የመስከረም 4/2018 ዓ.ም የ22ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመስከረም 4/2018 ዓ.ም የ22ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመስከረም 4/2018 ዓ.ም የ22ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.    መ. ሲራክ 3፡17-20.28-29

2.    መዝሙር 67

3.    ዕብራዊያን 12፡18-19.22-24

4.    ሉቃስ 14፡1. 7-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለ ትሕትናና ስለ መስተንግዶ

የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል “ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና፥ አንተንና እርሱን የጠራ መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ተውለት’ ይልሃል፤ በዚያን ጊዜም እያፈርህ ዝቅተኛውን ስፍራ መያዝ ትጀምራለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ! ወደ ላይ ውጣ’ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።”

የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው “ምሳ ወይም እራት ባሰናዳህ ጊዜ፥ ምናልባት እነርሱም በተራቸው እንዳይጠሩህ፥ እንዳይክሱህም፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ሀብታም ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባሰናዳህ ጊዜ ድሆችንና ጉንድሾችን አንካሶችንም ዐይነ ስውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት አጸፋ የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት በተዘጋጀ ድግስ ላይ መገኘቱን እና ወደ ድግሱ የተጋበዙት አንዳንድ ሰዎች የከበሬታ ሥፍራን ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ መመልከቱን ይነግረናል። የእነዚህን ሰዎች ሁኔታ የሚመስል፣ በሌሎች ሰዎች መካከል ራስን ከፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት፣ የበላይነትን ለማግኘት የሚደረግ መሽቀዳደም በዘመናችንም የሚታይ ተግባር ነው። በሕብረተሰብ መካከል ሆነ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ራስን ከሌሎች ከፍ አድርጎ ለማስቀመጥ የሚደረግ ጥረት፣ ማሕበራዊ የወንድማማችነት ሕይወትን የሚያበላሽ በመሆኑ መልካም አይደለም። ሰዎች ራሳቸውን በክብር ቦታ ላይ ለማስቀመጥ የሚያደርጉትን መሽቀዳደም አስመልክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለት አጫጭር ምሳሌዎቹ አማካይነት መሠረታዊ የሆኑ የመልካም ስነ ምግባር መንገዶችን ያስተምረናል። እነርሱም ትህትና እና ራስ ወዳድነት የሌለበት ልግስና ናቸው።የመጀመሪያው የኢየሱስ ምሳሌ የሚመለከተው በግብዣ መካከል ራሱን ወደ ከበሬታ ሥፍራ ውስዶ ያስቀመጠውን ሰው ይመለከታል። ኢየሱስ በምሳሌው ሲናገር፣ በተጋበዝክበት ግብዣ ላይ ራስን በቀዳሚ ሥፍራ ማስቀመጥ እንደማይገባ፣ ምክንያቱም ካንተ የሚበልጥ ሌላ ሰው ወደ ግብዣው በገባ ጊዜ፣ ሌላው ሳይሆን ያ የጋበዘህ ሰው ወደ አንተ በመምጣት፣ የተቀመጥክበትን ስፍራ ለቅቀህ ወደ ሌላ ሥፍራ እንድትሄድ ስለሚጠይቅህ እና በዚያን ጊዜ ከታላቅ ሃፍረት ጋር የመጨረሻውን ቦታ ለመያዝ እንድትሄድ ስለሚያደርግ ነው። “አንድ ሰው ለሠርግ ግብዣ ሲጠራህ ተሽቀዳድመህ በክብር ስፍራ አትቀመጥ። ምናልባት ካንተ የበለጠ ክብር ያለው ሰው ተጠርቶ ይሆናል። ታዲያ ሁለታችሁንም የጋበዛችሁ ሰው ወደ አንተ መጥቶ ይህን ስፍራ ለዚህ ሰው ልቀቅለት ይልሃል። ያን ጊዜ በታላቅ ሕፍረት ወደ ዝቅተኛ ቦታ ወርደህ ትቀመጣለህ” (ሉቃ. 14. 8 እና 9)። ነገር ግን ኢየሱስ ከዚህ በተለየ መልኩ ይህን እንድናደርግ ስተምረናል። “ነገር ግን ለግብዣ ስትጠራ ሄደህ በዝቅተኛ ስፍራ ተቀመጥ፤ በዚያን ጊዜ የጠራህ ሰው ወደ አንተ መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ ወደ ከፍተኛ ስፍራ ወጥተህ ተቀመጥ’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም በሌሎች ተጋባዦች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ” (ሉቃ. 14. 10)። ስለዚህ በሌሎች መካከል ራሳችንን ከፍ ማድረግ ይቅርብን። የሚሻለው እኛ ለራሳችን ክብር ከመስጠት ይልቅ ሰዎች ቢያከብሩን ይመረጣል። ኢየሱስ ዘወትር የትህትናን መንገድ ያሳየናል፣ ያስተምረናል። ስለዚህ የእርሱን የትህትና መንገድ መማር ያስፈልጋል። ከሰዎች ጋር እውነተኛ ወዳጅነት ሊኖረን የሚያደርግ የትህትና ሕይወት ነውና። ትህትናችንም ከአንገት በላይ ሳይሆን እውነተኛ መሆን አለበት።

ኢየሱስ በሁለተኛው ምሳሌ፣ በበዓሉ ላይ እንዲገኙለት ብሎ የተለያዩ ሰዎችን የጋበዘውን ሰው ይመለከታል። እንዲህም ይላል፥ “ነገር ግን ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ደሆችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችን፣ እውሮችንም ጥራ፤ ይህን ብታደርግ እነርሱ ውለታ ለመክፈል ስለማይችሉ ትመሰግናለህ፤ በጻድቃን ትንሳኤ ጊዜ እግዚአብሔር ይከፍልሃል”። (ሉቃ. 14. 13-14)። በዚህ ምሳሌው ኢየሱስ ከተለመደው የግብዣ ዓይነት በተለየ መልኩ፣ ሰብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ የሆነውን የእግዚአብሔር መንገድ በተከተለ መልኩ ተናግሯል። ምሳሌውንም መረዳት እንድንችል በቁ. 14 ላይ “በጻድቃን ትንሳኤ ጊዜ እግዚአብሔር ይከፍልሃል” በማለት፣ በሰዎች መካከል ለተናቁት፣ ለተረሱት፣ ለተዋረዱት፣ ለደሄዩት ሁሉ በምድር ላይ ለምናደርገው መልካም ተግባር ሁሉ፣ ሰዎች ሊሰጡን ከሚችሉት ምስጋና ወይም ሊከፍሉን ከሚችሉት ውለታ መጠን እጅግ በላይ አድርጎ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን ይናገረናል። ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ለሚያደርጉት ውለታ ተመጣጣኝ ምላሽን ወይም ክፍያን ይጠብቁ ይሆናል። የዚህ ዓይነታ ውለታ ክርስቲያናዊ ውለታ ሊሆን አይችልም። ምላሽን የማይጠብቅ የትህትና ልግስና ነው ክርስቲያናዊ ሊሆን የሚችለው። ብዙን ጊዜ በስዎች መካከል የሚደረግ ውለታ፣ በቸርነት የተሞላ ነጻ ውለታ ሊሆን ሲገባው ወደ ጥቅም ያዘነበለ በመሆኑ የተነሳ የሰዎችን ግንኙነት የሐሰት ግንኙነት ያደርገዋል። ከዚህ በተለየ መልኩ፣ ታላቅ ደስታ የሚገኘው በእግዚአብሔር ፍቅር በመመራት፣ እርሱ አዘጋጅቶ ወደሚጠብቀን ወደ ሰማያዊው ግብዣ ለመድረስ በሚያስችለን መንገድ መራመድ ይኖርብናል።  

በትህትና የተሞላች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በሰዎች መካከል ራሳችንን ከፍ የምናደርግ ሳንሆን ዝቅተኞች መሆናችንን እንድናውቅ፣ በእውነተኛ ቸርነት ደስታን ማግኘት እንድንችል ትርዳን”።    

 

13 Sep 2025, 09:25