ክርስቲያናዊ ጋብቻ ክርስቲያናዊ ጋብቻ  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “የተክሊል በዓልን ለማክበር ስለ መዘጋጀት”

ለጋብቻ የሚደረጉ የአጭር ጊዜ ዝግጅቶች በሠርግ ጥሪ፣ በአልባሳት፣ በድግስና  ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ጉልበትንና ደስታን ጭምር በሚያሟጥጡ ሌሎች በርካታና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ጥንዶቹ ወደ ሰርጉ ሥነ ሥርዐት የሚመጡት ለሚወስዱት ትልቅ እርምጃ ትኩረት ሰጥተውና ተዘጋጅተው ሳይሆን፣  ደክሞአቸውና ተቻኩለው ነው። ከትልቅ ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ጭንቀት አንዳንድ ሕጋዊ ያልሆኑ የጋብቻ አንድነትንም ይነካሉ።  ከእነዚህ  ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ ወጪዎች በመኖራቸው፣ ጥንዶቹ ከሁሉ በላይ ስለ ፍቅራቸውና እርሱንም በሌሎች ሰዎች ፊት ለማክበር ከመጨነቅ ይልቅ ፈጽሞ አይጋቡም። እዚህ ላይ ስለ እጮኛሞች አንድ ነገር ልበል። ልዩ ለመሆን ድፍረት ይኑራችሁ። በፍጆታና በከንቱ ታይታዎች በተሞላ ኅብረተሰብ አትዋጡ። ዋናው ነገር  በእግዚአብሔር ጸጋ የጠነከረና የተቀደሰ የጋራ ፍቅራችሁ ነው። ፍቅር ከማንኛው ነገር በላይ ቅድሚያ የሚያገኝበትን መጠነኛና ቀላል ሥነ ሥርዓት መምረጥ ትችላላችሁ። የሐዋርያዊ ሥራ ሠራተኞችና መላው ማኅበረሰብ ይህን ቅድሚያ እንደ ልዩ ነገር ሳይሆን እንደ መደበኛ መመዘኛ መውሰድ ይችላሉ።

ጥንዶቹ ለጋብቻ ሲዘጋጁ፣ ሥርዓተ አምልኮን መሠረታዊ የግል ልምድ እንዲያደርጉና የእርሱንም የእያንዳንዱን ምልክት ትርጉም እንዲያውቁ ማበረታታት ያስፈልጋል። ሁለቱም ሰዎች የተጠመቁ ከሆኑ፣ በቃለ መሐላና ጋብቻን ምሉእ በሚያደርገው አካላዊ ውህደት የሚገለጸው ዝግጁነት፣ ሥጋ በለበሰው በእግዚአብሔር ልጅና በቤተክርስቲያኑ መካከል እንዳለው የቃል ኪዳን ፍቅርና የአንድነት ምልክት የሚታይ ነ። በተጠመቁ ሰዎች ውስጥ፣ ቃላትና ምልክቶች ቀጥተኛ የእምነት ቋንቋ ናቸው። እግዚአብሔር በሰጠው ትርጉም የተፈጠረ አካል “የምሥጢሩ አዳዮች ቋንቋ” ይሆናል፤ እነርሱም በጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ ከራሱ ከእግዚአብሔር የመነጨው ምሥጢር እውን ሆኖ እንደሚገለጽ ያውቃሉ”። (242)

214.  አልፎ አልፎ፣ ጥንዶቹ ከቃለ መሐላ ቀጥለው የሚመጡ ምልክቶችን ሁሉ ትርጉም የሚገልጽ ነገረ መለኮታዊና መንፈሳዊ ቁም ነገር አይረዱትም። እነዚህ ቃላት ወደ አሁኑ ጊዜ ዝቅ ሊሉ እንደማይችሉና “ሞት እስኪለየን ድረስ” ያለውን ሙሉውን መጪውን ጊዜ ጭምር የሚያካትቱ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። የቃለ መሐላው ይዘት ግልጽ እንደሚያደርገው፣ “ነጻነትና መተማመን እርስ በርስ የሚቃረኑ ሳይሆኑ፣ በግለ ሰባዊምሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው። በእርግጥ፣ በሉላዊ መገናኛ ባህላችን ውስጥ፣ ባልተከበሩ የተስፋ ቃላት መበራከት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እናሰላስል… ቃልን ማክበር፣ ለሌላው የገቡትን የታማኝነት ቃለ መሐላ መጠበቅ፣ እነዚህ ነገሮች ሊሸጡና ሊለወጡ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም። በኃይል ሊገደዱና ያለ መሥዋዕትነት ሊጠበቁ አይችሉም”። (243) 

215. የኬንያ ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ “ብዙ ወጣቶች በሰርጋቸው ላይ ስለሚያተኩሩ፣ የሚገቡበትን የረጅም ጊዜ የውዴታ ግዴታ ይረሳሉ”። (244) ስለዚህ፣ ወጣቶች ምሥጢረ ተክሊልን እንደ አንድ ጊዜያዊና ትዝታው እየቆየ እንደሚረሳ ነገር ሳይሆን፣ የትዳር ሕይወትን በዘላቂነት የሚነካ እውነታ መሆኑን እንዲገነዘቡ መምከር ያስፈልጋል። (245) የወሲባዊነት ተዋልዶአዊ ትርጉም፣ የአካላዊ ቋንቋ እና በትዳር ሕይወት ውስጥ የሚገለጹ የፍቅር ምልክቶች ሁሉ “ቀጣይ የአምልኮ kንቅን” ይሆናሉ፤ “የጋብቻ ሕይወትም ሥርዓተ አምልኮአዊ ይሆናል”።

ባልና ሚስት በመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትና በሚለዋወጡአቸው የጣት ቀለበቶች  እንዲሁም የሥነ ሥርዓቱ አካል በሆኑ ሌሎች ምልክቶች ትርጉም ላይ ማስተንተን ይችላሉ። አንድ ላይ ሆነው ለእርስ በርሳቸው ሳይጸልዩ፣ በታማኝነትና በልግስና ለመቀጠል የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔርን እርዳታ ሳይሹ፣ ጌታ ከእነርሱ ምን እንደሚፈልግ ሳይጠይቁና ፍቅራቸውን በድንግል ማርያም ምስል ፊት ሳይቀድሱ ወደ ሰርግ ስፍራ ቢመጡ  መልካም አይሆንም። ስለዚህ ወጣቶችን ለጋብቻ የሚያዘጋጁ አካላት እነዚህን ጠቃሚ የጸሎት ወቅቶች እንዲለማመዱ ሊረዱአቸው ይገባል።

“የጋብቻ ሥርዓተ አምልኮ የቤተሰብም የማኅበረሰብም በዓል የሆነ ዐይነተኛ ሁነት ነው። ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምር ያደረገው በቃና የሰርግ ግብዣ ላይ ነበር። በጌታ ተአምር ለአዲሱ ቤተሰብ ደስታን ያመጣው መልካሙ ወይን ጠጅ፣ በማናቸውም ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ጋር የተፈጸመ የክርስቶስ ቃል ኪዳን የሆነ  አዲስ ወይን ጠጅ ነው… ብዙውን ጊዜ የሥነ ሥርዓቱ መሪ በቤተክርስቲያን ሕይወት እምብዛም ለማይሳተፉ፣ ወይም የሌላ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወይም ቤተእምነቶች አባላት የሆኑ ሰዎችን ላካተተ ጉባኤ ይናገራል። ይህም የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ መልካም አጋጣሚ ይሆናል”።

የመጀመሪያዎቹን የጋብቻ ዓመታት ስለ ማላመድ  

217.  ጋብቻ እርስ በርስ በነጻ ፈቃድ የተመራረጡና የሚዋደዱ ሰዎች ብቻ የሚመሠርቱት የፍቅር ሥራ እንደ ሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ፍቅር የአካላዊ መሳሳብ ወይም ደብዛዛ ፍቅር ብቻ ከሆነ፣ ጥንዶች በተለይ ይህ ፍቅር ሲደበዝዝ ወይም አካላዊ ውበት ሲረግፍ ለሥጋት ተጋላጭ ይሆናሉ። ይህ የሚሆንበት የጊዜ ድግግሞሽ ሲታይ፣ ጥንዶች በትዳር ሕይወት የመጀመሪያ ዓመታት ዕድሜ ልካቸውን በአንድነትና በፍቅር ተሳስረው ለመኖር አውቀውና ፈቅደው ያደረጉትን ውሳኔ ይበልጥ ማዳበርና ማጽናት እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ የመተጫጨት ጊዜ በቂ አይሆንም፣ ውሳኔው በተለያዩ ምክንያቶች ይዘቅጣል፤ ይባስ ብሎ ጥንዶቹ ራሳቸው በቂ ብስለት አይኖራቸውም። ከዚህም የተነሣ፣ አዲስ ባለትዳሮች በመተጫጨት ወቅት መከናወን ያለበትን ሂደት መፈጸም ያስፈልጋቸዋል።

218.  ሌላው ከጋብቻ ዝግጅት ጋር የተያያዘ ትልቁ ተግዳሮት ጋብቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደርጎ የሚያበቃ ነገር አለመሆኑን ጥንዶቹ እንዲገነዘቡ የመርዳት ጉዳይ ነው። የእነርሱ ኅብረት እውነተኛና የማይታጠፍ፣ በምሥጢረ ተክሊል የተረጋገጠና የተቀደሰ ነው። ሆኖም፣ ጥንዶቹ ሕይወታቸውን በአንድነት ሲያጣምሩ፣ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ንቁና ፈጠራ ያለበትን ሚና ይወስዳሉ። አሁን የእነርሱ እይታ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታገዝ በየዕለቱ እንዲገነቡት በተጠሩበት በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ማተኮር አለበት። በዚህ ምክንያት፣ ማንኛቸውም ሌላውን ፍጹም እንዲሆን መጠበቅ አይችልም። እያንዳንዳቸው ቅዠትን ትተው ሌላውን እንዳለ፣ እንዳልተጨረሰ፣ ማደግ እንዳለበትና በሂደት ላይ እንዳለ ሥራ አድርገው መቀበል አለባቸው። የትዳር አጋርን ሁልጊዜ መተቸት፣ ትዳርን በአንድነት፣ በትዕግሥት፣ በመግባባት፣ በመቻቻልና በልግስና የሚተገብሩት ዕቅድ ተደርጎ ላለመታየቱ አንዱ ምልክት ነው። ከዚያም ቀስ በቀስ፣ ነገር ግን፣  በእርግጠኝነት፣ ፍቅር ለማያበራ ጥያቄና ትችት ቦታውን ይለቃል፤ አንዱ ወገን በሌላው በጎና መጥፎ ነጥቦች ላይ ያተኩራል፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፤ በፉክክርና ራስን ትክክለኛ አድርጎ በማሳየት ላይ ይጠመዳል።  ያን ጊዜ ጥንዶቹ የዳበረ ኅብረት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ እርስ በርስ መረዳዳት ከማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ። ሰርግ “ገና ጅማሮ” መሆኑን ይረዱ ዘንድ ይህን እውነታ ከመነሻው ለአዲስ ተጋቢዎች ማስገንዘብ ያስፈልጋል። “ቃል እገባለሁ” ሲሉ  ወደ ግባቸው እንዳይደርሱ መንገድ ላይ የሚገጥሙአቸውን መሰናክሎች ሁሉ ማስወገድን የሚጠይቅ ጉዞ ይጀምራሉ። የሚቀበሉት የጋብቻ ቡራኬ ለዚህ ጉዞ የሚረዳ ጸጋና ማበረታቻ ነው። የሚጠቀሙት ቁጭ ብለው፣ ግባቸውን  በተጨባጭ ማሳካት በሚችሉበት መንገድ ላይ እርስ በርስ ሲወያዩ ብቻ ነው።

 የረጋ ውሃ አይረባም የሚል የቆየ ብሂል እንዳለ አስታውሳለሁ። በትዳር የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የጥንዶቹ የፍቅር ሕይወት እንቅስቃሴ ከሌለው፣ ወደ ፊት የሚያራምደውን የስሜት ኃይል ያጣል። ወጣት ፍቅር በደስታና በታላቅ ተስፋ ጉዞውን መቀጠል ያስፈልገዋል። ተስፋ በእነዚያ የመጀመሪያ የትጭጭትና የትዳር ዓመታት ከጭቅጭቅ፣ ከግጭትና ከችግሮች ባሻገር መመልከትንና ነገሮችን አስፍቶ ማየትን የሚያመቻች እርሾ ነው። ተስፋ እድገት እንዲኖር ጥርጣሬያችንና ጭንቀታችንን ይገታል። ከዚህ ሌላ፣ ተስፋ የአሁኑን ጊዜ በሙላት እንድንኖር፣ ሁለንተናችንን ለቤተሰብ ሕይወት እንድናውል ያደርገናል፤ ምክንያቱም ለነገ ጠንካራ መሠረት መጣል የሚቻለው ዛሬን በሚገባ በመኖር ነው።

ይህ ሂደት ልግስናንና መሥዋዕትነትን በሚጠይቁ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ ይከሰታል። የመጀመሪያዎቹ ብርቱ ማራኪ ስሜቶች ሌላኛው የትዳር አጋሬ አሁን የሕይወቴ አካል ሆኖአል ለሚለው ግንዛቤ ቦታቸውን ይለቃሉ። አንዱ የሌላው የመሆን ደስታ ሕይወትን የጋራ እቅድ አድርጎ ወደ ማየት፣ የሌላውን ደስታ ከራስ ደስታ ወደ ማስቀደም፣ ይህ ትዳር ኅብረተሰብን ያዳብራል ወደሚል አስደሳች ግንዛቤ ያደርሳል። ፍቅር እየዳበረ ሲሄድ፣ “መደራደርንም” ይማራል። ይህ ድርድር ከራስ ወዳድነት ወይም ለራስ ጥቅም ከመፈለግ የሚመነጭ ሳይሆን፣ ለቤተሰብ ጥቅም ሲባል የጋራ ፍቅርን የሚተገብርና የመስጠትና የመቀበል መስተጋብር ያለው ነው። በእያንዳንዱ የትዳር ሕይወት ደረጃ ሁለት አሸናፊዎች እንጂ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እንዳይሆን፣ ቁጭ ብሎ በተደረሰባቸው ስምምነቶች ላይ እንደ ገና መደራደር ያስፈልጋል። በቤት ውስጥ፣ ውሳኔዎች በተናጠል ሊወሰዱ አይችሉም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የትዳር አጋር የቤተሰብ ኃላፊነትን ይጋራል፤ ሆኖም፣ እያንዳንዱ ቤት ልዩ ነው፣ እያንዳንዱ ትዳርም ለራሱ የሚበጀውን መንገድ ያመቻቻል።

ምንጭ፡ ር ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 212-220

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በረገኔ

13 Sep 2025, 15:48