የናይጄሪያ ብፁአን ጳጳሳት በሃገሪቱ የተከሰተውን ሁከት ለማስወገድ ሰላማዊ ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. በ 2023 ዓ.ም. በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ወቅት ገለልተኛ በሆነው የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ላይ “ፍትሃዊ ያልሆነ አሰራር፣ ማጭበርበር እና አጠራጣሪ የሆኑ የምርጫ ሂደቶች” መታየታቸውን ሊቀ ጳጳስ ሉሲየስ አስታውሰው፥ ይህም የሃገሪቱ ዜጎች በምርጫ ኮሚሽኑ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ማድረጉን አስረድተዋል።
የናይጄሪያ ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንቱ ከካላባር ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በምዕራብ አፍሪካ በተንሰራፋው ሙስና፣ ዓመፅ እና የጸጥታ ችግር ምክንያት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ብፁእነታቸው በ 2023 ዓ.ም. የተደረገው የናይጄሪያ ምርጫ የተካሄደበት መንገድ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልፆ፥ በዚህም የበርካታ ፖለቲከኞች ባህሪ እንዳሳሰባቸው እና ሀገሪቱ ከባድ የህልውና ስጋቶች ላይ እንዳለች ብሎም ባለስልጣናቱ የምርጫ ቅስቀሳ ቃላቸውን ከመፈጸም ይልቅ የ2027ቱ የፓርላማ ምርጫ ያሳሰባቸው ይመስላል ማለታቸውን ገልጿል።
ሊቀ ጳጳስ ኡጎርጂ በማከልም ‘ማህበራዊ መረጋጋትን ለመጠበቅ መሰረታዊ ማሻሻያዎች አስፈላጊ’ መሆናቸውን ጠቁመው፥ እነዚህን ለውጦች በሰላማዊ መንገድ ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች ለማደናቀፍ የሚጥሩ ሁሉ በኃይል የሚደረጉ ለውጦችን የማይቀር ያደርጉታል’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አለመተማመን፣ ፍርሃት፣ መፈናቀል፣ ድህነት
ብፁእነታቸው በናይጄሪያ የጸጥታ ችግር ተጠናክሮ መቀጠሉን በመጥቀስ፥ ይህም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በፍርሀት የሚኖሩ ማህበረሰቦች እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ዜጎች ታፍነዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሷል፣ ተገድለዋል፣ በየቀኑ ከቤት ንብረታቸው ተሰደው በጊዜያዊ መጠለያ ካምፖች እንዲጠለሉ ተደርገዋል፣ ለከፋ የአየር ንብረት በመጋለጥ ብዙ ጊዜ ምግብና ውሃ እንዳያገኙ ተደርገዋል” በማለት በምሬት ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በመቀጠል የጸጥታ እጦት ደግሞ ወጣቶችን ወደ ወንጀል፣ ወደ ስደት እና ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደሚገፋፉ ጠቅሰው፥ ከዚህም በላይ ወደ ከፋ ድህነትና ሥራ አጥነት እንደሚመራቸው አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ሉሲየስ ኡጎርጂ በመጨረሻም የሃገሪቱ ባለስልጣናት የፖለቲካ ትምህርቶችን በማቅረብ ናይጄሪያውያን በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲሳተፉ መርዳት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ ከዚህም ባሻገር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በጣም አስፈላጊ በሆነው ሀገራዊ ለውጥ ውስጥ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።