የመስከረም 11/2018 ዓ.ም ሰንበት ዘፍሬ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ምንባባት
1. 2ቆር 9፡1-15
2. ያዕ 5፡1-9
3. ሐዋ. 19፡21-40
4. ማር 4፡24-38
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።
የአዳጊው ዘር ምሳሌ
ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ አጨዳ ይጀምራል።”
የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ
ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትላልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”
ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነ ግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?” አሉት።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማርቆስ ወንጌል 4፡26-34) ኢየሱስ ስለእግዚአብሄር መንግሥት እና የእድገቱን ጥንካሬ በተመለከተ ሁለት አጫጭር ምሳሌዎችን በመጠቀም ለሕዝቡ ይናገራል።
በመጀመሪያው ምሳሌ ላይ (ማር. 4፡26-29) የእግዚአብሔርን መንግሥት ከአንድ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ከምታድግ ዘር ጋር በማነጻጸር አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ዘሪው ምንም ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ በመጀመሪያ ቡቃያ፣ ቀጥሎ ዛላ፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች በማለት ይናገራል። ይህ ምሳሌ የሚያስተላልፍልን መልእክት የሚሆነው ኢየሱስ በስብከቱ እና በተግባሩ አማካይነት ያወጀው እግዚኣብሔርን መግሥት ልክ እንደ ዘር በዓለም ውስጥ በመዘዋወር በራሱ ኃይል እንደ ሚበቅል እና እንደ ሚያድግ፣ በሰውኛ አመለካከት ሊገለጽ በማይችል መልኩ በራሱ እንደ ሚበቅል የሚያመለክት መልእክት ያስተላልፍልናል። በታሪክ ውስጥ የእድገቱ እና የእድገቱ ሂደት በሰው ስራ ላይ ብዙ የማይመረኮዝ፣ ነገር ግን በተቃራኒው በእግዚኣብሔር ኃይል እና መልካምነት ላይ ብቻ የተመረኮዘ እንደ ሆነ፣ በእግዚአብሔር ሕዝብ ውስጥ ክርስቲያናዊ ሕይወትን የሚመራ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑን ያመለክታል።
አንዳንድ ጊዜ በእዚህ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሱት ተግዳሮቶችን እና ተዋናዮች ሰማያዊ አበታችን ለልጆቹ ሁሉ ያለውን የወንድማማችነት፣ የፍትህ እና የሰላም እቅድ በተቃራኒ አቅጣጫ በመሄድ ይመስላል። ነገር ግን እኛ በእነዚህን ጊዜያት ለመፈተን፣ ተስፋ ማድረግን እና በመጠባበቅ ላይ እንድንቆይ ተጠርተናል። በእርግጥ ልክ እንደ ትላንቱ ዛሬም የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለም ውስጥ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ እያደገች በሚያስደንቅ መንገድ ትናንሽ በምትባል ዘር ውስጥ በተደበቀ ኃይል አማካይነት ድል እየተቀናጀች ትገኛላች። አንዳንድ ጊዜ በግል ተግዳሮቶች እና በማሕበራዊ ጥፋቶች ምክንያት ተስፋችንን የሚጨለመ ቢመስልም ነገር ግን ኃይለኛ በሆነው የእግዚአብሔር ተግባር ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል። በእዚህ ምክንያት በጨለማ እና በችግሮች ውስጥ በምንገባበት ወቅቶች ሁሉ እኛ መርበትበት አይኖርብንም፣ በእግዚኣብሔር በመተማመን በእርሱ ላይ ጸንተን ልንኖር ይገባ፣ ሁልጊዜ በሚያድነው በእግዚኣብሔር ተስፋ መተማመን ይኖርብናል። ይህንን ሁል ጊዜ አስታውሱ፡ እግዚኣብሔር ሁሌም ያድናንል። እርሱ አዳኝ ነውና።
በሁለተኛው ምሳሌ ላይ (ማርቆስ 4፡30-32) ኢየሱስ የእግዚኣብሔርን መንግሥት ከአንድ የሰናፍጭ ዘር ጋር በንጽጽር ሲያቀርብ እናገኛለን። በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ ያልተጠበቀ አስገራሚ ዕድገት እንደ ምታሳይ ይናገራል። ለእኛ በእዚህ የእግዚኣብሔር አስተሳሰብ ውስጥ መግባት ወይም ይህንን መረዳት በጣም ቀላል የሆነ ነገር እና በሕይወታችን ውስጥ ይህንን እውነተ መቀበል በጣም ቀላል የሆነ ነገር አይደለም። ነገር ግን ዛሬ የእኛን እቅዶች፣ ስሌቶች፣ ትንበያዎቻችንን የሚያሸንፍ የእምነት አቋም እንዲኖረን ጌታ ያበረታታናል። እግዚአብሔር ሁሌም ያልታሰበ ነገር የሚያደርግ አምላክ ነው። ጌታ ሁሌም ያስገርመናል። በግለሰብ እና በማህበረሰብ ደረጃ ለእግዚኣብሔር የርኅራኄ እቅዶች በይበልጥ ራሳችንን እንድንከፍት የቀረበልን ግብዣ ነው። በማኅበርሰባችን ውስጥ ለሚገኙ ደካማ ለሆኑ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደ ሚገባን እና ጌታ ለእኛ ባሳየው በጎነት እንደ ታላቅ አጋጣሚ በመጠቀም በእርሱ ፍቅር፣ መስተንግዶ እና በሁሉም የምህረት ተግባራት ተነሳሽነት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል።
የቤተክርስቲያኗ ተልዕኮ እውነተኛነት የሚረጋገጠው ስኬታማ በመሆኗ ላይ ወይም ደግሞ አስደሳች የሆነ ውጤት በማስመስገቧ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ነገር ግን በታላቅ ብርታት በእግዚኣብሔር በመተማመን እና በእርሱ በመታቀፍ ወደ ፊት በመጓዟ ላይ የተመሰረተ ነው። እርሱን በመምሰከር እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ፊት መጓዝ። የእርሱ ትንሽ እና ደካማ መሳሪያ መሆናችንን ከግንዛቤ በማስገባት ራሳችን በእግዚኣብሔር እጅ ውስጥ በማድረግ እና በእርሱ ጸጋ በመተማመን ታላላቅ የሚባሉ ተግባራትን በመፈጸም የእርሱ መንግሥት መገለጫ የሆኑትን “ፍትህ፣ ሰላም፣ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚገኘውን ደስታ” ለማስፋፋት እንችላለን።
በዛሬው ቅዱስ ክፍል በሦስተኛ ደረጃ ኢየሱስ በውሃ ላይ ተራምዶ መሄዱን የሚገልጽ ቃል አዳምተናል (ማር. 4፡35-41)። በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕበሉን በኃይሉ ጸጥ ማድረጉን ሰምተናል። ደቀ መዛሙርቱ ተሳፍረው ሲጓዙበት የነበረው ጀልባ በብርቱ አውሎ ነፋስ ስለተመታ በሐይቁ ውስጥ የሚሰጥሙ መስሏቸው እጅግ ፈርተው ነበር። በዚህን ጊዜ ኢየሱስ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ፍርሃት ስለያዛቸው ወደ እርሱ ቀርበው “መምህር ሆይ! ስንጠፋ ዝም ትላልህን?” አሉት።
ብዙን ጊዜ እኛም ብንሆን በሕይወታችን ፈተና እና ችግር ሲያጋጥመን፣ ተስፋ አድርገን በምኞት የጀመርነው እቅዳችን ሲሰናከልብን፣ በጭንቀት ውስጥ ስንገኝ፣ በሕይወታችን ውስጥ ውድቀት ሲያጋጥመን፣ ሥራ በማጣት ይሁን ወይም በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ወደ ፊት መጓዝ ሲያቅተን ወይም ቤተሰቦቻችን ሆነ እኛ በማንድን በሽታ ተይዘን በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ስንገኝ፣ ወይም በሌሎች ችግሮች ውስጥ ሆነን፣ ኢየሱስ ሆይ! በችግር ውስጥ ስገኝ ለምን አትደርስልኝም በማለት ወደ ኢየሱስ ጮሄናል።
ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት እንደተጨነቁ ሁሉ እኛም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነን በፍርሃት የተጨነቅንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ተኝቶ የነበረ ቢሆንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ነበር። የሚሆነውን ነገር ሁሉ ይጋራቸው ነበር። ብርቱ አውሎ ነፋስ ተነስቶ ጀልባዋን ሲመታት፣ ደቀ መዛሙርቱም ደንግጠው ሲጮሁ፣ በሌላ ወገን ኢየሱስ ተረጋግቶ መተኛቱን ስንመለከት ይገርመን ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜ እና በሁሉ ስፍራ ከእኛ ጋር አለ። የእኛን ጩሄት፣ የእኛን ጥያቄ ይጠብቃል። በችግሮቻችን ውስጥ እርሱን እንድናሳትፍ እና እንድናስገባ ይፈልጋል።
የእርሱ ማቀላፋት ይበልጥ እንድንነቃ ያደርገናል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። እግዚአብሔርን ማመን ብቻውን በቂ አይደለም። እርሱ አለ ብሎ መቀመጥ በቂ እንዳልሆነ እንረዳለን። ከእርሱ ጋር መኖር ይጠበቅብናል። ከእርሱ ጋር ሆነን ድምጻችንን ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ሳንሰለች ጸሎታችንን ወደ እርሱ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጌታ ሆይ አድነኝ በማለት ወደ እርሱ መጮህ ያስፈልጋል። ዛሬ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በመሆኑ የደቀ መዛሙርቱ ድንጋጤ እና ጩሄት አንድ ነገር እንዳስታውስ አድርጎኛል። በትላልቅ ጀልባዎች ተሳፍረው የሜዲቴራኒያን ባሕር ሲያቋርጡ የነበሩ ስደተኞች አደጋ ባጋጠማቸው ጊዜ “አድኑን” እያሉ የነፍስ አድን ዕርዳታን ሲለምኑ ተመልክቻለሁ። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። በዚህ ጊዜ ታዲያ “ጌታ ሆይ እርዳን!”፣ “ጌታ ሆይ አድነን!” ብለን ጸሎታችንን እና ጩሄታችንን ወደ እርሱ እናቀርባለን።
ዛሬ እያንዳንዳችን ‘ሕይወታችንን የሚመታ አውሎ ነፋስ የትኛው ነው? በመንፈሳዊ ሕይወታችን ወደ ፊት እንዳንራመድ፣ ለቤተሰባችን ሕይወት እና ለስነ-ልቦናችንም እንቅፋት እየሆነብን የሚያደናቅፈን ማዕበል የቱ ነው’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ችግሮቻችንን በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንንገርለት። የመከራችን ጊዜ መሸሸጊያ እርሱን እናድርግ፣ ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው። ከማር. 4፡ 35-41 የተወሰደው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ይህን ይነግረናል። በማር. 4፡38 ላይ ‘ደቀ መዛሙርቱ ቀሰቀሱትና መምህር ሆይ! ስንጠፋ ዝም ትላለህን?’ አሉት ይላል። ስለዚህ ኢየሱስ እንድንቀሰቅሰው እና ችግራችንን በሙሉ እንድንነግረው ይፈልጋል። የእምነታችን መነሻ ይህ ነው። ምክንያቱም የመስጠም አደጋን፣ ማንኛውንም ችግር ብቻችን ልንቋቋመው አንችልም። መርከበኞች መንገዳቸውን ለማግኘት ኮከቦችን እንደሚፈልጉት ሁሉ እኛም ኢየሱስን እንፈልጋለን። እምነታችን የሚጀምረው ችግሮቻችንን ለማሸነፍ ብቻችን አቅም እንደሌለን ስናውቅ ነው። የእግዚአብሔር ዕርዳታ እንደሚያስፈልገን ስንገነዘብ ነው። ሊጋርደን የሚሞክረውን ፈተና ስንቋቋም፣ በጸሎታችን እግዚአብሔርን እንዳንጠይቅ የሚያደርግ የውሸት እምነት አሸንፈን ስንግኝ፣ እግዚአብሔር እርሱ በሕይወታችን ድንቅ ነገሮችን አድርጎ ሊያሳየን ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ ተዓምራትን ሊያደርግ የሚችል የጸሎት ኃይል ነው።
ኢየሱስም በደቀ መዛሙርቱ በተለመነ ጊዜ አውሎ ነፋሱን እና ማዕበሉን ጸጥ አደረገ። ከዚህም በኋላ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፥ ‘እንዲህ የምትፈሩት ለምንድን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?’ የማር. 4፡40. ደቀ መዛሙርትም በማዕበሉ ደንግጠው እና ፈርተው ስለነበር ኢየሱስን አይመለከቱም ነበር። ፍርሃት አዕምሮአችንን ወደ ችግራችን እንድናደርግ እንጂ ችግራችንን ወደሚፈታ ወደ ኃያሉ ጌታችን እንድንመለከት አያደርገንም። ለመሆኑ ስንቶቻችን ቀድመን ችግሮቻችንን ለኢየሱስ ከመንገር፣ የእርሱን ዕርዳታ ከመለመን ይልቅ በችግሮቻችን ላይ ብቻ እናተኩራለን? ችግር በበዛበት ሕይወታችን ውስጥ ስንት ጊዜ ኢየሱስን ወደ ጎን አድርገነዋል? ወይም በችግራችን ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ እንቀርባለን? ፈጽሞ ሳይደክም ዘወትር የኢየሱስን ዕርዳታ የሚፈልግ የእምነት ጸጋ እንዲበዛልን አጥብቀን መጠየቅ ይኖርብናል። እምነቷን ዘወትር በእግዚአብሔር ላይ ያደረገች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛም ዘወትር በእግዚአብሔር ተማምነን የሚያስፈልገንን ሁሉ ከእርሱ ለመቀበል የሚያስችለንን የእምነት ጸጋን እንዳታሰጠን በጸሎት እንማጸናታለን።
የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን