ቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍራሳቲ “እውነተኛ ወንድም” ነው ሲሉ ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎች መሰከሩ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. ሚያዚያ 6 ቀን 1901 ዓ.ም. በሰሜናዊ ምዕራብ ጣሊያን በምትገኘው ቱሪን ከተማ የተወለደው እና ሃምሌ 4 ቀን 1925 ዓ.ም. በ 24 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ድካም ያረፈው ወጣቱ ቅዱስ ፒየር ለመቶ ዓመታት የቆዩ ግጭቶች፣ ጦርነቶች እና መከፋፈሎች መካከል በህይወት የነበረ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ1925 በተከበረው የሰላም ኢዩቤሊዩ ወቅት በህይወት በመኖር እና በ 2025 ዓ.ም. እየተከበረ በሚገኘው የተስፋ ኢዩቤሊዩ ደግሞ ሢመተ ቅድስናው በመፈጸሙ ሁለቱን ኢዮቤልዩዎች በታሪክ አጋጣሚ አንድ ላይ ማገናኘቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ቅዱስ ፒየር በህይወት በነበረበት ወቅት የክርስቶስ ወዳጅና ወንድም ሆኖ እንደኖረ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስ ብለው ስላወጁለት ስለዚህ ወጣት ታሪክ ምስክርነታቸውን የሰጡት ከጣሊያን፣ ስፔን እና አርጀንቲና የመጡ እና ቅዱስ ፒየርን ወንድም እና የዕለት ተዕለት ህይወት አስተማሪ ብለው የሚጠሩ የ ‘ካቶሊክ አክሽን’ ማህበር ወጣት አባላት እና መሪዎች ሲሆኑ፥ የዕለት ተዕለት ማንነቱ በቅድስና እንደተሞላ እና ወደ እግዚአብሔር እና ወደ በጎ አድራጎት ሥራዎች የመራው የጸሎት ሕይወቱ እንደሆነ መስክረዋል።
ምን አይነት ሰላም ነው?
እ.አ.አ. ሐምሌ 6 ቀን 1925 ዓ.ም. የፒየር ፍራሳቲን በድን የያዘው የሬሳ ሣጥን በቱሪን ጎዳናዎች ሲያልፍ በታላላቅ ሰዎች የታጀበ ሳይሆን ከዚህ ይልቅ ማንነታቸው በማይታወቁ የድሆች ስብስብ የነበረ ሲሆን፥ ከመቶ ዓመት በኋላ ቅዱስ ወንጌልን ያለምንም ማመንታት በቁም ነገር የተገበረው ይህ ወጣት ቅድስናው በዕለቱ በተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ በይፋ እንደታወጀለት ተነግሯል።
ከዚህም ባሻገር ፒየር ፍራሳቲ የሰላም ኢዩቤሊዩ በተከበረበት ቅዱስ ዓመት ከዚህ ዓለም ማረፉ የሚታወቅ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት እየተከበረ በሚገኘው የተስፋ ኢዩቤሊዩ ቅዱስ ዓመት ቅድስናው መታወጁ ደግሞ ልዩ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
እነዚህ ሁለት የተለያዩ ዘመናት ‘ምን ዓይነት ሰላም ተስፋ እናደርጋለን?’ በሚለው እና በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም አስፈላጊ በሆነው ጥያቄ የተቆራኙ ሲሆን፥ ይሄንን ጥያቄ መመለስ ከእያንዳንዳችን እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው
የሢመተ ቅድስናው ሂደት ተሳታፊ የነበሩት ‘ካቶሊክ አክሽን’ የተባለው ተቋም ወጣት አባላት ስለ ፒየር ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ከሞተ ከመቶ ዓመት በኋላ እንኳን እኛን እያነጋገረ የሚገኘው ይህ ወጣት ዝም ብሎ ተራ ሃውልት ወይም የማይታይ ጀግና እንዳልሆነ ገልጸው፥ “እሱ ለእኛ እውነተኛ ወንድም ነው” በማለት ገልጸውታል።
እ.አ.አ. በ 1922 ዓ.ም. የተቋቋመው ‘ካቶሊክ አክሽን’ በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ ለመሳተፍ፣ በህብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር እና በጎ አድራጎትን ለማቅረብ ከአከባቢው ብጹአን ጳጳሳት ጋር በቅርበት በመተባበር የሚሰራ የካቶሊክ ምዕመናን ማህበር ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የቅዱስ ፒየርን ዓላማ ለማስቀጠል ከዶሚኒካኖች፣ ከቅዱስ ቪንሰንት ማህበር እና ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰራ እና ከጣሊያን እስከ አርጀንቲና ብሎም እስከ ስፔን ድረስ ምስክርነቱ አሁንም ድረስ እንደሚያስተጋባ ተገልጿል።
የካቶሊክ አክሽን ዩዝ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ሎሬንዞ ዛርዲ የቅድስናውን ዜና የሰሙት 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ብሔራዊ ምክር ቤት ጉባኤ ወቅት መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን፥ በወቅቱ በጣም ተደስተው እንደነበር እና ለረጅም ጊዜ በተስፋ ሲጠብቁት የነበረ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፥ ለእርሳቸው ፍራሳቲ ማለት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር ያለው ሰው ማለት እንደሆነ ገልጸዋል።
“የእርሱ የቅድስና መንገድ ለአሁኑ ጊዜ ታማኝ በመሆን በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ወንጌልን ስለመኖር ብቻ ነበር” ያሉት ሎሬንዞ፥ እርሱ በጎ አድራጊ ብቻ እንዳልነበረ፣ ድሆች ወደ እርሱ እንዲመጡ ብቻ የሚጠብቅ ሳይሆን እሱ ወደ እነርሱ የሚሄድ ሰው ነበር ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አልፎ አልፎ በሚከናወን የደግነት ተግባራት ላይ ብቻ መሳተፍ የሚያረካው ሰው ሳይሆን የበለጠ መልካም ውጤቶችን የሚያስገኙ መንገዶችን ይፈልግ እንደነበር፥ ብሎም ከአነስተኞች መካከል ክርስቶስን ለማገልገል የመረጠ ተማሪ እንደነበር የገለጹት ምክትል ፕረዚዳንቱ፥ ፖለቲካን በህዝባዊ ስሜት የኖረ ወጣት እንደሆነ፣ ብሎም ሁልጊዜ ከትንሹ ጀምሮ ለጋራ ጥቅም የሚያገለግል እና የሰላም መሰረት ሊሆን የሚችለውን ወዳጅነት የገነባ ወጣት እንደነበረ አስታውሰዋል።
አቶ ሎሬንዞ አክለውም ታሪኩን ለወጣቶች ማካፈላቸውን እንደቀጠሉ ጠቁመው፥ በዚህ ሂደት ውስጥ ራሳቸውን እንደገና እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
የሰኞ ቅዱሳን
በሮም የካቶሊክ አክሽን የወጣቶች መሪ የሆነችው አግኔስ ፓልሙቺ በበኩሏ ፒየር ማለት ለእሷ የሩቅ ቅዱስ ሳይሆን እውነተኛ ወንድም መሆኑን ጠቁማ፥ የዕለት ተዕለት ቅድስና ምን እንደሚመስል የሚያሳየን እውነተኛና የተለመደ ወጣት መሆኑን ገልፃለች።
“እራሳችንን ‘የሰኞ ሰዎች’ ብለን እንጠራለን” ያለችው አግኔስ፥ ምክንያቱንም ስታስረዳ እሑድ በየእለቱ መቀጠል ስላለበት እና እሱ የሰኞ ቅዱሳን ስለሆነ ተራውን ህይወት እንዴት መቀደስ እንዳለብን ያሳየናል ብላለች።
አግኔስ አክላም የእሱ አንድ መልካም ነገሩ ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ ምንጩ ምን እንደሆነ በግልጽ ማየት እንድንችል ማድረጉ ነው ያለች ሲሆን፥ ይህ ምንጭ ከሌለ የእነሱ እንቅስቃሴ ባዶ እንደሚሆን እና የእሱ በጎ አድራጎት ሥራ ተደብቆ እንደነበር፣ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለወላጆቹ እንኳን ሳይቀር በእውነት ምን ዓይነት ሰው እንደነበር የነገሯቸው ድሆች መሆናቸውን አስታውሳለች።
በፍትህ መጓደል ይበሳጭ እንደነበር እና ለፋሺዝም ፈጽሞ ያልተንበረከከ እንደነበር የገለጸችው አግኔስ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ ወደ አምላኩ ይማጸን እንደነበር እና አሁንም ድረስ በመልካም ተምሳሌትነቱ የተነሳ “እኔም እንደዛ መሆን እፈልጋለሁ” እንድንል ያደርገናል ብላለች።
በሮም ውስጥ በተጓዥ ኤግዚቢሽኖች እና ደብዳቤዎቹን ባማከሉ የንባብ ቡድኖች አማካኝነት የእሱ ትውስታ ዛሬም ድረስ ሕያው እንደሆነ ጠቁማ፥ ‘በእሱ ውስጥ ጸሎት ማለት ለእግዚአብሔር መስገድ ማለት እንደሆነ ማየት ትችላለህ’ ብላለች።
ከተራሮች ወደ ዲጂታል ዓለም
ከቦነስ አይረስ የመጡት የአርጀንቲና የካቶሊክ አክሽን ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ካርባጃል በበኩላቸው ከፍራሳቲ ህይወት ቁልፍ የሆነውን ክፍል ጎላ አድርገው በመግለጽ ‘በክርስቶስ ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት የቅድስና የጋራ መንገድ መሆኑን አሳይቶናል’ ብለዋል።
ከስፔን የመጣው ሌላኛው የካቶሊክ አክሽን ህብረት የወጣቶች መሪ ዳንኤል ዲያዝ በሁኔታው በጣም መደሰታቸውን ገልፆ፥ የካቶሊክ አክሽን ወጣት አባል በቅድስና መሠዊያዎች ላይ ሲነሳ ማየት ትልቅ ትርጉም እንዳለው በመጥቀስ፥ የቅዱሱ ህይወት በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ውስጥ ክርስቲያን መሆን እንደሚገባ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፍልናል ያለ ሲሆን፥ ጥላቻ በተሞላበት አካባቢዎችም ቢሆን እንኳን እምነትህን በድፍረት ማወጅ እንደሚገባ፣ ወጣት ማህበረሰቦችን መደገፍ እና የጋራ ግንዛቤን መፍጠር እንደሚገባ አስተምሮናል ብሏል።
ፈርናንዶ ቪጆ የተባለ ሌላኛው መስካሪ ፍራሳቲ ለወጣት ካቶሊኮች አርአያ መሆኑን ጠቅሶ፥ ተራሮችን የሚወድ፣ ለቅዱስ ቁርባን ጥልቅ ፍቅር ያለው እና ለድሆች ቅርብ መሆኑን በማስታወስ፥ “በጣም የገረመኝ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የነበሩት የቱሪን ድሆች መሆናቸው ነው” ሲል አግራሞቱን ገልጿል።
ከስምንቱ ብፁዓን ጋር
ጳጉሜ 1 የጣሊያኑ ካቶሊክ አክሽን በሮም “የፒየር ጆርጂዮ ፍራሳቲ ቅድስና በህይወት እና በታሪክ ውስጥ” በሚል ጭብጥ በቅዱስ ፒየስ 10ኛ አዳራሽ ውስጥ የተካሄደውን ጉባኤ ያዘጋጀ ሲሆን፥ ውይይቶቹ ጓደኝነት፣ ሰላም እና ማህበራዊ ፍትህ በሚሉ ሶስት ጭብጦች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የክራኮው ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት ፍራሳቲ “ከስምንቱ ብፁዓን ሰዎች አንዱ” እንደሆነ ገልጸው እንደነበር ተነስቷል።
እረፍት የማይሰጥህ ሰላም
ፍራሳቲ በአንድ ወቅት “እንደ ሌሎች ድሆች ሁሉ እኔም ድሃ ነኝ” ማለቱ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ እንቅፋቶችን የሚያፈርስ እና የሚንድ ማንነቱ እንደነበር ብሎም ሰብአዊነት የሚያሳስበው ሰው እንደነበር እህቱ ሉቺያና ጽፋለች።
“መልዕክቱ ውስብስብ እና የሽንገላ አልነበረም” ያለችው እህቱ፥ ለወዳጅነት እንዲሁም ወንድሞች እና ልጆች ስለሆኑ በመወለድ የሚገኘውን መብታቸውን ለሌሎች ለመስጠት የተደረገ ጥሪ እንደነበር ገልፃ፥ ይህም በጭፍን ተስፋ ሳይሆን በመከራ ውስጥ የሚገኝ ደስታ ነው ብላለች።
ወጣት ሮማውያን በቲሸርቶቻቸው ላይ ወጣቱ ቅዱስ በህይወት እያለ ከተናገራቸው አባባሎቹ ውስጥ አንዱ የሆነውን “ደስተኛ እንደሆንኩ ትጠይቁኛላችሁ? እንዴት መሆን አልችልም?” የሚለውን ጥቅስ እንዳሳተሙ እና ይህም በየዋህነት ስሜት ሳይሆን መልሱ በየቀኑ በፀጋ የተሞላ “አዎ ደስተኛ ነኝ” የሚል እንደሆነ ተነግሯል።
“እያንዳንዱ የማሳልፈው ቀን ዓለም ምን ያህል አስቀያሚ እንደሆነ፣ ምን ያህል በመከራ የተሞላ እንደሆነ የበለጠ ያረጋግጥልኛል” ሲል ፍራሳቲ የፃፈ ሲሆን፥ ነገር ግን እምነት እርግጠኛ በሆነ ድምጽ ‘አንተ ብቻህን ምንም ማድረግ አትችልም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የተግባሮችህ ሁሉ ማዕከል ከሆነ ግቡ ላይ ትደርሳለህ” ይለው እንደነበር በጽሁፉ ገልጿል።
ይህ የቅዱስ ፒየር ፍራሳቲ የተስፋ ራዕይ እንደሆነ፥ ለእግዚአብሔር መስገድ የሰላሙ ምንጭ እንደሆነ፣ እንዲሁም ጸሎትን ወደ ሕይወት፣ ፖለቲካን ወደ ፖለቲካዊ በጎ አድራጎት መለወጥ እንደሆነ ያስተምራል የተባለ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ተስፋ ሥጋ እንዲለብስ፣ ሰላምም ከቃል በላይ እንዲሆን ምን ያህል “አዎ” ለማለት ፈቃደኞች ነን? የሚለውን ሥር ነቀል ጥያቄ እንደሚፈጥር ተገልጿል።