውልድ ሲተላለፍ እንደነበር በማስታወስ፣ ወንድማማቾቹ “ይህን ውብ የሆነ ስጦታ” እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አብራርቷል።
ሁለቱ ወንድማማቾች ይህ ተግባር ከመካከለኛው ምስራቅ አልፎ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንደሚዘልቅ ተስፋ እንዳላቸው እና ይህም ተግባራዊ እንዲሆን ማህበራዊ ሚዲያው ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ጭምር አስረድተዋል።
‘እኛ ከዚህም በላይ ነን’
በዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት በተንሰራፉበት ዘመን ቻርቤል እና ጆቫኒ ‘ኢስተርን ክርስቲያንስ’ የተሰኘው ገፃቸው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ብቻ እንዳልሆነ አበክረው በማሳሰብ፥ ‘ሰዎችን ለመድረስ እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ ብሎም ሃሳባቸውን ለማጋራት ምርጡ መንገድ’ ይህ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከገፃቸው በስተጀርባ ያለው ተነሳሽነት በዜና እና በመረጃ በተሞላው ዓለም ላይ ተጨማሪ መረጃ ለመጨመር ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሰው ቻርቤል፥ አሁን ያለውን ትርክት በመቀየር ከስሜታዊነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት፣ በምስራቅ ክርስቲያኖች ላይ የሚደረገውን ብቻ ከማውራት ማንነታቸውን በሰፊው ወደ ማስተዋወቅ ድረስ የመሄድ እድል እንደሚሰጥ ገልጿል።
“እኛ ከሚደረግብን ነገር በላይ ነን” ያለው ቻርቤል “እኛ ስነ ጥበብ ነን፣ እኛ ሙዚቃ ነን፣ እኛ እምነት ነን፣ እኛ ጠንካራ ነን” በማለት አፅንዖት በመስጠት ከተናገረ በኋላ፥ ወንድማማቾቹ በገፃቸው ላይ በሚያወጡት መልዕክቶች አማካይነት በዘመናቸው ባሉ ስደትና ፈተናዎች መካከል ‘ለሕዝባቸው ድምጽ መፍጠር’ እንደቻሉ አስረድቷል።
እንደበፊቱ አይሆንም
ለበርካታ አሥርተ ዓመታት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሕይወት በብዙ ችግሮች ተሞልቶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፥ ቻርቤል አንድ በቅርብ ጊዜ የወጣ ጥናት ዋቢ አድርጎ እንዳመለከተው ባለፈው ምዕተ-ዓመት በክልሉ የሚገኙ የክርስቲያኖች ቁጥር ከ 13.6 በመቶ ወደ 4.2 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስታውሶ፣ “ይህ አሁን እኛ በህይወት እያለን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ጉዳይ ነው” ካለ በኋላ፥ ከዚህን በፊት ሌሎች ሃይማኖታዊ ጥቃቶች የነበሩ ቢሆንም እንደ ዛሬው ጊዜ እንዳልነበሩ ገልጿል።
ቻርቤል በማከልም መፍትሄው ከትውልድ አገራቸው መሸሽ እንዳልሆነ ጠቅሶ፣ ለሁለት ሺህ ዓመታት ሲታገሉለት የኖሩትን ነገር አሁን ላይ ጥሎ መሸሽ እንደማይፈልጉ፣ ይሄም ማንነታቸው እና ቤታቸው ስለሆነ ጥሎ መሸሽ ለእነሱ መፍትሄ እንዳልሆነ፥ ከዚህም ይልቅ እነሱ የሚፈልጉት መፍትሄ በመካከለኛው ምስራቅ በክብር እና በደስታ መኖር እንደሆነ አስረድቷል።
በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ዓለምን መድረስ
ወንድማማቾቹ በሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች 800,000 ተከታዮችን መድረስ መቻል የጸሎት እና የመንፈስ ቅዱስ መገለጫ እንደነበር ገልጸው፥ ይህም ለማኅበረሰባቸው፣ ለዓለም እና በሁሉም ቦታ ለሚገኙ ክርስቲያኖች አንድ ነገር እንዲያደርጉ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ይህም በመሆኑ ለዲጂታል ሚስዮናውያን እና ለካቶሊክ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ በሮም መገኘት ለእነዚህ ወንድማማቾች ልዩ ነገር እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ቻርቤል ይሄንን አስመልክቶ እንደተናገረው ‘ቫቲካን እንደ ካቶሊኮች እና እንደ ክርስቲያኖች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለዓለም መልዕክት ለማስተላለፍ እየሞከረች’ እንደሆነ ገልጿል።
“ማህበራዊ ሚዲያ በጣም ኃይለኛ መሳሪያ ነው” ያለው ጆቫኒ በበኩሉ፤ወንድማማቾቹ በዲጂታል ተልዕኮ ሥራቸው ትልቅ ኃላፊነት እንደሚወስዱ በድጋሚ በመግለጽ፥ በመጨረሻም “በምናደርገው ነገር እንድንቀጥል እና እንድንጸና የሚያደርገን በቀላሉ ክርስቲያናዊ እሴቶቻችን ናቸው፥ አንዴ ክርስቲያናዊ እሴቶችህን ከያዝክ ምንም የሚያስፈራህ ነገር የለም” በማለት አጠቃሏል።