ነፍስሔ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምስጢር ተክሊል ፈጻሚዎች የምስክር ወረቀት ሲስጡ ነፍስሔ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምስጢር ተክሊል ፈጻሚዎች የምስክር ወረቀት ሲስጡ   (Archivio Personale di Letícia Schafer)

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “የተክሊል በዓልን ለማክበር ስለ መዘጋጀት፥ ክፍል 2”

ለትዳር መፍረስ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል ስለ ጋብቻ ያልተገባና የተጋነነ ተስፋ ማድረግ ይገኝበታል። እውነታው ከተገመተው በላይ ውስንና ፈታኝ መሆኑ ሲታወቅ፣ መፍትሔው ፈጥኖና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መለያየትን ማሰብ ሳይሆን፣ የትዳር ሕይወት እያንዳንዱ የትዳር አጋር ሌላውን በእውቀት እንዲበስል የእግዚአብሔር መሣሪያ የሚሆንበት የዕድገት ሂደት እንደ ሆነ መገንዘብ ነው። ለውጥ፣ መሻሻል፣ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያሉ መልካም ባሕርያት ማበብ፣ እነዚህ ሁሉ የሚቻሉ ነገሮች ናቸው። እያንዳንዱ ትዳር፣ ከደካማ መሠረት ተነሥቶ በእግዚአብሔር ስጦታና በራሳችን ፈጠራ የታከለበትና ለጋስ ምላሽ በጊዜ ሂደት ወደ ውድና ዘላቂ ነገር የሚያድግ  “የድኅነት ታሪክ›” ይመስላል። የሁለት ፍቅረኛሞች ትልቁ ተልእኮ አንዱ ሌላውን ይበልጥ ወንድና ይበልጥ ሴት እንዲሆኑ እርስ በርስ መረዳዳት አይደለምን? እድገትን ማነቃቃት ማለት አንድን ሰው የራሱን ወይም የራስዋን ማንነት እንዲቀርጽ ወይም እንድትቀርጽ መርዳት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ፍቅር ጥበበኛነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ወንድና ስለ ሴት መፈጠር ስናነብ፣ እግዚአብሔር መጀመሪያ አዳምን ሲሠራ እናያለን (ዘፍጥ. 2፡7)። ከዚያም አንድ አስፈላጊ ነገር እንደ ጎደለ ስለ ተረዳ ሔዋንን ይሠራል፣ ሰውየውም (አዳምም) “እነሆ፣ ይህች አጥንት ከአጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” ብሎ በአድናቆት ሲናገር እግዚአብሔር ሰማ፡፡ እኛም ሰውየውና ሴቲቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋዋቁ ያደረጉትን አስደናቂ ጭውውት መስማት እንችላለን፡፡ በባለ ትዳሮች ሕይወት ውስጥ፣ በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር፣ አንዱ ሰው ሌላውን ሁልጊዜ እንደሚያስደንቅ፣ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይመስል የግንኙነታቸው አዲስ በሮች ወለል ብለው እንደሚከፈቱ መገመት ይቻላል፡፡ በእያንዳንዱ አዲስ ደረጃ፣ እርስ በርሳቸውን “ማነጻቸውን” ይቀጥላሉ፡፡ ፍቅር አንዱ ሌላውን በጥበበኛ ትዕግሥት፣ ከእግዚአብሔር በሚመጣ ትዕግሥት እንዲጠባበቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ለአዲስ ባለትዳሮች የሚደረግ ሐዋርያዊ ጥበቃ ሕይወትን ለመስጠት ለጋስ እንዲሆኑ ማበረታታትንም ያካትታል፡፡ “ከጋብቻ ፍቅር ግላዊና ሙሉ በሙሉ ሰብአዊ ከሆነ ባሕርዩ አንጻር፣ የቤተሰብ ዕቅድ በተገቢው መንገድ ሊፈጸም የሚችለው በባልና ሚስት መካከል በሚደረግ ስምምነትና ውይይት፣ ጊዜያትን በማክበርና የትዳር አጋርን ክብር በመጠበቅ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙውን ጊዜ ለሕይወት ጸር የሆነውን አስተሳሰብ ለመቃወም እንዲቻል “ሁማኔ ቪቴ” በሚል ርእስ የሚታወቀው ሐዋርያዊ መልዕክት (1014) እና “ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ” የተሰኘው ሐዋርያዊ ማበረታቻ አስተምህሮ (14፤ 2835) እንደ ገና ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅነትን የሚያካትቱ ውሳኔዎች “የአንድ ሰው እጅግ የተቀደሰ ምሥጢራዊ ማእከልና መጠለያ የሆነውን” ኅሊና ማነጽን ይጠይቃል፡፡ “በዚያ እያንዳንዱ ሰው ድምጹ ከልብ ጥልቅ ጓዳ ከሚያስተጋባው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን ይሆናል” (ጋውዲዩም ኤት ስፔስ፣ 16)፡፡ ጥንዶቹ በበለጠ ንቃተ ኅሊና እግዚአብሔርንና የእርሱንም ትእዛዛት ለመስማት በጣሩ (ሮሜ 2፡15) እና መንፈሳዊ ድጋፍ ባገኙ ቁጥር፣ ውሳኔአቸው ከተለመዱ ማህበራዊ አስተሳሰቦች ተገዥ ከሆነ ግላዊ ምክንያትና ይሉኝታ ይበልጥ ነጻ ይሆናሉ” (248)። “ጥንዶች በጋራ ምክርና ጥረት ውሳኔ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ፣ ሁለቱም የራሳቸውንና አስቀድመው የተወለዱትንም ሆነ ወደፊት የሚወለዱ ልጆቻቸውን ደህንነት በአስተውሎት ግምት ውስጥ ያስገቡ፡፡ ለዚህ ስሌት ደግሞ የዘመኑን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የኑሮ ሁኔታቸውን ማገናዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመጨረሻም፣ የቤተሰብ ቡድንን፣ የዓለማዊ ኅብረተሰብንና የራስዋን የቤተክርስቲያንን ፍላጎቶች መረዳት አለባቸው፡፡ በስተ መጨረሻ በእግዚአብሔር ፊት ይህን ዳኝነት የሚሰጡት  ወላጆች ራሳቸው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም” (249)።  በተጨማሪ፥ “በተፈጥሮ ሕግጋትና በተዋልዶ ሁኔታ› ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎችን መጠቀም” ( ሁማኔ ቪቴ፣ 11) ሊበረታታ ይገባል። ምክንያቱም “እነዚህ ዘዴዎች የጥንዶቹን አካላዊ ክብር የሚጠብቁ፣ በእነርሱም መካከል ርኅራኄን የሚያበረታቱና የእውነተኛ ነጻነት ትምህርትን የሚደግፉ ናቸው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ 2370)፡፡ ስለዚህ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታና ለወላጆችና ለቤተክርስቲያን የደስታ ምንጭ ስለ መሆናቸው የበለጠ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በእነርሱ አማካይነት ጌታ ዓለምን ያድሳል”፡፡

የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፥ “የመጀመሪያዎቹ የጋብቻ ዓመታት ጥንዶች የትዳር ሕይወትን ተግዳሮቶችና ትርጉም በይበልጥ የሚያውቁበት ዋናና አሳሳቢ ወቅት ነው፡፡ ስለሆነም፣ ለጥንዶቹ የሚሰጠው ምክር ከምሥጢረ ተክሊል ሥነ ሥርዓት ብቻ የዘለለ መሆን  ይኖርበታል (ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ፣ ክፍል 3)፡፡ በዚህ ረገድ፣ ተሞክሮ ያላቸው ጥንዶች የሚጫወቱት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ቁምስና እነዚህን የመሰሉ ልምድ ያላቸው ጥንዶች፣ በማኅበራት፣ በቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎችና በአዳዲስ ማኅበረሰቦች ትብብር፣ ወጣት ባለትዳሮችን  የሚረዱበት ስፍራ ነው፡፡ ወጣት ተጋቢዎች ታላቅ የልጆች ስጦታን ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ስለ ቤተሰብ መንፈሳዊነት፣ ስለ ጸሎትና በእሁድ መሥዋዕተ ቅዳሴ  ስለ መሳተፍ አስፈላጊነትም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ጥንዶችም በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግና ሕይወት ለሚጠይቀው የጋራ ጥቅም ለመሥራት አዘውትረው እንዲገናኙ መበረታታት ይኖርባቸዋል፡፡ ሥርዓተ አምልኮዎች፣ መንፈሳዊ ተግባራት  በተለይ በጋብቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለቤተሰብ  የሚደረጉ ሥርዓተ አምልኮዎች፣ ጸሎቶችና መሥዋዕተ ቅዳሴ በቤተሰብ አማካይነት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በዋና ምክንያትነት ተጠቃሽ ናቸው” (251)፡፡ ይህ ሂደት በእርግጥ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ፍቅር ደግሞ ጊዜና ቦታ ይፈልጋል፤ ሌላው ነገር ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ስለ አንዳንድ ነገሮች ለመወያየት፣ ለመረጋጋትና ለመተቃቀፍ፣ አብሮ ለማቀድ፣ እርስ በርስ ለመደማመጥና ዐይን ለዐይን ለመተያየት፣ እርስ በርስ ለመደናነቅና ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኅብረተሰባችን የጥድፊያ ሩጫና  የሥራ ቦታ ጫና ችግር ይፈጥራሉ፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ አንድ ክፍል ውስጥ እየኖሩ ነገር ግን አንዱ የሌላውን መኖር እንኳ የማያውቅበትና በጋራ የሚያሳልፉት ጥሩ ጊዜ ያለመኖር ችግር አለ፡፡ ስለዚህ፣ ወጣት ወይም ለችግር የተጋለጡ ጥንዶች እነዚያን ወቅቶች በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፉ፣ ትርጉም ያለው የጸጥታ ጊዜ እንዲጋሩና እርስ በርስ እንዲቀራረቡ ለመርዳት የሐዋርያዊ ሥራ ሠራተኞችና የባለትዳሮች ቡድኖች የተለያዩ ዘዴዎችን መቀየስ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህን እንዴት ማድረግ እንደሚገባቸው የተረዱ ጥንዶች ጠቃሚ የመሰሉአቸውን አንዳንድ ተጨባጭ ምክረ ሐሳቦች ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ ትርፍ ጊዜን ፣ ከልጆች ጋር የመዝናኛ ወቅቶችን፣ ዋና ዋና ሁኔቶች የማክበሪያ የተለያዩ መንገዶችን፣ እንዲሁም ለመንፈሳዊ እድገት የሚረዱ አጋጣሚዎችን እንዴት በጋራ ማሳለፍና ማቀድ እንደሚቻል ልምዳቸውን ማካፈል ይችላሉ፡፡ እንደዚሁም እነዚህ ወቅቶች ለወጣት ጥንዶች ትርጉም ያላቸውና አስደሳች እንዲሆኑ ለማድረግና ተግባቦታቸውን ለማሻሻል የሚጠቅም እርዳታ መለገስ ይችላሉ፡፡ ይህም በተለይ የጋብቻ ተሐድሶ  በሚደበዝዝበት ደረጃ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ጥንዶች ጊዜያቸውን እንዴት በጋራ ማሳለፍ እንዳለባቸው ካላወቁ፣ አንዳቸው ወይም ሁለታቸውም ራሳቸውን በኤሌክትሮኒክ መዝናኛ መሣሪያዎች   ውስጥ ወደ መደበቅ፣ ሌሎች የቀጠሮ ምክንያቶችን ወደ መፈለግ፣ የሌላውን ሰው እቅፍ ወደ መሻት፣ ወይም ምቾት የማይሰጥ ቅርበትን መሸሻ አማራጮችን ወደ መመልከት ሊያዘነብሉ ይችላሉ፡፡

226. ወጣት ጥንዶች ዕለታዊ ሁኔታዎችን በመጋራት ጤናማ የቅርርብ ስሜትና መረጋጋት የሚፈጥር የዘወትር ልምድ እንዲያዳብሩ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ እነዚህም ልምዶች ጠዋት መሳሳምን፣ ምሽት ላይ ደህና እደሩ መባባልን፣ ወደ ቤት የሚመለሰውን ሰው ደጅ ጠብቆ መቀበልን፣ አብሮ ሽርሽር መሄድንና በቤተሰብ የዕለት ተዕለት ሥራ መሳተፍን ያካትታሉ፡፡ ይህም ከተለመደው ሁኔታ ወጣ ብሎ ጊዜን በመዝናናት ለማሳለፍና የቤተሰብ ዓመታዊ ክብረ በዓላትንና ልዩ ሁነቶችን በደስታ ለማክበር ይረዳል፡፡ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች የምንንከባከብባቸውና ለሕይወት ያለንን ጉጉት የምናድስባቸው እነዚህን የመሰሉ ወቅቶች ያስፈልጉናል፡፡ መደሰት እስከቻልን ድረስ ፍቅራችንን ለማቀጣጠል፣ ከድግግሞሽ ነጻ ለማድረግና እያንዳንዱን ቀን በተስፋ ለመሙላት እንችላለን፡፡

227.  እኛ ጳጳሳት በእምነት እንዲያድጉ ቤተሰቦችን ማበረታታት አለብን፡፡ ይህም ማለት አዘውትረው ንስሐ እንዲገቡ፣ በመንፈሳዊ አቅጣጫ እንዲጓዙና አልፎ አልፎ ሱባኤ እንዲገቡ ማበረታታት ማለት ነው። እንዲሁም “አብሮ የሚጸልይ ቤተሰብ አብሮ ይኖራል” እንዲሉ በሳምንት ውስጥ የቤተሰብ ጸሎት እንዲኖር ማበረታታት ማለት ነው፡፡ የሕዝባችንን ቤቶች ስንጎበኝ፣ የቤተ ሰብ አባላትን ሁሉ መሰብሰብና ቤተሰቡን ለጌታ አሳልፎ በመስጠት ለእርስ በርስ አጭር ጸሎት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እያንዳንዳቸው የሚሸከሙት የየራሳቸው ምሥጢራዊ መስቀሎች ስላሏቸው፥ ከእግዚአብሔር ጋር ለብቻቸው የሚጸልዩበትን ጊዜ እንዲያገኙ ጥንዶችን ማበረታታት ጠቃሚ ነው፡፡ እኛስ ብንሆን ችግሮቻችንን ለምን ለእግዚአብሔር አንነግረውም? ፈውስንና በታማኝነት ለመኖር የሚያስፈልገንን እርዳታ እንዲሰጠን ለምን አንለምነውም? የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፣ “የእግዚአብሔር ቃል ለቤተሰብ የሕይወትና የመንፈሳዊነት ምንጭ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ሐዋርያዊ ሥራ ቤተክርስቲያን በጸሎት መንፈስ በምታነበው መጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት፣ ሰዎችን የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያን አባላት ሆነው እንዲቀረጹና እንዲታነጹ የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በግለሰብ ሕይወት ውስጥ የምስራች ቃል ብቻ ሳይሆን የጥበብ መመዘኛና ጥንዶችና ቤተሰቦች የሚያጋጥሙአቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች መለያ ብርሃን ነው” (252)፡፡

228.  በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ከጥንዶቹ አንዱ ያልተጠመቀ ወይም እምነትን ለመለማመድ የማይፈልግ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የሌላውን በክርስትና ሕይወት የመኖርና የማደግ ምኞት ሊያከብደውና አልፎ አልፎም አሳዛኝ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሆኖም፣ አንዳንድ የጋራ እሴቶችን ማግኘት፣ እነዚህንም እሴቶች መጋራትና መንከባከብ ይቻላል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ፣ አማኝ ላልሆነ የትዳር አጋር ፍቅርን ማሳየት፣ ደስታን መቸር፣ ቅሬታን ማለዘብና ሕይወትን መጋራት ወደ እውነተኛ ቅድስና የሚያመራ መንገድ ይሆናል፡፡ ፍቅር ምን ጊዜም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ይህ ፍቅር ተትረፍርፎ በሚፈስበት ቦታ ሁሉ፣ ብዙውን ጊዜ ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ፣ እንዲያውም “ያላመነ ባል በሚስቱ እንዲቀደስ፤ ያላመነችም ሚስት በሚያምን ባሏ እንድትቀደስ” (1 ቆሮ. 7፡ 14) የለውጥ ኃይል ይሆናል፡፡

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 212_ 229

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በረገኔ

20 Sep 2025, 16:19